Tuesday, 31 May 2016

ለአምራች ኢንዱስትሪው ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ ያለ ስርዓት



የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ራሱን ችሎ ከተቋቋመ ወዲህ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪውን ከከፍተኛ ኢንዱስትሪው ጋር ለማስተሳሰር ዘርፈ ብዙ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል፡፡ በተለይ መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪው ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራት ባለሀብቶች በዘርፉ ያለባቸውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል አሰራርና አደረጃጀት ዘርግቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ እኛም የቢሮው አቅጣጫና ሌሎች ተግባራቱን እንዴት ተግባራዊ እያደረገ እንደሚገኝ ከቢሮው ሀላፊ ከአቶ ጀማል ረዲ ጋር ቆይታ አድርገን በዚህ መልኩ ይዘንላችሁ ቀርበናል፡፡ መልካም ቆይታ፡፡
ህዳሴ፡- የከተማችን የኢንዱስትሪ ልማት አቅጣጫ በምን አይነት መንገድ እየተከናወነ ይገኛል?
አቶ ጀማል፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን የኢንዱስትሪ ልማት አቅጣጫን ስናይ እንደአገርም እንደከተማም አቅጣጫው በዘርፉ ጉልበትን በስፋት የሚጠቀሙ፣ በምርታማነት በጥራትና በዋጋ ተወዳዳሪ የሆነ ቀላልና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋትና በቀላሉ ምርታማነትን ለማሳደግ ነው፡፡
ኢንዱስትሪ ሲቋቋም መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪና ከፍተኛውን ለማስተሳሰር ሲሆን በአብዛኛው የትኩረት አቅጣጫው አነስተኛና መካከለኛ ሆኖ እያለ አነስተኛው ከጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ቢሮ ጋር በመሆኑ በአሰራር ላይና ለኢንዱስትሪው መሰረት ከማንጠፍ አንፃር ሰፊ ክፍተት ነበረበት፡፡ ምክንያቱም የአነስተኛ ኢንዱስትሪ ቅኝት ለኢንዱስትሪው ግብአት ከመሆን ይልቅ ስራ እድል ፈጠራ ላይ ትኩረት ያደረገ በመሆኑ ነው፡፡
የስራ እድል እየፈጠሩ ለኢንዱስትሪው መሰረት ከመጣል አንፃር የራሱ የሆኑ ጉድለቶች ስላሉበት አደረጃጀቱንና የህግ ማዕቀፎቹን እያየን እያጠናን ነው፡፡
የግል ባለሀብቶችም በመካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪ መሰማራት ሲፈልጉ የሚያበረታታ የህግ ማዕቀፍ ተቀምጧል”” እንደሚታወቀው በኢንተርፕራይዝ በኩልም ይምጡ በግልም በመካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪ መሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶች መሬት በምደባ ነው የሚያገኙት፡፡ ከዚህ ባሻገርም እንደ አቅጣጫ የተቀመጠው መሰረተ ልማት የማሟላት ሀላፊነት የመንግስት ነው፡፡ መሰረተ ልማት ስንል መብራት፣ ወሃ፣ ቴሌኮም፣ መንገድ ማለታችን ነው፡፡ በዚህ ሂደት በኛ በኩል እስካሁን የራሱ የሆኑ ጉድለቶች ነበሩብን፡፡ በምደባ የተገኘን መሬት አጠቃቀም ላይና ከመሬት አቅርቦቱም አንፃር ሰፊ ክፍተት ያለ ሲሆን የቀረበውንም መሬት ለታሰበለት አላማ ከማዋል አንፃር በባለሀብቱም ዘንድ ሰፊ ክፍተት አለ፡፡ እኛም ተከታትለን ለታለመለት አላማ ውሏል አልዋለም ብለን ክትትልና ድጋፍ ከማድረግ አንፃር ጉድለቶች ነበሩብን፡፡ ይህንን የሚያስተካክል የክላስተር ልማት አደረጃጀት ዘርግተን ለውጥ ለማምጣት ጥረት እያደረግን ነው፡፡
ህዳሴ፡- አሁን ባለው ሂደት የክላስተር ልማት አደረጃጀቱ ምን ይመስላል?
አቶ ጀማል፡- መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪው ላይ ትኩረት አድርገን ስንሰራ ያለባቸውን የካፒታል፣ የቦታ እጥረት ለመቅረፍ በክላስተር ልማት ተደራጅተው እንዲሄዱ የማድረግ ሰፊ ስራ እየሰራን ነው፡፡ ለዚህም ሲባል ከዚህ ቀደም ለመካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪ የሚሆኑ በርካታ ህንፃዎች ተገንብተዋል፡፡ ይሁን እንጂ አደረጃጀቱ ስራ እድል ፈጠራ ላይ ያተኮረ ስለነበር በሚፈለገው ልክ ለኢንዱስትሪው መሰረት እየጣለ እንዲሄድ አላደረገውም፡፡ 

ስለዚህ የክላስተር ልማታችንን እንደገና እንድናጠና አድርጎናል”” የክላስተር ልማቱ አንደኛ በየንኡስ ዘርፉ በግብአትም ጭምር እንዲመጋገቡ ተደርጎ ባለመሰራታቸው ያሉት ኢንዱስትሪዎች አነስተኛው ከመካከለኛው መካከለኛው ከከፍተኛው፣ እዛው ደግሞ አነስተኛው ከአነስተኛው ኢንዱስትሪ የሚተሳሰሩበትን ሁኔታ የፈጠረ አልነበረም፡፡
በዚህ ምክንያትም የክላስተር ልማቱ እርስ በርሱ የተሳሰረ ባለመሆኑ በግብአት ትስስርና በግብይት ስርዓቱ ላይ አሉታዊ ጫና ፈጥሯል፡፡ ለዚህም ነው አሁን ላይ አደረጃጀቱን እንፈጥረዋለን ብለን እየታገለን ያለነው፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታትና ክላስተር ልማቱ በገበያ፣ በግብይትና በግብአት ትስስር በጋራ ተሳስረው እንዲሰሩ የማምረቻ ማዕከላቱን ክላስተር በሆነ መንገድ እየገነባን የምንገኘው፡፡ ይህን ተቋም ደግሞ በንግድ አስተሳሰብ የሚያለማ፣ የሚያስዳድር፣ እያከራየ ነገ አቅማቸውን የሚገነባ ተቋም እንዲሆን ከወዲሁ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ አደረጃጀቱም ተጀምሯል እየተጠና ነው ያለው፡፡ ጥናቱም ሲጠናቀቅ ለከተማው ምክር ቤት ቀርቦ ከፀደቀ በኋላ ወደ ስራ ይገባል፡፡
ህዳሴ፡- ከዚህ በፊት በከተማችን ለኢንዱስትሪ ልማቱ ተብለው የተገነቡ የማምረቻ ህንፃዎች ምን እየሰሩ ነው?
አቶ ጀማል፡- በከተማችን ከአሁን ቀደም ከ130 በላይ የማምረቻ ህንፃዎች ተገንብተዋል፡፡ እነዚህ የማምረቻ ህንፃዎች በወቅቱ ትልቅ የስራ እድል የፈጠርንባቸው ሲሆን አሁን ላይ ለተሸጋገሩትም ላልተሸጋገሩትም ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ያበረከቱት ሚና ቀላል አይደለም፡፡ ነገር ግን እነዚህ ህንፃዎች መስጠት በሚችሉት ልክ አገልግሎት ሰጥተዋል ወይ ሲባል በርካታ ጉድለቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡ በክላስተር አስተሳሰብ የተገነቡ አይደሉም፣ በግብይትም፣ በግብአትም፣ በመሳሪያም፣ በቴክኖሎጂም እንዲተሳሰሩ እድል የሚሰጥ የግንባታ ዲዛይንም የላቸውም፤ ከዚህም ውጭ ህንፃዎችን ከማስተዳደር አንፃርም ሰፊ ችግር ያለባቸው ናቸው”” ከአቅም በታች ነው እየሰሩ የሚገኙት፡፡ በዚህም በቅርቡ በ130 ህንፃዎች ላይ ባደረግነው የዳሰሳ ጥናት ከ280 ኢንተርፕራይዞች በላይ አነስተኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችንና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ሊያስገቡ የሚችሉ ክፍት ቦታዎችን ለይተናል”” ይሄ ማለት ምንም አዲስ ህንፃ ሳንገነባ ከ6 ሺህ 230 በላይ ስራ ፈጣሪዎችን የማምረቻ ቦታ እንዲያገኙ ያስችለናል፡፡ ይህ ክፍተት የተገኘውም ከዚህ በፊት በተደራጀ የክላስተር ልማት ያልተገነቡና በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ድጋፍና ክትትል ባለመደረጉ ነው፡፡ አሁን እየሰራነው ያለው አደረጃጀት ግን ይህንን ችግር የሚቀርፍ ነው፡፡
ከዛ ውጭ ግን በተለያየ መልኩ ምንም የቦታ፣ የመሸጫና የማምረቻ ቦታ፣ የገበያ ትስስር፣ የፋይናንስ ድጋፍ ሳይደረግላቸው ለሀገር ውስጥ ገበያም ሆነ ለውጭ ገበያ የሚያመርቱ ኢንተርፕራይዞች አሉ፡፡ እነዚህን ኢንተርፕራይዞች ወደዚህ የለማ ክላስተሮች ስናስገባቸው የማምረቻ ዋጋ ስለሚቀንስላቸው ለኢንዱስትሪ ሽግግሩ የበለጠ ቁርጠኛ ሆነው እንዲሰሩ ያደርጋቸዋል፡፡
ቅኝቱም እያንዳንዱ አምራች ኢንዱስትሪ ከአካባቢው ጋር ተስማምቶ እንዲያመርት ስለሚያደርግ ተሳስረው እንዲሄዱ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ስለዚህ አካባቢን እያወደመ ኢንዱሰትሪ እንዲያመርት ስለማይፈለግ የፋብሪካ ቆሻሻዎችን የሚያክም ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
እያንዳንዱ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪ ለየራሱ የቆሻሻ ማከሚያ ሊኖረው ይገባል ከተባለ ከዋጋ አንፃር አዋጭ ስለማይሆን የማምረቻ ዋጋ ለመቀነስ ይህን የቆሻሻ ማከሚያ በጋራ መስራት ግድ ይላል፡፡ ስለዚህ በዚህ መልኩ ክላስተር በሆነ መንገድ በንኡስ ዘርፎች ተደራጅተው የሚያመርቱበት ሁኔታ ነው እየፈጠርን የምንገኘው፡፡
ህዳሴ፡- በዘርፉ ያለው ተግዳሮት ምንድን ነው? ችግሩንስ ለመቅረፍ በመንግስት በኩል ከመሰረተ ልማት፣ ከአደረጃጀት፣ ከአሰራር አንፃር ምን ምን ስራዎች እየተሰሩ ነው?
አቶ ጀማል፡- በመንግስት በኩል በአምራች ኢንዱስትሪው እንደ አቅጣጫ የተቀመጠው ጉልበት ተኮር እና ሰፊ የሰው ሀይል የሚጠቀም፣ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ፣ ለነገ 11 HÄs¤ የካቲግንቦት 20 qN 2008
ለከባድ ኢንዱስትሪው መሰረት የሚጥሉ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪ ለማስፋፋት ነው አቅጣጫ የተቀመጠው፡ ፡ በዚህ ሂደት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተብሎ ከወዲሁ ማስቀመጥ ላይ አንፃራዊ ችግሮች ነበሩ፡፡ በመንገድ በውሃ፣ በመብራትና መሬት ማቅረብ እንዲሁም ከአሰራርና ከአደረጃጀት አንፃር ሰፊ ክፍተት ነበር፡፡ አሁንም በማምረቻና መሸጫ ህንፃዎች እንዲሁም በኢንዱስትሪ መንደሮችን የመሰረተ ልማት፣ የአደረጃጀትና አሰራር ክፍተቶች አሉ፡፡ በኢንተርፕራይዞችም በኩል ከጥቃቅንና አነስተኛ ወደመካከለኛ ኢንዱስትሪ ሲሸጋገሩ የገበያ ትስስርና ሌሎች ድጋፎች ይቆማሉ፡፡ የተመረቁበትም ካፒታል የቀጣይ ጉዟቸውን ለማፋጠን የሚያግዝ አልነበረም፡፡ ስለዚህ እንደተመረቁ በአንድ በኩል የገበያ ትስስር ስለሚቆምባቸውና በራሳቸው ተወዳድረው የሚያገኙት ገበያ አነስተኛ ስለሚሆን ትርፋማነታቸው ይቀንሳል፡ ፡ በመንግስት በኩልም ምንም አይነት ክትትልና ድጋፍ ስለማይደረግ ባጠራቀሟት ገንዘብ ወደ ምርት ከመግባት ይልቅ የተሰጣቸውን መሬት ወደማልማት ሲገቡ ካፒታላቸውን በግንባታ አፍስሰው የፋይናንስ ችግር ያጋጥማቸውና ወደ ማምረት ሳይገቡ ይቀራሉ፡፡ መሬቶችም የለሙ ስላልሆና መንገድ መብራት ውሃ የተሟላላቸው ባለመሆኑ መሀል ላይ አቋርጠው ይቆማሉ፡፡ መሬቱን ለመያዝ ካላቸው ፍላጎት ብቻ ባለቻቸው አነስተኛ ገንዘብ የፋብሪካ ግንባታ ጀምረው ግንባታው ሙሉ በሙሉ ገንዘባቸውን ስለሚወስድባቸው ወደ ማምረት ሳይሸጋገሩ ይቀራሉ፡፡ በዚህም ወደ መካከለኛ ተሸጋግረው አምራች ሳይሆኑ ይታያሉ ወይም በሙሉ አቅማቸው ሲያመርቱ አይስተዋልም፡፡
የድጋፍ ማዕቀፍም በግልፅ ተለይቶ የተቀመጠ ባለመሆኑ ከተሸጋገሩ በኋለ ወደ ምርት እንዳይገቡ ትልቀ ችግር ሆኖ ቆይታል፡፡ በተጨማሪም የፋይናንስ ችግራቸውን የሚፈታ ተቋም ባለመኖሩ በዘርፉ ላይ እንቅፋት ፈጥሮ ቆይቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የከተማ አስተዳደሩ የፋይናንስ ችግራቸውን ለመቅረፍ አዲስ የካፒታል እቃዎች የሊዝ ኩባንያን አደራጅቶ ወደ ስራ ቢገባም ችግሩን ግን ልንሻገረው አልቻልንም፡፡
እንደ ሀገር በየትኛውም አምራች ኢንዱስትሪ የተሰማራ ባለሀብት ቴክኖሎጂና ማሽነሪ ሲያስገባ ከታክስ ነፃ ነው፡፡ ይህ ኩባንያ ግን የንግድ ኩባንያ ስለሆነ በህግም ከታክስ ነፃ ስላልሆነ የፋይናንስ ችግራቸውን በተፈለገው መንገድ ሊቀርፍ አልቻለም፡ ፡ ይህንንም ትክክል እንዳልሆነ ተረድተን በኩባንያው በኩል የሚገቡ ማሽነሪዎች ከታክስ ነፃ እንዲሆኑ በማድረግ የፋይናንስ ችግራቸውን ለመቅረፍ የበኩላችንን መንቀሳቀስ ጀምረናል፡፡ ይሁን እንጂ ሲመረቁም ጭምር ያን ያህል የፋይናንስ አቅማቸው ጠንካራ ስላልነበረ የግብአት ግዥ፣ አስተዳደራዊ ገንዘብ ላይ ትልቅ ፈተና ሆኖባቸው ቆይቷል፡፡ መንግስት ግን የአምራች ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ቁርጠኛ አቋም ስላለው ያለባቸውን ችግር እየለየ ለመደገፍ ጥረት ማድረግ ተጀምሯል፡፡
ማሽነሪ ገዝተው የመስሪያ ህንፃውንም ገንብተው ለአስተዳደራዊና ለማምረቻ ግብአት የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ ከንግድ ባንክ በብድር የሚያገኙበትን አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ስለዚህ አምራች ኢንዱስትሪውን በመደገፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑና የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ነው እየተሰራ ያለ፡፡
ለዚህም ነው በአሁኑ ሰዓት በማምረት ስራ ላይ እያለ የገበያ ትስስር፣ የፋይናንስ ድጋፍ፣ የቴክኖሎጂ መረጣ እስከ ተከላና ኮሚሽኒግ ድረስ በመደገፍ አምራች ኢንዱስትሪውን ማስፋፋት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡ በአንድ በኩል ክላስተሩን የሚገነባ የሚያስተዳድር የሚያከራይ ተቋም ገንብተናል፡፡ በሌላ በኩል አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪው ለከፍተኛው መሰረት ጥሎ እንዲያልፍ ስራዎችን የሚሰራ ሌላ ተቋም በኢንዱስትሪ ሴክተሩ በኩል አደራጅተናል፡፡
ይህ ሴክተር ቴክኖሎጂን ይመርጣል፣ ያስተዋውቃል፣ ከተለያዩ ኩባንያዎች ጋር እስከ ማሽነሪ ተከላ ድረስ ተከታትሎ ያስጨርሳል፡፡ እስከዚህ ድረስ እገዛና ክትትል የሚያደርጉ ተቋማትና ባለሙያዎችን የማደራጀት ስራ ለመስራት ነው እየተንቀሳቀስን የምንገኝ፡፡ ስለዚህ ከአሁን በኋላ በዚህ መልኩ የሚመጡ ባለሀብቶችና ከጥቃቅንና አነስተኛ የሚመረቁ መካከለኛ ባለሀብቶች ከዚህ ቀደም ይደርስ የነበረባቸውን መጉላላትና የአሰራር የአደረጃጀትና የመሰረተ ልማት ክፍተቶችን በማሟላትና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ቶሎ ወደ ምርት ተግባር እንዲገቡ የሚያስችል ተግባራትን ቢሮው እያከናወነ ይገኛል፡፡
ህዳሴ፡- በተያዘው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በማኒፋክቸሪንግ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ከዚህ አንፃር በዘርፉ በአዲስ አበባ ምን ሊሰራ ታስቧል?
አቶ ጀማል፡- ሰፊ የሰው ጉልበት እና የአገር ውስጥ ግብአት የሚጠቀሙ የውጭ ምርቶችን የሚተኩ ኤክስፖርት ምርቶችን የሚያመርቱ እና ያልተወሳሰቡ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለቀጣይ የከባድ ኢንዱስትራላይዜሽን ስራችን መሰረት የሚጥሉት ላይ ትኩረት አድርገን እንሰራለን፡፡ በተለይ በአዲሰ አበባ በ6ቱም ዘርፍ ላይ ነው ትኩረት አድርገን እየሰራን ያለነው፡፡ በይበልጥ ትኩረታችን አልባሳት ላይ የሚሆነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ላይም ትልቅ አንፃራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ስራዎችን በመስራት ላይ ነን፡፡
እውነት ነው አሁን ላይ በአምራች ኢንዲስትሪው ዘርፍ በከተማችን ባለሀብቶች በስፋት ገብተዋል ተብሎ የሚወሰድ አይደለም፡፡ አዋጭ ስላልሆነና በመንግስትም በኩል ማበረታቻዎቹ ስለሌሉ አይደለም ቅድም ያልኳቸው ጉድለቶች እዚህም እዛም ስላሉና እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ከተማ እኛ ለዘርፉ ሆነ ማለትም ለኢንዱስትሪውም ሆነ ለአምራች ኢንዱስትሪው አዲስ ስለሆነ ነው፡፡
የተለያዩ ሀገራት ልምዶችም እንደሚያሳዩት በአምራች ኢንዱስትሪ ያልተሰማሩ ሀገራት ዘላቂ የሆነ ልማት ማረጋገጥ እንደማይችሉ ነው፡፡ በአገልግሎት ዘርፍ ረጅም ርቀት ከሄዱ በኋላ አምራች ኢንዱስትሪውን ደጉመውም ጭምር የሚያበረታቱ ሀገራት አሉ፡፡
እኛም አዲስ አበባን ብንወስድ አሁን ባለው ሁኔታ የኢኮኖሚ ድርሻው ከ50 በመቶ በላይ አገልግሎት ነው፡፡ አምራች ኢንዱስትሪው ሳይሆን አገልግሎቱ ነው ሰፊውን ድርሻ የያዘ”” እስከአሁን ባለሀብቱ ወደአምራች ኢንዱስትሪ እንዲገባ መስራት የሚገባንን ስራ ባለመስራታችንና ሁለተኛ የገቡትም ከመሰረተ ልማትና ከፋይናንስ ድጋፍ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ችግር ስለነበር በስፋት ያለመግባታቸውን ክፍተት ለይተናል፡፡ በተለይ ከኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት ጋር ተያይዞም እጥረት ስለነበረብን ይህንን ከባለሀብቱ ጋር ተቀራርበን ማስረዳት ባለመቻላችን ወደዘርፉ ላለመግባታቸው ሌላ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ስለዚህ አሁን ላይ የተጀመሩ መልካም ጅምሮች ለቀጣይ ስራዎቻችን የተሻለ መደላድል ስለሚፈጥሩ ከባለሀብቱም ጋር ተቀራርበን እየሰራን ነው፡፡
ስለዚህ ባለሀብቱ ወደ አምራች ኢንዱስትሪው ያልገባበት ምክንያት በኛ በኩል የተጠናከረ ስራና ከባለሀብቱ ጋር ተቀራርበን አለመስራታችን ሲሆን በሌላ በኩል ከመሰረተ ልማት አንፃር የሚጎድሉንን በማስረዳት እንደሚሟሉ የማግባባት ስራ ባለመስራታችን ነው፡፡
ሌላውና ዋነኛው ባለሀብቱ ወደ አምራች ኢንዱስትሪው እንዲገባ ያላደረገው አንዱ ምክንያት የአጭር ጊዜ ትርፍ እይታ ነው”” በአምራች ኢንዱስትሪ የተሰማራ በአጭር ጊዜ ትርፍ ማግኘት አይችልም ወደዚህ የተሰማራበትን ካፒታል ግን ቢነግድበት በአጭር ጊዜ ምን ያህል ትርፋማ እንደሚሆን ስለሚያሰላ ወደ አምራች ኢንዱስትሪው ለመግባት አይፈልግም፡፡ የማይገባበትም ምክንያት በንግዱ ዘርፉ በአጠቃላይ በአገልግሎት ዘርፉ ኢፍትሀዊ በሆነ መንገድ የሚገኙ ጥቅሞችን መንግስት ቁርጠኛ አቋም ወስዶ መዘጋት ባለመቻሉ ነው፡፡
ስለዚህ ባለሀብቱ ወደ አምራች ኢንዱስትሪው እንዲገባ በተቻለን አቅም አመራጮችን ልናሳይ ይገባል፡፡ ባለሀብቶችን ወደ ማኑፋክቸሪንጉ ዘርፍ እንዲገቡ አቅጣጫ አስቀምጠን እያበረታታን እንገኛለን፡፡
ህዳሴ፡- መሬት ወስደው እስካሁን ወደ ስራ ያልገቡ ባለሀብቶች አሉ፡፡ ምክንያቱ ምንድን ነው? የተወሰደስ የማስተካከያ እርምጃ አለወይ?
አቶ ጀማል፡- ዘላቂነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ ከተፈለገ ባለሀብቱን ወዴት ነው መምራት ያለብን፣ የትኞቹን ዘርፎች ማበረታታት አለብን፣ ያበረታታናቸውን ዘርፎችንስ ደግሞ ተከታትለን ከግብ ማድረስ እንዴት እንችላለን፣ ለሚለው መልስ ሳያገኝ ቆይቷል፡፡ ማበረታቻና ድጋፍ ተብሎ ለተሸጋገሩት መሬት በምደባ ከተሰጠ በኋላ ለታለመለት አላማ መዋሉን ማረጋገጥ ላይ በመንግስት በኩል ክፍተት ነበር፡፡ ሌሎች የፋይናንስ፣ የገበያ ትስስርና ሌሎች ድጋፎችም ከየት ነው የሚያገኘው የሚለው ተገቢ ምላሽ ሳያገኝ ስለቆየ በቂ እይታ ነበረው ተብሎ የሚወሰድ አልነበረም”” በተለይ ለኢንዱስትሪ ልማቱ ተብለው በተከለሉ አካባቢዎች የመሰረተ ልማት ችግር አንዱና ዋነኛው ማነቆ ነው፡፡ ስለዚህ ባለሀብቶቹ የተሰጣቸውን መሬት ለታለመለት አላማ እንዳያውሉት ከላይ የጠቀስኳቸው ክፍተቶች መንገድ ከፍተውላቸዋል፡፡
ስለዚህ ክትትላችን ደካማ የነበረ ሲሆን መሰረተ ልማት ከማሟላትና ባለሀብቱን ወደ አምራች ኢንዱስትሪው ከማስገባት አንፃር በመንግስት በኩል ትኩረት ተሰጥቶት ሳይሰራ በመቆየቱ ባለሀብቱ ወደ ማምረት ስራ እንዲገባ ምቹ ሁኔታ አልተፈጠረም”” ይህን ብለንና በጥናታችን አረጋግጠን ስለተነሳን እነዚህ ባንድም ሆነ በሌላ መንገድ በሙሉ አቅም የማያመርቱትን እንዲያመርቱ፣ ወደ መስመሩ ያልገቡትንም እንዲገቡና እንዲያመርቱ በቅድሚያ መደገፍ አለብን ብለን ነው የተግባባን ነው፡፡ ደግፈን ችግራችውን ፈትተን ካበቃን በኋላ ግን ወደ ማምረት ተግባር በማይገቡት ላይ ወደፊት የእርምት እርምጃ እየወሰድን የምንሄድበት ሁኔታ ይኖራል፡፡
ህዳሴ፡- በአሁኑ ወቅት መንግስት በተለያዩ ቦታዎች የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እያስፋፋ ይገኛል፡፡ ከዚህ አንፃር በከተማችን ምን ለመስራት ታስቧል?
አቶ ጀማል፡- ጥሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከሚገነባባቸው ከተሞች ውስጥ አንዷ አዲስ አበባ ናት፡፡ የመጀመሪያው የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታም አዲስ አበባ ላይ ነው የተገነባው፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኩም ማምረት ጀምሮ ምርቱን ወደ ውጭ በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ ነው፡፡ ይሄም በቂ አይደለም በሚል አሁንም የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት ለሚችሉ ለሰፋፊ ኢንዱስትሪዎች መሬት የመከለል ስራ ተሰርቷል፡፡ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪውም የሚውል መሬት የመከላከል ስራ ተሰርቷል፡፡ አሁን ባለበት ሁኔታ ሀዋሳ ላይ እንደተገነባው ባህር ዳር፣ መቀሌ፣ ኮምቦልቻና ድሬዳዋ ላይም ተመሳሳይ የኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገነባ ሲሆን እኛም ጋር በቀጣይ ይገነባል፡፡ ለዚህ ነው እነዚህን ተቋማት የሚያስተዳድር የሚያለማ ራሱን የቻለ ተቋም እንገነባለን ብለን ቀድመን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ለኢንዱስትሪ ፓርኩም የሚሆን ቦሌ ለሚ አካባቢ መሬት የመከለል ስራ ተሰርቷል፤ መሬቱ ግን ነፃ ሆኖ ለልማት ተዘጋጅቷል፡፡ ለኢንዱስትሪ መሰረት ሲጣል እዛው ሌላም ትልቅ የስራ እድልና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚደረግባቸው አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪዎች በየክፍለ ከተማው ቢኖሩ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች የስራ እድል ከመፍጠር ባሻገር ነገ ኢንዱስትራሊስቶችን ማፍራት ይቻላል በሚል በአሁኑ ሰአት በየክፍለ ከተማው 500 ሄክታር መሬት የማዘጋጀት ስራ ተጀምሯል፡፡
ከነዚህ ውጭም በሂደት ሊታጠፉ የሚችሉ መለስተኛ የክላስተር ማዕከላት በየክፍለ ከተማው እንዲኖሩ ለማድረግ ውይይት ላይ ነን፡፡ የውጭ ሀገራት ተሞክሮም እንደሚያሳየን በተለይ በጀርመን የሚሰራው በአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንዱስትሪ ውስጥ ትልቅ ሀብት ፈጥረው ሲያበቁና ወደ ሌላ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ ሲሸጋገሩ የክላስተር ማዕከላቱን ወደ ሌላ አገልግሎት ማዕከልነት ያውሉታል፡፡ የማምረቻ ክላስተሮችና ሼዶችን ትምህርት ቤትና መዝናኛ ለተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ነው የሚያውሏቸው፡፡ እኛም ክላስተርድ ሆነው መሄድ አለባቸው ስንል በቀጣይ ይህንን ተሞክሮ ተግባራዊ ለማድረግ በማሰብ ነው፡፡ መስራትም ይቻላል፡፡
ህዳሴ፡- በመጨረሻ ግንቦት 20ን አስመልክተው ለሴክተሩ ሰራተኞች ለባለድርሻ አካላትና ለአንባቢዎቻችን የሚያስተላልፉት መለዕክት ካለ?
አቶ ጀማል፡- የግንቦት 20 25ኛ አመት በአል እንደ ሴክተር ስናከብር ትልቅ ደስታ እየተሰማን ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ በቢሮ ደረጃ የተደራጀው አምና ነው፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ በሴክተሩ ውስጥ የሚገኝ ሴክተሩ የማን ውጤት እንደሆነ የሚገነዘብበት፣ አጋጣሚ ስለሚፈጥር በኛ በኩል ለየት ያለ አጋጣሚ ፈጥሮልናል”” በአጠቃላይ በዚህ አመት በኢንዱስትሪ ዘርፍ አጠቃላይ ጉዳዮች ላይና በስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ እና ኢንዱስትሪ ሴክተሩ ምንም ካልነበረበት አሁን ወደ ደረሰበት ደረጃ የሚያሳይ ውይይት እንድናደርግ እድል ስለሚፈጥርልን ግንቦት 20 25ኛ አመት የድል በአል እንኳን አደረሳችሁ እላለሁ፡፡
ግንቦት 20ን ስናስብ የኢኮኖሚ መዋቅር ለውጡን ነው የምናስበው፡፡ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ የኢንዱስትሪው ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ብቻ አይደለም፡፡ የኢንዱስተሪ ሴክተር ሲባል የአንድ አመራር ወይም ፓርቲ ጉዳይ ሳይሆን የሀገር ጉዳይ ነው፡፡ የሀገር ጉዳይ ደግሞ ሁሉንም ይመለከታል፡፡ ስለዚህ ግንቦት 20 ያበረከተልንን ትሩፋትና የጋራ ተልዕኮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ከኛ ጋር በመስራት የኢንዱስተሪ ሽግግሩን ማፋጠን ይኖርብናል፡፡
ህዳሴ፡- ስለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቻችን ስም እናመሰግናለን፡፡
አቶ ጀማል፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

No comments:

Post a Comment