Friday, 24 June 2016

ትርምስ የኤርትራ መንግስት እስትንፋስ



 . ነጋሽ


 

የኤርትራ መንግስት ሰሞኑን በኢትዮጵያ ላይ ትንኮሳ መፈፀሙን ተከትሎ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጠንከር ያለ እርምጃ ወስዷል። የተወሰደውን እርምጃ አስመልክቶ በኢፌድሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች /ቤት በሰጠው መግለጫ እርምጃው በኤርትራ ለተፈፀመው ትንኮሳ የተሰጠ አፀፋ መሆኑን አስታውቋል። የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ ሚኒስትር ጌታቸው ረዳ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ማብራሪያ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በኤርትራ ጦር ላይ በወሰደው አፀፋዊ እርምጃ የደረሰው ኪሳራ ሻዕቢያ ለሚፈፅማቸው ጥፋቶች ሁሉ ቆም ብሎ እንዲያስብበት የሚያደርግ ነው ብለዋል። በዚህ አጸፋዊ እርምጃም የተፈለገው ውጤት ተገኝቷል ያሉት ሚኒስትሩ እርምጃው የኤርትራ መንግስት የሚያደርጋቸውን ትንኮሳዎች ሊያስቆም ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸው ብቻ ሳይሆን የኤርትራ መንግስት ከዚህ በኋላ የሚያደርገውን ትንኮሳ ከቀጠለ፣ መንግስት የሚወስደውን ተመጣጣኝ እርምጃ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።

 
የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ትንኮሳ ሲፈፅም ይህ የመጀመሪያው አይደለም። 1990 / በኢትዮጵያ ላይ ግልጽ ወረራ ፈፅሞ አሳፋሪ ሽንፈት ተከናንቦ ወደነበረበት ከተመለሰ በኋላ ባሉት አስራ ስምንት ዓመታት ይፋ ወረራ ለመፈጸም ባይደፍርም በተለያየ መንገድ ትንኮሳዎችን ሲፈፅም መቆየቱ ይታወቃል።
የኤርትራ መንግስት ህዝቡ የሚፈልገውን የኢኮኖሚና የማህበራዊ ልማት ፖሊሲና እቅድ ነድፎ የሚያስፈፅም፣ ዴሞክራሲንና ሰላምን ለማስፈን የሚሰራ ትክክለኛ የመንግስት ተግባራትን የሚያከናወን ተገቢ መንግስት (proper government) አይደለም። የኤርትራ መንግስት እነዚህን በየትኛውም ሃገር የሚኖር ህዝብ ፍላጎት የሆኑ ጉዳዮች በማሳካት በህዝብ ይሁንታ ስልጣን ላይ የመቆየት ፍላጎት የለውም። በአንድ ግለሰብ ፈላጭ ቆራጭነት የሚመራው የኤርትራ መንግስት ኤርትራን ነፃ ለማውጣት ያበረከተው አስተዋፅኦ እንደ ውለታ ተቆጥሮ ማብቂያ የሌለው ተጠያቂነት የሌለበት ሃገሪቱን የመግዛት ስልጣን ሊኖረኝ ይገባል ባይ ነው። ለዚህ ነው ኤርትራ የአለማችን ብቸኛ ህገመንግስት 2

አልባ ሃገር የሆነችው። ኤርትራ በህግ ሳይሆን ኢሳያስ አፈወርቂ በፈላጭ ቆራጭነት በሚያሳልፉት ውሳኔ የምትመራ ጉደኛ ሃገር ነች። ይህ ተጠያቂነት የሌለበት የአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭነት በዚህ ዘመን በማንኛውም ህዝብ ተቀባይነት የለውም። ኢሳያስ አፈወርቂ ተቀባይነት ለማግኘት የኤርትራ ህዝብ በመራራ ትግል ያገኘሁት ነፃነቴ ሊነጠቅ ነው የሚል አጉልና ከንቱ ስጋት እንዲያድርበት የማድረግ ስልትን ይከተላሉ። በመራራ ትግል ያገኘውን ነጻነት በውጭ ሃይል የማጣት ስጋት የተጋረጠበት የሚመስለው ህዝብ ነፃ አውጭውን ኢሳያስ መድህን አድርጎ በመውሰድ ከስጋት የመነጨ የገዢነት ይሁንታ እንዲሰጣቸው የማድረግ አካሄድ ነው የሚከተለው። በዚህ የተነሳ የኢሳያስ መንግስት ሁል ግዜ ጠላት ይፈጥራል። ሁልግዜ ጠላት ያለው ሆኖ በመታየት ህዝቡ ላይ ስጋት ለመፍጠር አካባቢውን የማተራመስ ስትራቴጂ ነድፏል። የኤርትራ መንግስት ዋነኛ መገለጫም ይሄውና ይሄው ብቻ ነው።
የኤርትራ መንግስት እንደመንግስት ከተመሰረተ ማግስት ጀምሮ አጎራባች ሃገራትን ያለማቋረጥ መተንኮስን ስራዬ ብሎ የያዘው ለዚህ ነው። በኢሳያስ አፈወርቂ ፈላጭ ቆራጭነት የሚመራው የኤርትራ መንግስት እንደተመሰረተ በመጀመሪያ ሱዳንን፣ በመቀጠል የመንን ወረረ፤ ከየመን በኋላ ወረራው ወደ ኢትዮጵያ መጣ። ትንሿ ሃገር ጀቡቲም ከኤርትራ ወረራ አላመለጠችም።
የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያ ላይ ወረራ የፈፀመው ኤርትራ ነፃ ሃገር ሆኛለሁ ባለች በስድስተኛው፣ የኢፌዴሪ መንግስት በተመሰረተ በሁለተኛው ዓመት ነበር። ይህን ያደረገው ቀደም ሲል እንደገለፅኩት ህዝቡ ወረራ ተፈፀመብን በሚል ስጋት መንግስቱን መድህን አድርጎ እንዲመለከት ነው።
በግልፅ እንደሚታወቀው የኤርትራ መንግስት በእነዚህ በግልፅ ወረራ በፈፀማቸው ጦርነቶች አልተሳካለትም። በተለይ ከኢትዮጵያ ጋር በገጠመው ጦርነት ክፉኛ በመመታቱ የሰራዊቱ ሞራል ክፉኛ ደቋል። ህዝብም በመንግስቱ ላይ ያለው እምነት ተሸርሽሯል። ወታደራዊ አቅሙም ተዳክሟል። በመሆኑም ዳግም ግልፅ ወታደራዊ ወረራ መፈፀም የማይችልበት ሁኔታ ላይ ወድቋል።

ይሁን እንጂ የኤርትራ መንግስት የሁሉንም ኤርትራውያን ይሁንታ አግኝቶ ሃገሪቱን መግዛት የሚችለው ጠላት በማብዛት ህዝቡ ላይ ስጋት መፍጠር ሲቻል ነው ብሎ ስለሚያምን አካባቢውን ማተራመሱን ቀጠሎበታል። የኤርትራ መንግስት ቀደም ሲል እንደገለፅኩት ሃገርን የማስተዳደር፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን የማምጣት፣ ሰላምና ዴሞክራሲን የማስፈን ህዝብን የማስተዳደር ስራ ከማከናወን ይልቅ ስጋት በመፈጠር መድህን ሆኖ መታየት ስለሚፈልግ አካባቢውን በተለይ ኢትዮጵያን የማተራመስ ስትራቴጂውን ገፍቶበታል።
የኤርትራ መንግስት የተከተለው ቀዳሚው ኢትዮጵያን የማተራመስ ስልት፣ በኢፌዴሪ ህገመንግስታዊ ሥርአት ሥር ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግን ያልመረጡ ተቃዋሚ ቡደኖችን አስጠልሎ ወታደራዊና የሽብር ጥቃት ስልጠና በመስጠት አስታጥቆ ወደኢትዮጵያ ማስረግ ነው። እነዚህ የኤርትራ መንግስት ወይም ኢሳያስ አፈወርቂ እጁን በማዝለቅ ኢትዮጵያን ለማጥቃት አላማ ያሰለጠናቸውና ያስታጠቃቸው ቡደኖች ሁለት አይነት ናቸው። በአንደኛው ወገን እንወክለዋለን የሚሉትን አካባቢ በሃይል የመገንጠል ዓላማ ያላቸው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) የመሳሰሉት የመሳሰሉ ናቸው። ሌላኛው ደግሞ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በፌደራላዊ ስርአት ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደራቸው ሃገሪቱን ይበታትናል የሚል አቋም ያላቸው ናቸው። እነዚህ ቡድኖች ቀደም ሲል በሃገሪቱ የነበረውን አሃዳዊ ስርአት የመመስረት ዓላማ ያላቸው ሲሆኑ የኢትዮጵያ አረበኞች ግንባር የተሰኘው ከእነዚህ አንዱ ነው። ግንቦት 7 የተባለው ቡድንም ይህንኑ አሃዳዊ ስርአት የመመስረት ዓላማ ይዞ 2000 / በሻአቢያ እጅ የገባ ቡድን ነው።
የኢሳያስ አፈወርቂ መንግስት በዚህ አኳኋን የሽብር ጥቃት ስልት ስልጠና የወሰዱ አሸባሪዎችን ፈንጂ አስታጥቆ በማስረግ የሽብር ጥቃት የመሰንዘር ተደጋጋሚ ሙከራ ሲያደርግ ቆይቷል። የኢሳያስ መንግስት 1998/99 መንግስት አልባ በነበረችው ሶማሊያ የተመሰረተውን አልሸባብ የተባለ ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድን ኢትዮጵያ ላይ ጥቃት እንዲፈፅም ወታደራዊ ስልጠና በመስጠት አስታጥቋል። የዓለም አቀፉ አሸባሪ አልቃይዳ የአፍሪካ ክንፍ ሆኖ የወጣው አልሸባብ 1989 / በኬንያና ታንዜኒያ የአሜሪካ ኤምባሲ ፅህፈት ቤቶች ላይ የተፈፀመውን የሽብር ጥቃት በጠነሰሱና ጥቃቱን በመሩ ግለሰቦች ጭምር የሚመራ መሆኑ ይታወቃል።

ይህ በኤርትራ መንግስት የወታደራዊ ስልጠናና የትጥቅ ድጋፍ የተደረገለት ቡድን 1998 / ኢትዮጵያ ላይ ግልፅ የጂሃድ ጦርነት አወጆ ነበር። የኤርትራ መንግስት ከአልሸባብ ጋር ወዳጀነት የመሰረተው በእስላማዊ አክራሪነት አይዲዮሎጂ ስለሚመሳሰሉ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ቡድኑ ኢትዮጵያን ሊያተራምስ የሚችል መሆኑ ነው በጥብቅ ያወዳጃቸው። የኢፌዴሪ መንግስት ጉዳዩን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማቅረብ አስወስኖ ወደሶማሊያ የመከላከያ ሰራዊቱን በማዘለቅ በወቅቱ ከነበረው የሶማሊያ የሽግግር መንግስት ጋር በመሆን የአልሸባብን የጂሃድ ወረራ ወደኢትዮጵያ ሳይሸጋጋር ማክሸፍ መቻሉ ይታወሳል። በወቅቱም የኤርትራ መንግስት ወታደሮቹን ወደአልሸባብ ይዞታ አስገብቶ ተዋጊዎችን እንደሚያሰለጥን፣ በራሱ አወሮፕላን መሳሪያ አጓጉዞ እንደሚያስታጥቅ በተጨባጭ ማስረጃ ተረጋገጠ።
ይህን ተከተሎ የኤርትራ መንግስት ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድንን በመደገፍና አካባቢውን በማወክ ተግባር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ክስ ይመሰረትባታል። ምክር ቤቱ የቀረበውን ክስ ትክክለኛነት አረጋግጦ በኤርትራ መንግስት ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ይወስናል። ይህን ጉዳይ የሚከታተል የኤርትራና ሶማሊያ አጣሪ ኮሚቴም ተሰይሟል። ይህ ኮሚቴ አሁንም የኤርትራን ጉዳይ እየተከታተለ ይገኛል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአልሸባብ በኩል ኢትዮጵያን የማጥቃቱና የማተራመስ ስልቱ የከሸፈበት የኤርትራ መንግስት፣ ቡድኖቹ ለሚያራምዱት ዓላማ ስኬት ሳይሆን ኢትዮጵያን የማተራመስ ስትራቴጂውን ለማስፈፀም ዓላማ ያሰባሰባቸውን ቡድኖች በሽብር ጥቃት በማሰልጠንና በማሰታጠቅ ወደኢትዮጵያ ማስረጉን ቀጥሎበታል። በተለያየ ግዜና አቅጣጫ የኦነግን በኋላም የግንቦት 7 አባላትን በሽብር ጥቃት ስልት አሰልጥኖ ወደሃገር ውስጥ አስርጓል። በተለይ 2000 / በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ በሚካሄድበት ወቅትአዲስ አበባን ባግዳድ የማድረግየሽብር ተልእኮ የተቀበለና የተደራጀ ቡድን ወደኢትዮጵያ አዲስ አበባ ዘልቆ እንደነበረ ይታወሳል። አዲሰ አበባ ውስጥ ህዝብ የሚሰበሰብባቸው፤ ፍል ውሃ፣ የተለያዩ ሆቴሎች፣ የህዝብ መጓጓዣ አወቶቡሶች ወዘተ በማፈንዳት የንፁሃንን ህይወት የማጥፋት ተልዕኮ ተቀብለው የተሰማሩ ግለሰቦች በተደጋጋሚ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወቃል። በቅርቡ በአርባ ምንጭ አካባባ ሲንቀሳቀሱ በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች የኤርትራ መንግስት አሁንም በሽብር ጥቃት ኢትዮጵያን በማተራመሰ ተግባሩ እንደገፋበት ያረጋግጣል። ከኤርትራ የሰረጉ አሸባሪዎች ያቀዷቸው የሽብር ጥቃቶች ግን በሙሉ አልተሳኩም፤ ከሽፈዋል።
የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ኤርትራ አካባቢውን ለማተራመስ በፈፀመችው ጥፋት የጣለባትን ማዕቀብ አፈፃፀምና ሃገሪቱ ያሳየችውን መሻሻል የሚከታተለው የሶማሊያና የኤርትራ የክትትል ኮሚቴ ባለፈው ዓመት ለፀጥታው ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት፣ ኤርትራ አልሸባብን የምትረዳ መሆኑን የሚያመለክት መረጃ ባይኖርም በኢትዮጵያ በጦርነት የመንግስት ለውጥ ለማምጣት የሚንቀሳቀሱ ቡደኖችን እንደምትደግፍ ማረጋገጡን አስታውቋል። በዚሀ መነሻነት ማዕቀቡ ለአንድ ዓመት እንዲራዘም ምክር ቤቱ ውሳኔ አሳልፏል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኤርትራ ተፈፅሟል የተባለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲመረምር ያቋቋመው ይሄው አጣሪ ኮሚሽን ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ሪፖርት ደግሞ የአገሪቱ መሪዎች ዜጎችን በግፍ እያሰቃዩ ነው፤ በአስገድዶ መድፈር እና ግድያ ላይም ተሰማርተዋል በአጠቃለይ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እየፈፀሙ ነው ብሏል የፀጥታው ምክር ቤት ማዕቀብ እንዲጥል እና በዚያች አገር ይህን የሰብዓዊ መብት ጥሰት መመልከት የሚችል ፍርድ ቤት ባለመኖሩ ጉዳዩን ወደ አለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እንዲመራውም ጠይቋል። ኤርትራ ነፃነቷን ካገኘችበት 1991 / ወዲህ ወሰን ከሌለው የውትድርና ግዳጅ ጀምሮ በሀገሪቱ በርካታ ግፎች እንደሚፈፅሙ የመንግስታቱ ድርጅት አጣሪ ኮሚሽን ሊቀመንበር ማይክ ስሚዝ ገልፀዋል። እንደ ሪፖርቱ ባለፉት 25 አመታት 300 ሺህ እስከ 400 ሺህ ኤርትራውያን በግዳጅ በብሄራዊ ውትድርና ተሰማርተዋል።
የአጣሪ ኮሚሽኑ ሪፖርትአንዳንድ ግለሰቦች፣ በተለይም የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ የገዥው ፓርቲ ዋነኛ አመራሮች ለዚህ በሰው ልጅ ላይ ለሚፈፀም ወንጀል እና ተያያዥ የመብት ጥሰቶች ተጠያቂ መሆናቸውንም ይግልፃል።
ይህ በሪፖርቱ ላይ የሰፈረ ዕውነታ የኤርትራ መንግስት ከራሱም ህዝብ አልፎ በመላው ዓለም እንዲተፋ እንደሚያደርገው እርግጥ ነው። እናም እንደለመደው ህዘቡ የወረራና ነፃነቱን የመነጠቅ፣ የመደፈር ስጋት እድሮበት ይሁንታውን እንዲሰጠው የትርምስ ስልቱን በአዲስ መልክ ለመፈጸም የሚያስገድድ አጣብቂኝ ውስጥ ከቶታል። ሰሞኑን ኢትዮጵያ ላይ ትንኮሳ ፈፅሞ ሲያበቃ ወረራ ተፈፀመብኝ ብሎ ያወራው በዚህ ምክንያት። የሰሞኑ የኤርትራ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የፈፀመው ትንኮሳ መንስኤም እዚሁ አጣብቂኝ ውስጥ ከመግባቱ ውጭ ሌላ አይደለም።
የኢትዮጵያ መንግስት በህገመንግስት የሚመራ መንግስት ነው። በህገመንግስት የተደነገገ ግልፅ የውጭ ግንኙነት መርህ፤ ከዚህ መርህ የመነጨ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲም ያለው መንግስት እንጂ እንዲሁ በዘፈቀደ የሚመራ አምባገነናዊ ስርአት አይደለም። በእነዚህ ፖሊሲዎች መሰረት ከሃገራት ጋር የሚመሰርተው ግንኙነት ሰላምን የሚያረጋግጥና በመጠቃቀም ላይ የተመሰረተ ነው። እናም በፖሊሲ ደረጃ ወረራ እንዲፈፅም የሚፈቅደለት ምንም አይነት ክፍተት የለም።
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግስት፣ የኤርትራ መንግስት ወረራ ፈፅሞ ወሰኔን ይቆርሳል ወይም የከፋ ጉዳት ያደርስብኛል የሚል ስጋት የለበትም። በመሆኑም ኤርትራ ላይ ወረራ እንዲፈፅም የሚያነሳሳው አንዳችም ምድራዊ ምክንያት የለም። የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ጥቃት ሊሰነዘርብኝ ይችላል የሚል የሩቅ ስጋት ቢኖርበት እንኳን ይህን ለመከላከል እንደመርህ የያዘው ሃገራትን ወርሮ በማጥቃትና በማዳከም አይደለም። ከዚህ ይልቅ ለጥቃት የሚያጋልጠው ድህነት በመሆኑ ድህነትን አስወግዶ ለዘለቄታው ጠንካራ የመከላከያ ሃይል መገንባት ነው።
የኢትዮጵያ መንግስት ወረራንና የኤርትራ መንግስት አሸባሪን በማስረግ የሚፈፅምበትን የማተራመስ ጥቃት ተፅእኖ ለዘለቄታው መከላከል የሚያስችለው መንገድ የሃይል እርምጃ ሳይሆን ድህነትን መዋጋት መሆኑን አምኖ በዚሁ ላይ ያተኮረ መንግስት ነው። ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሲያደርግ እንደነበረው ሰሞኑንም እንዳደረገው ጥቃት ሲሰነዘርበት አስተማሪና ተመጣጣኝ የአፀፋ እርምጃ ይወስዳል። የኤርትራ መንግስት ጠላት ካላፈራ ህልውናው የሚያከትም ስለሚመስለው ማለትም ትርምስ እስትንፋሱ በመሆኑ ጠላት ለማፍራት ደግሞ አካባቢውን በተለይ ኢትዮጵያን ማተራመስ ስለሚኖርበት በቀላሉ አድቦ ይቀመጣል ብሎ መገመት ስህተትነቱ የሚያይል ይመስለኛል። እናም ለወደፊት፣ በቀጥታም ይሁን ተላላኪዎቹን በማስረግ ሊፈፅመው በሚችለው ጥቃት በአንድም ዜጋ ላይ ቢሆን ጉዳት እንዳያደርስ ጥንቃቄ ሊደረግ የሚገባ መሆኑ መዘንጋት የለበትም።

No comments:

Post a Comment