Tuesday, 31 May 2016

ፌዴራሊዝም ወዴት እየወሰደን ነው? ለአፍሪካ ሁነኛ አማራጭ “ልዩነትን በአንድነት” መገንባት ( በመቃብሽ ርግበይ) የመጨረሻ ክፍል



አቶ አለም ሃብቱ የተባሉ ሙሁር “የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ዳራ፣ ወቅታዊ ሁኔታና መፃኢ እይታ” በሚል ርእስ በፃፉት መፅሐፍ እንዳስቀመጡት “የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም በአፍሪካ የተለየ ክስተት ያደረጉት አንቀፆች የያዘ በመሆኑ የሙሁራን የጥናት ትኩረት እንዲሆን አድርጎታል” ይላሉ፡፡ ህገ- መንግስቱ ለብሄር ብሄረሰቦች እስከ መገንጠል መብትና ስልጣን መስጠቱና ፓርቲዎች በብሄር ስም እንዲደራጁ እውቅና በመስጠቱ ብዝሃነት ፀጋ ሳይሆን መርገምት ሆኖ በሚታይባት አፍሪካ በእርግጥም አስደንጋጭ ህገመንግስታዊ ውሳኔ ነበር፡፡ እንዲህ ያለ አወቃቀር “ታፍራና ተከብራ ለዘመናት የኖረችን ሃገር” ይበታትናታል ብለው የዩጎዝላቪያና ሶቭዮት ህብረት ማስረጃ የሚያቀርቡ ተቃዋሚዎች በርከት ያሉ ናቸው፡፡
አብዛኞቹ የአፍሪካ ሃገራት የብሄር ብዝሃነት ያላቸው ግን የተከተሉት ስርአተ መንግስት አሃዳዊ ነው፡፡ ፌዴራላዊ አደረጃጀት ይበትነናል የሚል ስጋት ስላላቸው ወይም ቅኝ ገዥዎች ፈጥረውት የሄዱት የውስጥ አስተደደር እንዳለ በመቀበል የቀጠሉ ናቸው፡፡ ይህ እውነታን መካድ ነው፡፡ እውነታውን መካድ ደግሞ የተፈራውን አያስቀርም፡፡ በ1950ዎቹና 60 ዎቹ በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ሃገራዊ ብሄርተኝነት በአፍሪካ አህጉር የተቀጣጠለበት ነበር፡፡ ይህ ሃገራዊ ብሄርተኝነት የቅኝ ግዛት እንዲያበቃ ያደረገ ቢሆንም አፍሪካውያን ከባዕድ ገዥዎች ነፃ ያወጣ እንቅስቃሴ ቢሆንም ዴሞክራሲ አላረጋገጠም፡፡ የነፃነት ትግሉ አምጦ አምጦ ይልቁንስ አምባገነን መሪዎችን ወለደ፡፡ የዚሁ አንድ መልክ የነፃነት ታጋዮች ለብሄራዊ ማንነት የነበራቸው አፋኝ እይታ ነው”” በሃገራዊ ነፃነት ትግል ስም የማህበረሰቦች ማንነት ተጨፍልቋል፡፡ እንዲያውም ለሃገራዊ ምስረታና ግንባታ እንቅፋት ተደርጎ ታይቷል፡፡ ይህ በኢትዮጵያም የከፋ ገፅታ የነበረው ከግማሽ ምዕተ አመት ቀደም ያለ እድሜ የነበረው እንጂ የተለየ አልነበረም፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም በልዩነት ላይ የተመሰረተ አንድነት ነው ማለት ልዩነቶችን የተቀበለ ነገር ግን ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ያምናል ማለት ነው፡፡ በህገ-መንግስቱ ድንጋጌ ግልፅ እንደተደረገው በአገሪቱ የሚኖሩ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች የከፍተኛ ስልጣን ባለቤት እንደመሆናቸው መጠን የፌዴራሉ አስተዳደር የነሱ ተወካይ ነው እንጂ የራሱ የሆነ ስልጣን ያለው አካል አለመሆኑን እንገነዘባለን”” በተመሳሳይ ሁኔታ በክልሎች ደረጃም በአንድ ክልል የሚኖሩ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች የበላይ ስልጣን ባለቤቶች እንደመሆናቸው የክልሉ አስተዳደር የክልሉ ህዝቦች ተወካይ እንጂ የራሱ የሆነ ልዩ ስልጣን ያለው አካል አይሆንም፡፡
በመሆኑም ከአሃዳዊ መንግስት በተለየ በፌዴራል መንግስትና በክልል መንግስታት መካከል ህገ-መንግስታዊ ዋስትና ያለው የስልጣን ክፍፍል ነው ያላቸው፡፡ ስለሆነም ከአሃዳዊ መንግስት በተለየ የክልል መንግስት ያለው ህጋዊ ህልውና በፌዴራል መንግስቱ በጎ ፍቃድ ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ ይህ ማለት ፌዴራል መንግስት በተናጠል ለክልል የተሰጠ ስልጣን በአዋጅ ሊሽረው፣ ሊያሰፋው ወይም ሊያጠበው አይችልም፡፡
በመሆኑም የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም በአንድ በኩል በአንድ ማእከል ተከማችቶ የቆየውን ስልጣን /the centralization power/ ሲያስቀር በሌላ ኩል ከሃገሪቱ የፖለቲካ ስልጣን ተገለው የነበሩ /marginalization/ ህዝቦች ህጋዊ ተሳትፎ መብት እንዲኖራቸው ያደረገ ነው”” በመሆኑም ብሄር ብሄረሰቦች ማንነታቸው መታወቁና ራሳቸው ማስተዳደራቸው አንድነት ያላላል የሚለው እንቶፈንቶ ኢሳይንሳዊ መሆኑ በኢትዮጵያ ተረጋግጧል፡፡ ለዚህ አንዳንድ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል፤
1. በ1980ዎቹ የፌዴራል ስርአቱ አወቃቀር ሰዎች ሃገራዊ ማንነታቸውን አደብዝዞ ብሄራዊ ማንነታቸው ላይ እንዲያተኩሩ በማድረግ ሀገሪቱን ይበታትናታል፡፡ ክፉ አይምጣ እንጂ ዳር ድንበሯን የሚከላከልላት አይኖርም የሚል ፀረ ፌዴራሊዝም አስተሳሰቦች እጅግ ገዝፈው የወጡበት ሁኔታ ነበር የፈጠረው”” ነገር ግን የኤርትራ መንግስት ወረራ በ1991 ሲከሰት የታየው የኢትዮጵያ ህዝቦች ቁርጠኛና መነሳሳት ለፀረ ፌዴራሊዝም አራማጆች ሃይለኛ ምት ያሳረፈ ነበር፡፡ በወቅቱ ከኦነግ በስተቀር ጦርነቱ አያገባኝም ያለ ሃይል አልነበረም፡፡ እናም ጨቅላው ፌዴራሊዝም መጀመሪያ ፈተናው አለፈ፡፡ የኦጋዴኖች /ኢትዮጵያ ሶማሌ/ ከየትኛም ብሄር ብሄረሰብ ቀድመው ፍየሎቻቸውን ጭነው በሰሜን ግንባር መገኘታቸው ከማንኛውም በላይ የአዲሱ ስርአት ቱሩፋት መገለጫ ነበር የሚለው ብዙ ምሁራን በአስረጅነት የሚያቀርቡት ታሪካዊ እውነት ነው፡፡
የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ያልተሳተፈበት ኢትዮጵያዊ አለ ወይ የለም? ስለሆነም የሀገር ሉአላዊነትን መከላከል በዘመነ ፌዴራሊዝም የታየ አዲስ ክስተት ነው ባይባልም ለሀገር ቀናኢነት ህዝባዊ ማእበል ሆኖ ወጥቶ ያየነው ግን በዘመነ ፌዴራሊዝም ነው፡፡ በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት የታጠቀ ሃይል ሳይሆን ህዝብ እንደህዝብ ነው የጎረፈው፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ቀደም ሲል የተጠቀሰው የኢትዮጵያ ሶማሌ ዜጎቻችን ከኦጋዴን ጫፍ ከማንም ቀድመው በዛላንበሳ ግንባር ፍየሎቻቸውን ጭነው መገኘታቸው በማንም የማይዘነጋ ልብ የሚነካ ክስተት ነበር፡፡ እንግዲህ እነዚህ ወገኖች በአሃዳዊ ጨቋኝ ስርአት ተማረው በሽግግር መንግስቱ ለፕሬዝዳንት መለስ ዜናዊ “እባክዎ ይህ እንመሰርተዋለን የምትሉት መንግስት ከትናንቶቹ የተሻለ አይሆንምና ገና ሳይጠናከር በጥዋቱ መውጣት ይሻለናል” ያሉ ሰዎች ናቸው፡፡
2. ኢትዮጵያውያን በዚህ ትውልድ ያከበሩትና የጋራ እሴታቸው መሆኑ ለአለም ያሳወቁት አንድ ክስተት የኢትዮጵያ ምዕተ አመት /ሚሊኒየም/ ነው፡፡ በዚህ በአንድ ሺ አመት ከብዙ ትውልዶች በኋላ የሚመጣው ሃገራት የትልቅነታቸው መገለጫ አድርገው የሚገልፁት ሚሊኒየም በኢትዮጵያ የሚገኙ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በአንድ ድምፅ ‹‹ታላቅም ነበርን ታላቅም እንሆናለን›› በሚል የተባበረ የአንድነታቸውን ቃል አሰምተው በትልቅ ንቅናቄና መነሳሳት አክብረውት ታዝበናል፡፡ ይህ በየትኛው መመዘኛ ሀገራዊ አንድነቱ የደበዘዘ ህብረተሰብ ሊያደርገው የሚችል አይደለም፡፡ በዚህ በአል የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ከድህነትና ከኋላቀርነት የመውጣት እጣፈንታቸው የተሳሰረ መሆኑ በግልፅ ያሰመሩበትና እጅ ለእጅ ተያይዘው ወደ ታላቅነት ማማ ለመውጣት መነሳታቸው ለአለም ህዝብም ግልፅ መልእክት ያስተላለፉበት የዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም እሴት ነው፡፡
3. ሌላ የዚህን ዘመን ትልቅ ክስተትም መጥቀስ ይቻላል፡፡ የህዳሴ ግድብ፡፡ የታላቁ የህዳሴ ግድብ እየተገነባ ያለው በማን ነው የሚለውን መመልከት በቂ ነው፡፡ ግድቡ እየተገነባ ያለው በመልክዓምድር ከሆነ በሀገሪቱ ምዕራብ ጫፍ ነው፡፡ ነገር ግን በምስራቅ ጫፍ ላሉት ኢትዮጵያ ሱማሌዎች፣ በሰሜን ጫፍ ላሉ ኢሮብና ኩናማዎች በደቡብ ጫፍ ላሉ ሀመሮች ወዘተ ... ግድቡ እጅግ ቅርባቸው ነው፡፡ የቦታ ርቀት የማይገድበው የእኔነት ስነ ልቦናዊ ትስስር አለው፡፡ ይህ እየሆነ ያለው እንግዲህ በዘመነ ፌዴራሊዝም ነው፡፡
4. የሀገሪቱ ታላቁ ባለራዕይ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ አለም ሲለዩ የታየው የህዝቡ ታላቅ ሃዘን የፌዴራል ስርአቱ ያመጣው ጤናማ አስተሳሰብ ነው”” የኢትዮጵያ ህዝቦች ከጫፍ ጫፍ በሃዘን የተመቱት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የግል ስብእና ብቻ አይደለም፡፡ ከበስተጀርባ ያለው እውነታ ለመጀመሪያ ግዜ የብሄር ብሄረሰቦች እውቅና የሰጠ ስርአት መሪ በመሆናቸው እንጂ”” በወቅቱ በኢትዮጵያውያን የታየው ሐዘንና ቁጭት የትምክህተኞችና ጠባቦች ወገብ የቀነጠሰ ክስተት ነበር፡፡ ለዘለዓለምም ታሪክ መዝግቦት ይናራል፡፡ ኢትዮጵያውያን አባቶች፣ እናቶችና ወጣቶች “መለስ ሱማሌ ነው፣ መለስ ኦሮሞ ነው፣ መለስ አማራ ነው፣ መለስ ጌዲኦ ነው” ... እያሉ ሲገልጿቸው አድምጠናል፡፡
5. የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በርካቶቹ ነባር የአመት አቆጣጠር እንዳላቸው ይታወቃል”” እነዚህ ክብረ በአላት በታላቅ ድምቀት እያከበሯቸው ያሉ በዘመነ ፌዴራሊዝም ነው”” የሲዳማ ጨምበላላ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህ የጨምበላላ በአል ለዘመናት ታፍኖ የነበረ የሀገሪቱ አንድ የጋራ ውበታችንና እሴታችን ነው”” ሲዳማዎች ደግሞ የማንነታቸው መገለጫ በመሆኑ ሞቅ ደመቅ አድርገው ያከብሩታል፡፡ የኦሮሞ አባገዳ ስርአትና የእሬቻ በአልም እንደገና ህይወት የዘሩት በዚህ ዘመን ነው፡፡ ይህንን ሲያዩ የሚበረግጉ አሉ፡፡ የፌዴራሊዝም ስርአት አፍቃሪዎች ግን የእሬቻንም ሆነ የጨምበላላ በአል በድምቀት መከበር የፌዴራላዊ ስርአቱ ጤናማ ጉዞ አድረገው ይቆጥሩታል፡፡ ነገር ግን ብሄር ብሄረሰቦች የነባር ዘመን አቆጣጠራቸው እያከበሩ ባሉበት ዘመነ ፌዴራሊዝም ደግሞ በጋራ የኢትዮጵያ ሚሊኒየምን በጋራ እጅግ በሚያምርና ለኢትዮጵያ ህዳሴ ቆርጠው መነሳታቸውን በማወጅ ጭምር አክበረውታል፡፡
በመሆኑም ባለፉት 25 አመታት የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች የራሳቸው የብሄር ማንነት በመገንባትና በሃገራዊ ማነነት ግንባታ ምንም ተቃርኖ እንደሌላችው አሳይተዋል፣ አይተዋል”” አካባቢያቸውን ያለማሉ፡፡ ሀገራቸውንም ያለማሉ፡፡ ነባር ባህላዊ በአላቸውንም ያከብራሉ””
የኢትዮጵያ ሚሊኒየምም በጋራ ያደምቃሉ”” ማንነታቸውን ይጠብቃሉ፣ ሀገራዊ ሉአላዊነታቸውም መስዋእት ይሆናሉ፣ በአካባቢያዊ ጉዳያቸውም ላይ ይወስናሉ፣ ለሀገራዊ አንድነታቸው ደግሞ ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ፡፡ ይህ ልዩነትን ያከበረ አንድነት በመገንባታቸው የመበታተን አደጋን በእጅጉ አዳክመውታል፡፡ ጠንካራ ሀገራዊ አንድነታቸው አፍሪካውያን የሚጓጉለት ሆኗል፡፡ ውጥረትና ድህነትን በበዛበት የአፍሪካ ቀንድ አይን ማረፊያ የሆነች የሰላም ምድር፣ የልማትና እድገት ቀንዴል የሆነች ሀገር እየገነቡ ነው፡፡ እናም ህብረብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም ወዴት እየወሰደን ነው ለሚለው ጥያቄ በግንቦት 20 25ኛው የድል ቀን ሆነን እርግጠኛ የሆነ መልስ መስጠት እንችላለን፡፡ ህብረብሄራዊ ዴሞክራሲያዊ ፌዴራሊዝም ወደ ታላቅነት ማማ እያስወነጨፈን ያለ ባቡር ነው፡፡

No comments:

Post a Comment