በአገራችን የፖለቲካ ስልጣን በህዝብ
ነፃ ምርጫ የሚያዝ እንደሆነ በህገ መንግስታችን ተደንግጓል፡፡ እንደገናም በአገራችን የግድ በሆነው የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ
ስርአት የፖለቲካ ፓርቲዎች መመስረትን ጨምሮ የመደራጀትና ለፖለቲካ ስልጣን የመፎካከር መብት በህገ መንግስታችን በጥብቅ ተደንግገዋል፡፡
እነዚህ ሁለት ህገ መንግስታዊ ዋስትናዎች በአንድ በኩል አገራችንን የህዝብ ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤትነት የተረጋገጠባት፣ በሌላ በኩል
ደግሞ የመድበለ ፓርቲ ህልውና የተመሰረተባት ዴሞክራሲያዊ አገር እንድትሆን አድርገዋታል፡፡
እንደሚታወቀው
የፖለቲካ ስልጣንን በነፃ ምርጫ የመመስረት መብት የህዝቡና የህዝቡ ብቻ ነው፡፡ ፓርቲዎች ሊወዳደሩ ከመቻል አልፈው የፖለቲካ ስልጣኑን
በኃይልም ሆነ በማጭበርበር ሊይዙ የማይችሉበት ይልቁንም የሉዓላዊ ሥልጣኑ ባለቤትነት የህዝቡ ብቻ የሆነበት ስርዓት ደግሞ በእርግጥም
ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ህዝቡ ብዝሃነት ያለው ከመሆኑ የሚመነጩ በርካታ ፍላጎቶች የሚኖሩት
እንደሚሆንና ይህም በአንድ ፓርቲ ብቻ ሊወከል እንደማይችል በመገንዘብ በአገራችን የመድበለ ፓርቲ ህልውና ህጋዊ ዋስትና ተሰጥቶታል፡፡
በዚህ መሠረት ዜጎች በሚያስማማቸው ፕሮግራም ዙሪያ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችን ወይም ፓርቲዎችን እንዲመሠርቱ፣ እነዚህ ፓርቲዎች
ህጋዊ
ሠላማዊ
በሆነ መንገድ እንዲወዳደሩና ህብረተሰቡ ከፓርቲዎች መካከል በተሻለ ደረጃ መብቴንና ጥቅሜን ያስከብርልኛል የሚለውን ድርጅት በመምረጥ
ለስልጣን ሊያበቃ እንደሚችል የአገራችን ዴሞክራሲ በህጋዊ ማዕቀፉ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ላለፉት አራት ምርጫዎች ያረጋገጠው ጉዳይ
ነው፡፡ በመሆኑም ስለ አምስተኛው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ስናስብ መነሻችን መንግስትን በነፃ ውሳኔውና ምርጫው የመመስረት ሉዓላዊ
ስልጣን የህዝቡ እንደሆነ በማወቅና ፓርቲዎች ደግሞ አማራጫቸውን በህጋዊና ሠላማዊ መንገድ ለህዝብ በማቅረብ የመፎካከር የተሟላ መብት
እንዳላቸው በመቀበል ጭምር ነው፡፡ በዚህ ረገድ የህዝብን የመወሰን ስልጣን መጋፋትም ሆነ የፓርቲዎችን ህጋዊና ሠላማዊ በሆነ መንገድ
የመወዳደር መብት መገደብ ፈፅሞ ተቀባይነት የሌላቸው መሆናቸውን በአፅንዖት መመልከት ይገባል፡፡
ይህን መነሻ
በማድረግ ህገ መንግስታችን ከፀደቀ በኋላ ባሉት ሃያ ዓመታት አራት አገራዊና ክልላዊ፣ አራት ደግሞ የአካባቢና የማሟያ ምርጫዎችን
አካሂደናል፡፡ ምርጫዎቹ የህዝብ ሉዓላዊነት የተከበረባቸው ምርጫዎች ነበሩ፡፡ ህዝቡም በእነዚህ ምርጫዎች በሰፊው ተሳትፏል። እንደሚታወቀው
በበለፀገው ዓለም ብዙሃኑ ህዝብ በተለይ ደግሞ ኒዮ ሊበራሊዝም የበላይነቱን ካረጋገጠበት ጊዜ በኋላ ባሉት ዓመታት በምርጫ ያለው
ተሳትፎ ግፋ ቢል ሀምሳ በመቶ ያህል ሲሆን ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ በመሄድ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ለዚህ መሠረታዊው ምክንያት
ደግሞ በብዙ የምዕራብ አገሮች ብዙሃኑ ህዝብ በአጠቃላይ በስርዓቱ በተለይ ደግሞ በምርጫ ስርዓቱና ውጤቱ ላይ አመኔታ ማጣቱ ነው፡፡
ይህም ህዝቡ በምርጫ ብሳተፍም ባልሳተፍም የማመጣው ለውጥ የለም ብሎ ወደ ማመን ያዘነበለበት ሁኔታ ከመፈጠሩ ጋር ተያይዞ የተከሰተ
ችግር በመሆኑ በአንድ ወቅት ለመምረጥ መብት መከበር ከባድ መስዋዕት የከፈሉ ሁሉ በምርጫ ዴሞክራሲው ደስተኞች ባለመሆን ራሳቸውን
የሚያገልሉበት ሁኔታ እንደተፈጠረ የሚያመላክት ነው፡፡
በአገራችን ግን ብዙሃኑ የአገራችን
ህዝብ ከዚህ በላቀ ምጣኔ ሲሳተፍ ቆይቷል፡፡ በሁሉም ምርጫዎች የተመዘገበውና የመረጠው ህዝብ ከዘጠና በመቶ በላይ ነው፡፡ ይህም
የአገራችን ምርጫ ለህዝቡ ከፍተኛ ትርጉም የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን ዕድሉን ከምርጫዎች ጋር አቆራኝቶ የሚመለከት ህዝብ እንዳለን አመላካች
ነው፡፡ የአገራችን ህዝቦች መንግስት ልማትን ከማፋጠንና ዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደርና ዘላቂ ሠላምን ከማስፈን ባሻገር ተጠቃሚነታቸውን
ለማረጋገጥ የሚጫወተውን ሚና ተመልክተዋልና በምርጫ ለሚመሰርቱት መንግስት የላቀ ትኩረት ሰጥተው በሂደቱ በሰፊው መሳተፋቸው የሚጠበቅ
ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ያለፉት ምርጫዎቻችን ሰፊ የህዝብ ተሳትፎ ያልተለያቸው መሆኑ የሚያመላክተው ምርጫዎቻችን በእርግጠኛነት የህዝብ
ጠንካራ አመኔታ የተቸራቸው ምርጫዎች እንደነበሩ ነው፡፡
ባለፉት አራት ምርጫዎች በአገራችን
የሚገኙ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተፎካካሪነት ቀርበው የተወዳደሩበት ሁኔታ እንደነበረም ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ከፓርቲዎች ተሳትፎ
አኳያ በአገራችን የተካሄዱትን ምርጫዎች በበለፀገው ዓለም ከሚካሄዱ ምርጫዎች የሚለያቸው መሠረታዊ ነገር የለም፡፡ በበለፀገውም ዓለም
የተለያዩ ፓርቲዎች ለስልጣን ይወዳደራሉ፡፡ በአገራችንም እንደዚሁ፡፡ ስለዚህም በአገራችን የተገነባው አዲሱና ዴሞክራሲያዊው ሥርዓታችን
የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ ይህ ተመሳሳይነት እንደተጠበቀ ሆኖ ግን በአገራችንና በበለፀገው ዓለም
ተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል የሚታዩ ጉልህ ልዩነቶች አሉ፡፡
በበለፀገው
ዓለም ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ በተፎካካሪነት የሚቀርቡት ፓርቲዎች ቁጥር ከአንድ እጅ ጣት የማይበልጥ ነው፡፡ ለዚያውም ከተፎካካሪ
ፓርቲዎች መካከል የጎላ ጥንካሬ የሚኖራቸው ከሁለትና ሦስት ፓርቲዎች የማይበልጡ ናቸው፡፡ ይህም የሆነው በአንድ በኩል ገና ከጥዋቱ
የመደራጀት መብት የተገደበና በተለይ ደግሞ ለባለሃብቶች ብቻ የተፈቀደ ሆኖ በመጀመሩሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ፓርቲዎቹ በርከት
ብለው ቢጀምሩም በዘመናት ሂደት ልዩነቶቻቸውን እያጠበቡና እየተዋዋጡ በመምጣታቸው ነው፡፡ በአገራችን ግን የመደራጀት መብት ገደብ
ያልተደረገበት መብት በመሆኑ ገና ከጠዋቱ ብዙ ፓርቲዎች ሊፈጠሩ ችለዋል፡፡ በሌላ በኩል ፓርቲዎች በተለይ ደግሞ ብዙዎቹ ተቃዋሚ
ፓርቲዎች ተመሳሳይ የፖለቲካ ዓላማ እያላቸውም ቢሆን ተቀራርበውና ተሰባስበው የመታገልና የመፎካከር ባህል ያላዳበሩ ከመሆናቸው ጋር
ተያይዞ ከጊዜያዊ ህብረቶች ያለፈ ቋሚ ውህደት በመፍጠር ሲዋዋጡ አይታዩም፡፡ በአንድ የምርጫ ወቅት አነሰ ቢባል ሀምሳና ስልሳ ተፎካካሪ
ፓርቲዎች ለመንበረ ስልጣን ይፋለማሉ፡፡ በዚህ ምክንያት የመድብለ ፓርቲ ሥርዓታችን ከኢህአዴግ ውጭ ብዙም ጠንካራ ተፎካካሪ ፓርቲ
የማይታይበት ነገር ግን በብዙ ትንንሽ ፓርቲዎች የተጥለቀለቀ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ሊሆን ችሏል፡፡
No comments:
Post a Comment