በ1986 ዓ.ም የተነደፈው የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ በሀገራችን በነበረው የትምህርት ስርአት
ውስጥ ማነቆ የሆነውን ክፍተት መቅረፍ ችሏል፡፡ ፖሊሲው በበርካታ ስርአት ውስጥ የዜጎችን የትምህርት ጥማትና የሀገሪቱን ቁልፍ ችግር
በመፍታት ይዞት የመጣው ውጤት በቃላት ብቻ የሚገለፅ አላደረገውም፡፡ በመሰረታዊነት የትምህርት ተደራሽነትን፣ ፍትሃዊነትን፣ ጥራትን
ተገቢነትን፣ የትምህርት አመራርና የአስተዳደር ችግሮችን ስር ነቀል በሆነ መልኩ በማቃለል ምቹ መደላድሎችን ፈጥሯል፡፡ ፖሊሲው መተግበር
ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባሳለፍናቸው 22 ዓመታት ውስጥ ከላይ የተጠቀሱትን መሰረታዊ ነጥቦች በሚታይና በሚለካ መልኩ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
በውጤቱም ዛሬ ሀገራችን ለደረሰችበት የእድገት ደረጃ ቁልፉ አጋዥ መሆን ችሏል፡፡
በቅርብ አመታትም በተቀመጡት የስትራቴጂክ እቅዶች የትምህርት ዘርፍ ዋነኛ ትኩረት ተደርጎበታል፡፡
በመሆኑም በአንደኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን የተመዘገቡትን ውጤትና ተግዳሮት በጥልቀት በማጤን ለሁለተኛው የእቅድ
ዘመን በመነሻነት በእቅድ ተይዞ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡ በተለይም ሀገራችን ለነደፈችው የትራንስፎርሜሽን እቅድና የኢንዱስትሪ እድገት
ቀጣይነት ለማረጋገጥ እንዲቻል ወሳኝና ቁልፍ ከሆኑ ስራዎች ውስጥ አንዱ የሰው ሃይል ልማት ነው፡፡ የሰው ሃይል ሲባል ደግሞ ከ80
በመቶ በላይ የሚይዘው የዝቅተኛ እና መካከለኛ ባለሙያተኛ በብቃት በብዛት ማምረት ነው፡፡ በመሆኑም በትምህርትና ስልጠና ዘርፍ የሽግግሩ
መሰረት በሆነው የቴክኖሎጂ እውቀት መጎልበት ልዩ ትኩረት አግኝቶ እየተሰራበት ይገኛል፡፡ ይህንን ተግባር ለማፋጠንና በተቀመጠለት
ተልዕኮ መሰረት የኢንዱስትሪውን ማነቆ በመፍታት ሀላፊነት ከተጣለባቸው ተቋማት አንዱ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ነው፡፡
ዘርፉ በተለይም በከተማችን ህብረተሰቡንና ኢንዱስትሪውን በማገናኘት ውጤት ተኮር የስልጠና
ሙያ ስልት በመዘርጋት የቴክኖሎጂ ሽግግር ማዕከል ለመሆን በቅቷል፡፡ አስተዳደሩም ለተቋሙ በየደረጃው የማጠናከርና የማስፋት ስራን
አበክሮ እየተወጣም ይገኛል፡፡ በመንግስት 10 ኮሌጆችና 22 መለስተኛ ተቋማት በግሉ ዘርፉ ደግሞ 69 ኮሌጆችና 282 መለስተኛ
ተቋማት በመከፈታቸው ከ100 ሺህ በላይ ሰልጣኞች በተለያዩ ደረጃዎች የሙያ ስልጠና በመውሰድ የሙያ ባለቤት ሆነዋል፡፡
በተለይም የመንግስት የስልጠና ኮሌጆችና ማዕከላቱ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች በምርት
ጥራትና ምርታማነታቸው በገበያ ተወዳዳሪ ሆነው ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለሚደረገው ሽግግር መሰረት እንዲሆኑ ለማስቻል በአራት
የድጋፍ ማዕቀፎች የካይዘን አቅም ግንባታ፣ የስራ ፈጠራ አቅም ግንባታ፣ የቴክኒካል ክህሎት አቅም ግንባታ እና የቴክኖሎጂ አቅም
ግንባታ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽ አገልግሎት ፕሮግራም በመዘርጋት ወሳኝ ስራ እየተሰራ ነው፡፡
በእነዚህ ተቋማት በርካታ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ ከእሴት ሰንሰለት ተነስተው
አዳዲስ ፈጠራዎች በአሰልጣኞቹ እየተሰሩ ነው፡፡ የአነስተኛ ተቋማትም ወደ ምርት እየቀየሩዋቸው ይገኛሉ፡፡
ለውጤቱ መገኘት አብይ ድርሻ ካበረከቱት ተቋማት ውስጥ በኮሌጅ ደረጃ ለበርካታ ዜጎች ስልጠና
እየሰጠ ወዳለው ከፍተኛ 4 ቴክኒክና ሙያ አምርተን ወደ ተግባር የተለወጠ የቴክኖሎጂ ኩረጃን ቀንጭበን ለአንባቢያን በሚያመች መልኩ
ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ ተቋሙ በልደታ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ኮካ ኮላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም በርካቶች
ሰልጥነው አብላጫ ቁጥር ያላቸው የራሳቸውን ስራ ፈጥረው ህይወታቸውን ቀይረውበታል፡፡ የተቀሩትም በተለያዩ ኢንዱስትሪዎችና የግል
ተቋማት በመቀጠር እውቀታቸውን ወደ ተግባር ለውጠዋል፡፡
አሁን ባለንበት የእድገት ጉዞ ከተለያዩ ተቋማት የተመረቱ ቴክኖሎጂዎችን የማላመድ፣ ለደንበኛ
የማስተላለፍ ስራና በርካታ አንቀሳቃሾችን ማሰልጠን ተችሏል፡፡ በዚህ ረገድ ሰፊ ህዝባዊ መሰረት ያላቸው የጥቃቅንና አነስተኛ አንቀሳቃሾች
ሀይሎች ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ሽግግር ከሚሹት ውስጥ ይካተታሉ”” ከፍላጎት
ባሻገርም በምርት እና አገልግሎት አሰጣጥ ረገድም ከፍተኛ የሆነ ክፍተት አለባቸው፡፡ ታዲያ ይህንን ማነቆ ብሎም ፍላጎትን መሰረት
አድርጎ ምላሽ በመስጠት የከፍተኛ 4 ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ በኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ዘርፍ ውስጥ የፈጠራ እና የሂሳብ አያያዝ ባለሙያ
ወጣት አድማሱ በቀለ አንድ ነገር እንካችሁ ብሎናል፡፡ መቶ በመቶ በመኮረጅ ተግባራዊ ያደረገውን ቴክኖሎጂም ለግንቦት 20 መታሰቢያነት
ማበርከቱትን ሲገልፅ ደስታው ወደር አልነበረውም፡፡
ወጣቱ ቴክኖሎጂውን በመቅዳት ውጤታማ መሆን የቻለበት መሳሪያ ወተትን ወደ እርጎነት በ3 ሰዓት የሚቀይር መሳሪያ ነው፡፡
መነሻውም ሁለት ምክንያቶች እንደሆኑ ያስቀምጣል፡፡ አንደኛው በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ሳይንስ ትምህርቱን ሲከታተል ወተትን
በባህላዊ መንገድ መስራቱ ኋላቀር ከመሆኑም አልፎ ዩኒቨርሲቲው ዘመናዊ መሳሪያ ማጣቱ ትልቅ ቁጭት ፈጥሮበት እንደነበርና በሁለተኛነት
ደግሞ የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ኤጀንሲ የተሟላ ስልጠና ለመስጠት በ19 ዘርፎች የእሴት ሰንሰለት ጥናት ማሰራት መፈለጉ ሌላ
ምክንያት እንደ ሆነው ይገልፃል፡፡ በመሆኑም ከሁለት የከተማ ግብርና እሴት ሰንሰለት ማለትም ከዶሮ እርባታ እና ከብት እርባታ ሁለተኛውን
በመምረጥ ከባልደረባው ጋር ጥናት አደረጉ፡፡ በጥናቱም በወተት ዙሪያ የሚያጋጥሙ የምርት ውስንነቶች እና ብክነቶች አካተዋል፡፡ በጥናቱም
ወተትንና የወተት ተዋፅኦ በተለያየ መልኩ ከሚያመርቱ የግብርና ተዋፅኦ ኢንዱስትሪ እንዲሁም የጥቃቅንና አነስታኛ አንቀሳቃሾች ተካተዋል፡፡
በጥናቱ የእውቀት፣ የክህሎትና የስልጠና ክፍተቶች በስፋት መኖሩን አረጋገጡ፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ ወተትን በተለያየ
መልኩ የሚያቀነባብር መሳሪያ ወይም ቴክኖሎጂ አለመኖሩ የችግሩ ቁንጮ ነበር፡፡ ታዲያ እነዚህን ሁለት ምክንያቶች ወደ እውነታ የለወጠለት
መልካም አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘው የኢትዮeያ ስጋና
ወተት ኢንስቲትዮት የአንድ ወር ስልጠና ማግኘቱ ቁጭቱን ወደ እውነታ ለመቀየር በር ከፈተለት፡፡ በሰለጠነበት ተቋም ወተትን ወደ
እርጎ የሚቀይር መሳሪያ ከውጭ ተገዝቶ የገባ ነበር፡፡ ነገር ግን አድማሱ የመሳሪያውን እያንዳንዱ ክፍል በማጤን ሊሰራው እንደሚችል
ወጥኖ ወደ መደበኛ ስራው ተመለሰ፡፡
ቀጥሎም የእሴት ጥናቱን ውጤት እና መፍትሄውን ያካተተ እቅድ ለተቋሙ አቅርቦ ፀደቀለት፡፡ ተቋሙ አዎንታውን የሰጠበት
እለት ለአድማሱ ድርብ ሃላፊትን የተጣለበት በመሆኑ ሀሳቡን በተግባር ለመቀየር ሌት ተቀን በመስራት ተጠመደ፡፡ ከሚያሰለጥንበት ተቋምም
የተለያዩ ግብአቶችን ማለትም ከአልሙኒየም የኤሌክትሪክመንገድ ቁርጥራጭ ብረቶች፣ መስታወትና ለኩረጃና የሚጠቅሙ ግብአቶችን በግዥም
በማሟላት ተጠቅሞ በሶስት ሰአት ውስጥ ወተትን ወደ እርጎነት የሚቀይር መሳሪያን ሰራ፡፡
ማሽኑ በአንድ ጊዜ 20 ሊትር ወተት ማርጋት
የሚችል ባለ አራት ክፍል ሲሆን መስሪያው የሙቀት እና የቆይታ ጊዜውን በዲጂታል መሳሪያ በመቆጣጠር ካለሰው ንክኪ አርግቶ ያደርሳል”” ቆይታው ለሶስት ሰአት ሲሆን የሙቀት መጠኑ
ደግሞ 45 ዲግሪ ሴሊሼስ እንደሆነ ወጣት አድማሱ ገልፆልናል፡፡ መሳሪያው ከውጭ ሀገር ከሚገባው የሚለይበትንም ሲገልፅ የሙቀት መጠኑን
የሚያሳይና አንዴ አስተካክለው ከሰጡት ሳያወላውል ሙቀቱን ሲጨምር እየቀነሰ ሲቀንስ እየጨመረ የሚሰራ መሆኑ ነው፡፡
ከውጭ የሚመጣው ግን ይላል አንዴ የሰጡትን
ሳይለቅ እስከመጨረሻው የኤሌክትሪክ ፍጆታውን ከፍ ያደርገዋል፡፡ ሌላው የሙቀት መጠኑን የሚያሳይ መሳሪያ ነው፡፡ የተሰጠውን ትዕዛዝ
በአግባቡ ፈፅሞ ሲጨርስ ድምፅ በማሰማት መልዕክትም ያስተላልፋል፡፡
ወተቱን ወደ እርጎ ለመቀየር በመጀመሪያ
ደረጃ የታለበውን ወተት በ95 ዲግሪ ሴሊሼስ ሙቀት ማፍላት አስፈላጊ መሆኑንና በወተት ውስጥ ያለው ፋቶጂኒክ ባክቴሪያ
/Fatojenik Backteria/ ማስወገድ እንደሚገባም ወጣቱ ነግሮናል፡፡
“ይህ በተፈጥሮ በሽታ አምጪ ባክቴሪያ
ለማስወገድ እና መካከለኛ ሙቀት በመቋቋም ወተትን ወደ እርጎ ለመቀየር የሚረዳውን ቴርሞፈሊክ /Termofilic
Backteria/ የተሰኘ ባክቴሪያ በቀላሉ መራባት እንዲችል ማድረግም ያስፈልጋል፡፡” የሚለው ወጣት አድማሱ ይህ ብቻ አይደለም
በ95 ዲግሪ የፈላውን ወተትም ተመልሶ ወደ 45 ዲግሪ መቀዝቀዝ አለበት ይለናል፡፡
ሌላው ቴክኖሎጂው እርጎን በማር፣ በእንጆሪ፣
በአናናስና በተለያዩ ጣዕም ለማዘጋጀት ምቹ ሁኔታንም አካቷል፡፡ አሰልጣኙ በቅርቡ በከተማ ደረጃ በተዘጋጀ የቴክኒክና ሙያ ሳምንት
መሳሪያውን አቅርቦ አንድ አስተያየት አሻሽሎበታል፡፡ ይህም የሀይል መቆራረጥን በምን መልክ መቅረፍ እንደቻለ ጥያቄ ቀርቦለት ነበር”” በምላሹም ጀኔሬተር መጠቀም እንደሚቻል
ምላሽ ሰጠ፡፡ ሆኖም ጥያቄውን ያቀረቡለት የኤሌክትሪካል ባለሙያዎች የሶላር ሀይል አማራጭ ማድረግ እንደሚችል ሲነግሩት ወዲያው ሀሳቡን
ቀየረ፡፡ የፀሀይ ሀይልን ሰብስቦ ወደ ኤሌክትሪክ ጉልበት የሚቀይር መስሪያ /Conferter/ በመግጠም ለችግሩ እልባት አስቀምጧል፡፡
አድማሱ ከእሴት ሰንሰለት በመነሳት የስራውን
የቅጅ መሳሪያ ለመስራት የተቋሙ ድጋፍ አልተለየውም፡፡ ማሽኑ 15 ሺህ 600 ብር የፈጀ ሲሆን ሙሉ ወጭውንም የሸፈነለት ከፍተኛ
4 ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ነው፡፡ በስራው ደስተኛ የሆነው ወጣት ስራውን ለኢትዮeያ አዕምሯዊ ንብረት በማመልከት እውቅና ለማግኘት በሂደት ላይ ነው፡፡ የከተማ
አስተዳደሩም በግንቦት አጋማሽ የሙሉ እውቅና ፕሮግራም ላይ ሽልማት ሊሰጠው እንደሆነም ነግሮናል”” ነገር ግን በዚህ ብቻ ሳያበቃ እርሱም
ሆነ የሚሰራበት ተቋም የግንቦት 20 ፍሬ መሆናቸውን ተገንዝቦ የኮረጆውን የቴክኖሎጂ ውጤት ለመታሰብያነት ለግንቦት 20 አበርክቷል፡፡
የተቋሙ ምክትል ዲን አቶ ፍሬው አመነም ኮሌጁ ከዚህ ቀደም ችግር ፈቺ የሆኑ ግኝቶች ለህብረተሰቡ መተላለፋቸውን ይናገራሉ”” ታዲያ ይህንን ተከትሎ እንደ አድማሱ አዲስ
ነገር ይዘው ብቅ ላሉ ወጣቶች ልዩ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ገልፀዋል፡፡ የቅጂ ስራውንም ለሁለት ጥቃቅንና አንስተኛ አንቀሳቃሾች ለማስተላለፍ
ስልጠናም ሰጥቶ ቴክኖሎጂው ለታሰበለት አላማና ለህብረተሰቡ በቀላል ገንዘብ እንዲደርስ ድጋፍና ክትትል እያደረገላቸው መሆኑን አጫውቶናል”” ማህበራቱ በቅርቡም ወደ ምርት ለመግባት
ዝግጅት አጠናቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ቴክኒክና ሙያ ኤጀንሲ በዘንድሮው
አመት ብቻ 171 ቴክኖሎጂዎችን ከንድፈ ሀሳብ አንስቶ የተገጣጠሙ መሳሪያዎችን ለተጠቃሚዎች አስተላልፏል፡፡ በኤጄንሲው የቴክኖሎጂ
ልማት ባለሙያ አቶ በላይ ከፍአለ ከ27 ተቋማት በኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን መርሀ ግብር የተቀመጠውን አቅጣጫ ለማሳካት በሚደረገው
ጥረት ሀገሪቱ እስከ 2017 ዓ.ም ቴክኖሎጂን መቅዳት በሚለው ዘርፍ የአድማሱ የቅጁ ስራ ውጤታማነት የተመሰከረለት መሆኑን ይናገራሉ፡፡
በቀጣይም ኤጀንሲው በተመሳሳይ ስራ ላይ
ለተሰማሩ ማህበራት ድጋፍ በመስጠት ተቋሙ እርጎ ማርጊያውን እያመረት እንዲያስረክብ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ላይ ናቸው፡፡ እያስገነባቸው
ከሚገኙ 11 ደረጃቸውን የጠበቁ ሰርቶ ማሳያ /work shop/ ግንባታዎች ከፍተኛ 4 የቆዳና ብረታ ብረት ሰርቶ ማሳያ ይገኙበታል፡፡
አሁን ላይ ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ስራ ለመግባት ለምርቃት ተሰናድተዋልም፡፡ በመጪው ጊዜም የአድማሱን የእርጎ ማርጊያ መሳሪያ በዚሁ
ተቋም አምርቶ ለማሰራጨትም መታሰቡም ሌላኛው ስራው ወደ መሬት መውረዱን የሚያመላክት ነገር ነው፡፡
አዎ ዛሬ ሀገራችን ያለችበትን ችግር ቆሞ
የሚመለከት ትውልድ የለም፡፡ ወደፊትም እንዳይኖር በትጋት እየተሰራ ነው”” ለትጋቱ መሳያ ከሆኑት መካከል አድማሱም ስርአቱን ለዘረጋው ግንቦት 20 ስራውን ዘክሯል፡፡ አሁን እርሱም ትውልድ
ተምሮ ሰርቶ ራሱን ከመለወጥ አልፎ የሀገሩን ችግር በመቅረፍ ላለበት ስርአት አለኝታነቱን ሲያሳይ ደስታው እጥፍ ድርብ ነው፡፡ እኛም
ቴክኖሎጂን በመቅዳት ለግንቦት ያበረከተ ፈርጥ ብለነዋል፡፡
No comments:
Post a Comment