Monday, 30 May 2016

የመጨረሻዋ ጥይት (The Last Bullet) የመጨረሻ ክፍል (ዘመቻ ወጋገን)






ሊነጋ ሲል….
ግንቦት 20 1983 የኢትዮጵያ ህዝች በልዪ ሁኔታ የሚያስታውሷት አመትና እለት ናት!
አዲስ አበበ በሶስት አቅጣጫ በኢህአዴግ ሰራዊት ተከባለች”” ከየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል የሚወጣም የሚገባም የለም”” የቀለበቱ ማጥበብ ቀጥሏል፡፡ አምቦ የነበረው ሰራዊት ወደ ሆለታና ታጠቅ ተጠጋ፡፡ በጅማ በኩል የነበረው ግልገል ግቤን ተሻግሮ ወሊሶን አልፎ ወደ አለም ገና ተጠግቷል፡፡ ደብረብርሃን የነበረው ሃይል ገሚሱ ወደ ደቡብ ምስራቅ በመጓዝ ደብረዘይትን ከበባት፡፡ ማንኛውም የጦር አውሮፕላን ወደ ሰማይ አልወጣም”” አልወረደምም፡፡ እናም በሳሞራ ዮኑስ የሚመራ ሶስተኛ ግንባር ተፈጠረ፡፡ ደብረ ብርሃን የነበረ በፃድቃን ገ/ትንሳኤ እየተመራ ሰንዳፋ ገባ፡፡
የኢህአዴግ ሰራዊትን ጉዞ የሚቋቋም ሃይል ያልነበረ ቢሆንም ጉዞው እንዲገታ በድርጅቱ ቁንጮ ታዘዘ፡፡ በመጨረሻ ሰአትም ኢህአዴግ ከጦርነት ሰላምን ምርጫው አድርጓል፡፡ በወቅቱ ከደርግ ልኡካን ለንደን ላይ ለውይይት /ድርድር/ ተቀምጦ ነበር፡፡ ደርግ በወቅቱ አንድ እግሩ ብቻ ሳይሆን ሁለቱም እግሩ ጉድጓድ ላይ ገብቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ምን ይሁን ምንም ጥይት በተተኮሰ ቁጥር የሰው ህይወት መቀጠፉ አይቀርም፡፡ አጠቃላይ ሁኔታው በኢህአዴግ ቁጥጥር ላይ ነበር፡፡ ነገር ግን ባለቀ ሰአት ከወደቀ መንግስት የሰላም ውይይት ለምን አስፈለገ የሚል መነሳቱ ተገቢ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ በሶስተኛ ወገን ብቻ ሳይሆን የአዲስ አበባ ብርሃን ወጋገን ማታ ማታ ለሚታያቸው ታጋዮችም ጭምር እንቆቅልሽ ነበር፡፡ ነገር ግን ታጋዮች ለአመታት በገነቡት በአመራራቸው ላይ በነበራቸው የፀና እምነት ግን ለበለጠ ድርጅታዊ ፋይዳሲባል መሆኑ እንዲሁ ገብቷቸዋል፡፡ ሶስት ረጃጂም ቀናትም ከእንጦጦ ተራራ ጫፍ ተጠግቶ ሌላ ትእዛዝ ተጠባበቀ፡፡ በወቅቱ በርካታ ፖለቲካ ተንታኞች አዲስ አበባ የሞቃዲሾና የሞኖሮቭያ እጣ ፈንታ እንደሚያጋጥማት ተነበዩ፡፡ የከተማው ጎዳናዎች አውደ ግንባር ይሆናሉ፤ ጎዳናዋ በሰው ሬሳ ይሞላሉ፤ ህንፃዎቿ ወደ ፍርስራሽ ይቀየራሉ የሚል ትንታኔያቸውን አሰሙ፡፡ እንደ ኢድሃቅ /በኢህአፓ ግንባር ቀደምትነት የተሰባሰበ ስደተኛ ሃይል/ ፀረ ኢህአዴግ የትጥቅ ትግል እንደሚቀጥል አሳወቀ፡፡ በስብስቡም ኢህአፓ፣ የሃይለስላሴ አልጋወራሾች፣ ኢድዩ ተሰባሰቡ፡፡ በመጨረሻ ግን ኢዲዩ ከስብስቡ ወጥቶ ወደ ሽግግሩ ተቀላቀለ፡፡
አዲስ አበባ ሰላም ደፍርሶ የከተማው ወሮ በላ ሊያናውጣት ደረሰ፡፡ ዝርፍያ ተጀመረ፡፡ ማን እንደሚተኩሰው የማይታወቅ በከተማው ተኩሱ ይሰማል፡፡ ይህንን አቁም የሚል ሃይል የለም”” በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሃየሎም አርአያ እንዲህ ይገልፀዋል፡፡
“በአዲስ አበባ ከባድ ጦርነት እንዳይካሄድ በህዝብ ላይ እልቂት እንዳያስከትል በሰላማዊ መንገድ ለመቋጨት ለንድን የተጠራው የሰላም ውይይት ኢህአዴግ ተቀብሎት የድርጅቱ ሊቀመንበር ልኮ እየተነጋገረ ባለበት አዲስ አበባ ላይ ስርአት አልበኝነት ነገሰ”” በተለያየ መንገድ ወደ ከተማ ያስገባናቸው ታጋዮች ያለው አማራጭ የኢህአዴግ ሰራዊት መግባት ብቻ መሆኑ ነገሩን፡፡ ጊዜ መውሰድ በህዝብና ሃገር ንብረት ላይ ተጨማሪ ጉዳት መፍጠርና የባሰ አደጋ እንዲከሰት ማድረግ መሆኑን በአፅንኦት ነገሩን፡፡ እናም በመጨረሻ እንድንገባ ተወሰነ፡፡” ይላል፡፡
የኢህአዴግ አመራር ወደ ከተማው ያሰረጋቸው የስለላ አባላቱ፣ ግንቦት 17 ሾልከው እንዲገቡ የተደረጉ ልዩ ስልጠና የወሰዱ 20 የሚሆኑ የኮማንዶ አባላትና በከተማው በመከላከያ ሚኒስተር፣ በሃገር ውስጥ ደህንነትና በተለያያ የመንግስት መዋቅር በነበሩ ነባር የከተማ አባላቱ በኩል በቂ እውቀትና መረጃ ነበረው፡፡ የከተማ አባላቱ ሰንደፋ ወደ ነበረ ሃይል በመሄድ ስለጠላት አቀማመጥ፣ የወሳኝ የመንግስትና የኢኮኖሚ ተቋማት መገኛ ዝርዝር መረጃዎች ያቀብላሉ፡፡ ከዚህም አልፎ ከኮማንደሮቹ ጨምሮ አዲስ አበባን በአካል ለማያቃት የኢህአዴግ ሰራዊት በካርታ ብቻ ለሚያቃቸው ምድብ ቦታዎቹና መስመሮቹ እንዲመሩም ተመድበው ቦታ ቦታቸውን ይዘዋል፡፡ ሂደው ተቀላቅለዋል”” የለንደኑ ኮንፈረንስ ትርጉም አልባ ሆኖ ከመቋጨቱ በላይ በቆይታው አዲስ አበባ የአመፃ ከተማ ሆነች፡፡ ኢህአዴግ ከገባ ከተማዋ ሞኖሮቪያ ትሆናለች ሲባል መንግስት አልባ አዲስ አበባ የስርአት አልበኞች ሆነች፡፡ ይህ ለአመታት ለህዝብ ሰላም ሲታገል ለነበረውና መስዋእት የከፈለው ታጋይ የሚያም ትእዛዝ ነበር፡፡
ግንቦት 19/1983 ልክ ከቀኑ 10 ሰአት ወታደራዊ ዘመቻውን በበላይነት የሚያስተባብረው ቡድን ለመጨረሻ የሰላም ውይይት ሎንደን ከነበረው የበላይ አመራር “ቀጥል” የሚል አጭር መልእክት ደረሰው፡፡ ቀድሞ በተደረገው ጥናት አዲስ አበባ በሶስት ግንባር ተከፍላለች፡፡ በአምቦ ግንባር የነበረው በጎጃም በር በኩል ወደ ፒያሳ በመዝለቅ መርካቶን ተቆጣጥሮ ወደ ጅማ መንገድ ያመራል፡፡
ሁለተኛው ግንባር በደብረዘይት የሚመጣ በአቃቂ ገብቶ ንፋስ ስልክ፣ ጎተራ፣ ቄራ፣ አራተኛ ክፍለጦር፣ ስታዲየም ጨምሮ እስከ ሜክሲኮ ያለውን ይይዛል፡፡
ሶስተኛው በሰንዳፋ የሚመጣ በኮቴቤ በመውረድ ብረታ ብረት ፋብሪካ ከደረሰ በኋላ ለሶስት ንኡስ ግንባር ይከፈላል፡፡ አንዱ በመገናኛ በኩል ወደ ኤርፖርት ያመራል፡፡ ሁለተኛ ክፍል 22 ሰንጥቆ ወደ መስቀል አደባባይ በመሄድ ታችኛው ቤተመንግስት ይቆጣጠራል፡፡ ሶስተኛው ክፍል በእንግሊዝ ኤምባሲ አቅጣጫ በግንፍሌ አድርጎ ወደ አራት ኪሎ በመግባት ቤተመንግስትን ይቆጣጠራል፡፡
ኮማንደሮቹ ይህንን ድልድል በማድረግ ሌሊቱን በሙሉ ሲዘጋጁ አደሩ፡፡ እነ ሐየሎም በነበሩበት አቅጣጫ ታጠቅ አካባቢ የነበረው ሃይል ማታ ወደ ከተማ የመፍረስ ምልክት ስለታየ ይህ ሃይል ወደ መሃል ከተማ ከገባ አላስፈለጊ ዋጋ የሚያስከፍል ውጊያ ስለሚያስከትል አስቀድሞ መያዝ አለበት ተብሎ ስለ ተወሰነ በዋዜማው የተወሰነ ሃይል ቀድሞ ወደ ቦታው እንዲጠጋ በማድረግ በኮልፌ 18 ማዞሪያ በኩል ተዘጋ፡፡ ከከተማው ወደ ውጪ እንዲበተንም ተደረገ፡፡
አስቀድሞ የወጣው ስትራቴጂ በሚገባ የሰራ መሆኑ እየተረጋገጠ ነው፡፡ የመንግስት አብዛኛው ወታደር ከአዲስ አበባ ከመግባቱ በፊት እንዲበታተን ተደረገ፡፡ ስለሆነም ከተበተነ ወታደር ማለትም ገሚሱ መሳሪያ የያዘ ገሚሱ መሳሪያ የሌለው እየተንቀረፈፈ ከሚገባ በስተቀር ተደራጅቶ ወደ ከተማዋ የሚያፈገፍግ ሰራዊት አልነበረም፡፡ ይህ ለኢህአዴግ ትልቅ ድልና ስኬት ነበር፡፡ በህዝቡ ዘንድም ስጋትን የቀነሰ ነበር፡፡
የወጋገን ዘመቻ ዋና አላማው የቀረውን ሰራዊት መደምሰስ ሳይሆን ከተማዋን በብልሃት መቆጣጠር ነበር፡፡ የወጋገን ዘመቻ ሲነሳ አግአዚ ክፍለጦርን ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ አግአዚ ማለት ነፃ አወጣ ማለት ነው፡፡ ለክፍለሰራዊቱ ስያሜው የተሰጠው ግን የህወሓት የከተማ ክንፍ ይመራ የነበረውና በ1968 በተሰዋ ዘርኡ ገሰሰ የበረሃ ስሙ አግአዚ ነበር፡፡
የመጨረሻው ቤተ መንግስት እንዲቆጣጠር ተልእኮ የተሰጠው ይህ ክፍለ ጦር ነው፡፡ አግአዚ ክፍለ ሰራዊት አምስት ሬጂመንት ነበራት ከአምስቱ ሁለቱ /1ኛ ሬጂመንትና አራተኛ ሬጂመንት/ በቀጥታ ቤተመንግስት ተመድበዋል፡፡ አምስተኛ ተብላ የምትቆጠረው የተንቀሳቃሽ ከባድ መሳሪያ ምድብ ስትሆን በወቅቱ በተደረገ ማስተካከያም ለሁለት በመክፈል በሁለቱ ሬጂመንቶች የተኩስ አቅም ሆና ተመደበች፡፡ አንዷ ሬጂመንት ኤርፖርት እንድትቆጣጠር ተመድባለች፡፡ አንዷ ደግሞ ተጠባባቂ ሆና መገናኛ ላይ የቦታ ማስተካከያ አድርጋ ትጠባበቃለች፡፡ የክፍለ ሰራዊቷ ኮማንደር ምግበይ ሃይሌ ቤተ መንግስት አካባቢ ከበድ ያለ ተቃውሞ ሊገጥም እንደሚችል ገምቷል፡፡ ምክንያቱም ቤተ መንግስት ላይ የሰፈረው ቅልብ ጦር ራሱን የስርአቱ ዋና ጠባቂ አድርጎ እንዲቆጥር ተደርጎ የተቀረፀ ነው፡፡ አዲስ አበባ የነበሩ የኢህአዴግ አባላትም ሰንዳፋ ድረስ ወጥተው ዝርዝር መረጃና ዝግጅቱን ሰጥተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ሁለት አይነት ሃይል ነበረ”” አንዱ መጀመሪያውም አዲስ አበባ ምድብተኛ የሆነ ሰራዊት ሲሆን ሌላው ደግሞ በየአቅጣጫው እየተንጠባጠበ የገባ ሰራዊት ነው፡፡
አብዛኛው የኢህአዴግ ሰራዊት አባልና ሰራዊት አመራር ከተማዋን አያውቃትም፡፡ የአዲስ አበባን ስፋት በአይነ ህሊናውም ማሰብ አይችልም፡፡ መደረግ ያለበትና የሌለበት ተጨማሪ ማብራሪያ ተሰጠው፡፡ አንዳንዱ የአፍሪካ ህብረት ፅህፈት ቤት አዲስ አበባ እንደሚገኝም የሚያውቅ አልነበረም፡፡ በርካታ ኤምባሲዎችና አለም አቀፍ ተቋማት እንዳሉ እና ወደ እነዚህ ግቢዎች መግባት እንደማይቻል የጠላት ሰራዊት ሰብሮ ቢገባ እንኳን ከቅርብ ርቀት ሆኖ መከታተል እንጂ መግባትም ወደ ግቢው መተኮስም እንደማይችል ማብራሪያ ሲሰጠው ለብዙ ታጋይ አዲስ ነገር ነበር፡፡
እንዲህ ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት ገና በለጋ እድሜያቸው ወደ ትግል የተቀላቀሉት ምግበይ ሃይለ የክፍለ ሰራዊቱ አዛዥ በመጨረሻ ሰአት ሲያጋጥሙ የነበሩ መስዋእት ከምንም በላይ ያሳዝንዋቸዋል፡፡ ሰንዳፋ እያሉ እንዲህ ሆነ፡፡ የሬጂመንት 3 ድርጅት አመራር የሆነች ጓል ጎዳን የምትባል ታጋይ ነበረች”” አመራሩ የክፍለ ሰራዊቱ አመራር በነበረበት ቦታ ተገኝተው ኦረንቴሽን ሲወስዱ አምሽተው በፒክ አፕ ሲመለሱ ሹፌሩ ያላየው ጎርጅ ነበርና ድንገት ሲገባ ከፒክአፑ እላይ የነበረች ጓል ጎዳን ተስፈንጥራ ወደ አስፋልቱ ወደቀች፤ እዛም ተሰዋች፡፡ ሁሉም ታጋይ ያሳዘነ አጋጣሚ ነበር፡፡
ለግንቦት 19 አጥቢያ ነበር፡፡ የግንባሩና የክፍለ ሰራዊት አመራሮች ከፊታቸው የመረጃ ቡድን አስቀድመው ለመጨረሻ አካላዊ ጥናት ሰንዳፋን አልፈው ወደ ለገዳዲ አቅጣጫ አመሩ”” የኮተቤ አካባቢ ተራሮች ላይ ጠላት ሊኖር ስለሚችል እንዴት ማለፍ ይኖርብናል የሚል ለማጥናት ነበር፡፡ በወቅቱ ለጋዳዲ አንድ የመንግስት ብርጌድ ነበር፡፡ የኢህአዴግ ሰራዊት አመራሮች ይህንን ብርጌድ አልፈው ወደ ውስጥ ገብተዋል፡፡ አመራሮቹ አበበ ተክለሃይማኖት /ጆቤ/፣ ነጋሽ ሕሉፍ፣ ግርማይ ማንጁስ፣ ሳልሕና ምግበይ ነበሩ፡፡
አብዛኛዎቹ አዲስ አበባን የሚያውቋት በካርታ ነውና ካርታ ዘርግተው አስፋልት ላይ ማየት ጀመሩ”” ካርታውና አከባቢውንለማነፃፀር፡፡ በዚህ መሃል ነበር አንድ ወታደር የያዘች አይፋ ከተፍ ያለችባቸው፡፡ አመራሮቹ ለብቻቸው ነው ከአንድ ክላሽን ውጭ የነበራቸው መሳሪያ የታጠቁት ሽጉጥ ብቻ ነበር፡፡ ወታደሮቹም ሲያይዋቸው ተደናግጠው ተኩስ ከፈቱ”” ከአመራሩ የነበሩ ኦፕሬተሮች ወደ መኪናዋ ቦምብ መወርወር ጀመሩ፡፡ አይፋ ላይ የነበሩ ወደ 20 የሚገመቱ ወታደሮች መሳሪያቸውን ማንጣጣት ጀመሩ፡፡ ከተወሰነ ተኩስ በኋላ በተለይ ሹፌሩ ጎይተኦም በተባለ አፕሬተር በተወረወረ ቦምብ በመቁሰሉ ወታደሮቹ ተደናግጠው ተበታተኑ፡፡ ገሚሶቹም ተማረኩ፡፡ ታጋዮቹም አይፋውን ይዘው ወደ ቦታቸው ተመለሱ፡፡
የግንቦት 20 መባቻ፡፡ ልክ ከሌሊቱ ሰባት ሰአት ሰራዊቱ ወደ ከተማዋ እንዲገባ ታዘዘ፡፡ ሰራዊቱም ከሰንዳፋ መንቀሳቀስ ጀመረ”” ጉዞው ግን በጥንቃቄና እያንዳንዱ የኮተቤ ተራሮችና ሾጦችን እየፈተሹ ይደረግ ነበርና ረጂም ጊዜ ፈጀ፡፡ ነገርግን ምንም አይነት የተኩስ ተቃውሞ አልነበረም፡፡ በየቦታው የሚያጋጥማቸው ወታደር መሳሪያውን እያስረከበ እጁን ይሰጣል፡፡ ንጋት ላይ መገናኛ ደረሰ፡፡ መገናኛ ላይ ሲደርስ ቀድሞ በወጣ እቅድ መሰረት ለሶስት ተከፈለ ወደ ዜናዊ የሚባል የክፍለ ሰራዊቱ የድርጅት ሃላፊ አንዱን ክንፍ፣ ገብረኪዳን ኮሚሳሪያ የሚመራው ሁለተኛ ክንፍ፣ ምግበይ የክፍለ ሰራዊቱ አዛዥ አንድ ክንፍ ያዙ፡፡
ሶስት አመራሮች ወደ ሶስት አቅጣጫ የተመደበውን ሰራዊት ተከፋፍለው ይዘው ለመጨረሻ ግዳጅ ጉዞ ሆነ፡፡ የክፍለሰራዊቱ አዛዥ ምግበይ ሃይለ የÊJmNT m¶W gù:>N xSkTlÖ በእንግሊዝ ኤምባሲ በኩል ግንፍሌን አልፎ ወደ ትምህርት ሚኒስተር ያመራውን ሃይል ይዘው ገቡ፡፡ ገብረኪዳን የያዘው ሬጄመንት አራት /የእነ ፅዋሃብ አሁን የፓርላማ አባል/፣ /ጥሒሳ፣ ሃይለ ማንጁስ የሬጂመንቷ መሪዎች/ በመገናኛ መስቀል አደባባይ የሚያመራው ዋናውን መንገድ በመውረድ በእስጢፋኖስ ቤተክርስትያን ታጥፈው ወደ ታላቁ ቤተ መንግስትና ውጭጉዳይ ሚኒስተር አመሩ፡፡
ንጋት 11 ሰአት አራት ኪሎ ትምህርት ሚኒስተር የደረሰው የምግበይ ሃይል ከፍተኛ የፒቲ አር ተኩስ ተቃውሞ ገጠመው፡፡ በርካታ ታንኮችም የኢህአዴግ ሰራዊትን ለመግታት ተከራከሩት”” አመራሮቹ በፍጥነት ያኔ የኢሰፓ ፅ/ቤት የነበረው /አሁን ኢህአዴግ ፅ/ቤት/ ጣራ ላይ በመውጣት ሁኔታውን አጠኑት”” እጅግ በርካታ ታንክ ቤተመንግስቱን ሰፍሯል፡፡ እናም ምን ማድረግ ይሻላል ለማለት በወቅቱ ከነበሩት የሃይል መሪዎች ውይይት ተደረገ፡፡ በመጨረሻ ሰአትም ቢሆን ታጋዩ ለመስዋእት ዝግጁ ነው፡፡ ትግልና መስዋእት የማይነጣጠሉ ቢሆኑም እነ ምግበይ እንደአመራር በዛች የመጨረሻ ሰአት የአንድ ታጋይም ቢሆን ህይወት መክፈል በእጅጉ አሳስቧቸዋል፡፡ እናም ማድረግ የነበራቸው አንድ ነገር ነበር፡፡ በእያንዳንዱ ሃይል ስምንት አርፒጂ ስለ ነበር አንድ ላይ በማሰር አንድ ላይ እንዲተኮስ ወሰኑ፡፡ እንደዛም አደረጉ”” በጣም ትክክለኛ ውሳኔ ነበር፡፡ አዲስ አበባ የፈራችው ሰዓት የደረሰ መሰለ”” አዲስ ዓውደ ግንባር ሆነች፡፡ ቤተመንግስት ዙሪያ የተከማቸ ሃይል ማፈግፈግ ጀመረ”” ሃይል መሪዎች ሃይላቸውን ይዘው የመንገዱን ግራና ቀኝ ይዘው በፓርላማና በባሻወልዴ ትይዩ ወደ ቤተ መንግስት ዘለቁ”” በዚህ መሃል ግን የቤተመንግስት ጋራጅ ጋር ሲደርስ አንድ አጠር ያለ ደንዳና ታጋይ እነ ምግበይ ጣራ ላይ ሆነው ሲወድቅ ተመለከቱት”” የሃይል መሪው ማውጫ ነበር፡፡
ጦርነቱ ቀጥሏል፡፡ አዲስ አበባ ጨንቋታል፡፡ በሩን ዘግቶ የተኮራመተው ቤተሰብ ድምፅን ተከትሎ የሚመጣ ጥይት ያለ ይመስል በዝምታ ተውጧል፡፡ አባቶችና እናቶች እንደየእምነታቸው በፀሎት ተጠምደዋል፡፡
የቅልብ ሰራዊቱ ተቃውሞ ከፊት ለፊት ሲሰበር ከጀርባ ሃይለኛ ፍንዳታ ተሰማ፡፡ ተኩስ ሲበረታ አብዛኛው ሃይል ወደዛ እንዲዞር ተደረገ፡፡ ወታደሮቹ የጥይት መጋዘኑን አቃጠሉት፡፡ ታንኮችን አቃጠሉ፡፡ ጦርነቱ የተፋፋመ መሰለ፡፡ ሆኖም 12 ከ30 ሁሉም ነገር በቁጥጥር ላይ ዋለ፡፡
ስለሆነም ከዚህ ዘመቻ ጋር በታያያዘ የሚጠቀስ ውጊያ ከነበረ አልሞት ባይ ተጋዳይ እንዲሉ አለቃውን የሸኘው በቤተመንግስት የነበረው ቅልብ ጦር የፈፀመው እምቢተኝነት ነበረ፡፡ ለ45 ደቂቃ የተካሄደው ውጊያም የአዲስ አበባ ነዋሪ መሬት የተገለበጠች እስኪመስለው ተጨነቀ፡፡ በቦታው የተመደበው የአግአዚ ክፍለ ሰራዊት የተወሰነው ሜካናይዝድ ሰራዊት በቤተመንግስት ዙሪያ ከነበሩት 60 የሚገመቱ ታንኮች 8 በማቃጠል የተቀሩትን በኢህአዴግ እጅ ወደቁ፡፡ በውጊያውም ታጋይ ማውጫንና ሌሎች አምስት ታጋዮች በድምር ስድስት ታጋዮች መስዋእት ሆኑ፡፡ የመጨረሻዋ ጥይት ሰማእታት፡፡ ለ17 አመታት የተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነትም እንዲህ ግንቦት 20 ተቋጨ፡፡ ረፋድ 4 ሰአትም የኢህአዴግ ሰራዊት አዲስን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠራት፡፡
ማጠቃለያ
ለ17 አመታት የተካሄደው የእርስበርስ ጦርነት የሀገሪቱን ተፈጥሯዊና ሰውሰራሽ ሃብትን ያወደመ፣ ከምንም በላይ ደግሞ ይቺን ሃገር ለማበልፀግ የሚችሉ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች፣ከተሜዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ምሁራን ... ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በየከተማው ተረሽነዋል፡፡ በየቀየው በአውሮፕላኖች ተደብድበዋል፡፡ በታንኮች ተጨፍልቀዋል”” በመትረየስ ታጭደዋል፡፡ በመድፍ ከአፈር ጋር ተቀላቅለዋል፡፡
ከግማሽ ሚሊዮን በላይ በደርግ አስገዳጅ ዘመቻ ታጥቀው በየበረሃው ለከንቱ አላማ ሞተዋል፣ አካላቸው ጎድሏል፣ ሊጠግኑ በማይችሉት ህይወታቸው ተመሰቃቅሏል፡፡ በሌላ በኩልም ከትግል ውጪ ሌላ አማራጭ ስላልነበረ የዩኒቨርስቲ ትምህርታቸው፣ የውጪ ሃገር የሞቀ የግል ኑሯቸው፣ ትዳር ከድል በኋላ ብለው ወደ 70 ሺህ የሚሆኑ የኢህዴግ ታጋዮች መስዋእት፣ ከ100 ሺህ በላይ ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ በመስዋእትነታቸውም የሀገሪቱ አስከፊ ጦርነት ተዘግቷል፡፡
እነሆ ኢትዮጵያና ከተማዋ ሌላዋ ሞቃዲሾና ሞኖሮቪያ /ላይበሪያ/ ትሆን ይሆን ተብላ የተሰጋችው ኢትዮጵያ ስጋቶቹን ሁሉ ተሻግራ ለ25 አመታት የሰላም ከተማ ሆነች፡፡ አስገራሚውና በታሪክም ሊከተብ የሚገባው የራሷን ሰላም ከማስጠበቅ አልፋ የሞቃዲሾና የላይበሪያን ሰላም ለማስጠበቅ ወደ ሁለቱም ሀገራት የሰላም አስከባሪ ሰራዊት ልካለች፡፡
በዚህ ላይ ሳይወሰን በተባበሩት መንግስታት ለአለም ሰላም ትልቅ ሚና እየተወጣች ያለች የአለም ሰላም አምባሳደር የሚል መልካም ስም እንድትጎናፀፍ ያስቻላት በነባር የኢህአዴግ ድርጅታዊ ዲስፕሊን የታነፀ ሰራዊት ባለቤት ገንብታለች፡፡ በተባበሩት መንግስታት መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ ሰራዊታቸውን ለአለም ማህበረሰበ ሰላም ካሰማሩ አራት የአለማችን ሃገራት አንዷ ናት፡፡ ዘላለማዊ ክብር ለዚህ ያበቁን የኢህአዴግ ሰማእታት፡፡

1 comment: