ከተማችን አሁን ላይ በከፍተኛ የለውጥ ማዕበል ውስጥ ትገኛለች፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ከመቼውም ጊዜ በላይ ፍላጎቱ እየጨመረ የመጣ ህዝብ ተፈጥሯል፡፡ ይህም እድገት ሁሌም ሂደት መሆኑንና የእድገት
ማማ እንደሌለ ያመላክታል፡፡ በአራቱም የከተማችን ጫፍ አመራሩም ፈፃሚውም ህዝቡም በስራ ተወጥረዋል፡፡ ስራ ለነገ የማይመከር ቢሆንም
በተለያዩ ምክንያቶች ትናንት ያልተሰሩ የልማት ስራዎችና ያልተፈቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለዛሬ ተደራርበው የተደራጀ እንቅስቀሴን
ጠይቀዋል፡፡ ለዚህም የመንግስት፣ የድርጅትና የህዝብ ክንፎች ግንኙነታቸውን የበለጠ አጠናክረው መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ቆርጠው
ተነስተዋል፡፡ በተግባርም አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገብ ጀምረዋል፡፡
ለዚህ ማሳያ እንዲሆነን የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማን የልማትና
የመልካም አስተዳደር ግንባታ እንቅስቃሴን ቃኘት አድርገናል፡፡ ክፍለ ከተማው ህዝቡን በማነቃነቅ በርካታ የልማት ተግባራትን እያከናወነ
ነው”” በተለይም የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት በአጠቃላይ ህገ ወጥ ተግባራትን ለመከላከል
ባደረገው የተቀናጀ እንቅስቃሴ ሰፋፊ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ የዝግጅት ክፍላችንም ከክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ
ከአቶ ፍፁም ካህሳይ ጋር ቆይታ በማድረግ ለውድ አንባቢያችን በዚህ መልኩ ይዘንላችሁ ቀርበናል”” መልካም ንባብ፡፡
ህዳሴ፡- የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በክፍለ ከተማውና በወረዳዎች ምን ምን ስራዎች
እየተከናወኑ ነው?
አቶ ፍፁም፡- በክፍለ ከተማችን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት አስቀድመን እያደረግን
ያለነው ከተለያዩ አካላትና የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ችግሮችን የመለየት ስራ ሰርተናል፡፡ ችግሮችንም ከለየን በኋላ ከሚመለከታቸው
ባለድርሻ አካላትና ከህብረተሰቡ ጋር በችግሮቹ ዙሪያ ውይይት አድርገናል”” የተለዩ
ችግሮችንም አሟጠን ለመፍታት በምክር ቤት የተነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመሰብሰብ ሞክረናል፡፡ በተለያዩ አደረጃጀቶችም
መድረኮችን በመክፈት በመልካም አስተዳደር ዙሪያ የተነሱ ጥያቄዎችንም ለመለየት ሞክረናል፡፡ ባጠቃላይ ከክፍለ ከተማ እስከ ቀጠና
ድረስ በየደረጃው ከ30 ሺህ ህዝብ በላይ በተገኙበት መድረኮች በዝርዝር ችግሮች ዙሪያ ውይይት ተደርጎ በክፍለ ከተማው አመራር የጋራ
ተደርገዋል፡፡ የጋራ ያደረግናቸውንም በእቅድ የትኛው ችግር መቼና እንዴት መፈታት እንዳለበት እንዲሁም ማን መፍታት እንዳለበት ግልፅ
አቅጣጫ በማስቀመጥ ወደ ተግባር ገብተናል፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በሶስት መንገድ ከፍለናቸዋል፡፡ አንደኛው በከተማ የሚፈቱ
አሉ፡፡ ሁለተኛው በክፍለ ከተማ ደረጃ የሚፈቱ ሶስተኛ በወረዳው አቅም የሚፈቱ ብለን ከፋፍለናቸዋል፡፡ በወረዳ ደረጃ ስንል በመንግስት
አቅም ብቻም ሳይሆን በህዝቡም አቅም ጭምር ብለን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመለየት ሞክረናል፡፡
በቅርቡ በክፍለ ከተማ ደረጃ የሚገኙ የተለያዩ አደረጃጀቶች ጋር ማለትም ከምክር ቤት፣ ከፎረም፣
ከእድርና ከመሳሰሉት አደረጃጀት አመራሮች እንዲሁም ፈፃሚዎች በተገኙበት ውይይት አድርገናል፡፡ በዚህም መድረክ የተፈቱ ችግሮችን
አድንቀው ያልተፈቱ ችግሮችን ግን በፍጥነት መፈታት እንዳለባቸው አንስተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በክፍለ ከተማም ይሁን በወረዳ ደረጃ
በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ሲነሱ የነበሩ ችግሮችን በአብዛኛው በእቅዳችን በአመቱ ይፈታሉ ካልናቸው መካከል ከ60 በመቶ በላይ ለመፍታት
ተችሏል”” በወረዳ ደረጃም በመንግስትና በህዝቡ አቅም በጋራ ይፈታሉ ብለን ካልናቸው ብዙዎቹ 70 እና
80 በመቶ በላይ ተፈትተዋል፡፡ በከተማ ደረጃ አብዛኛው አፈፃፀሙ ዝቅተኛ ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት አንዳንዱ የመመሪያ ጉዳይ
ስለሆነ፣ አንዳንዱ ደግሞ ትላልቅ በጀት የሚጠይቅና የተለየ አሰራር የሚጠይቅ ስለሆነ በአጭር ጊዜ ለመፍታት አስቸጋሪ ስለሆነ ነው
እንጂ በቂ በጀትና አቅም ኖሮ ሳይፈቱ የቀሩ አይደሉም፡፡
ህዳሴ፡- ተፈቱ ከሚባሉ ጥያቄዎች ዋና ዋናዎቹን ሊገልፁልን ይችላል?
አቶ ፍፁም፡- በአብዛኛው በክፍለ ከተማ ደረጃ የህብረተሰቡ ችግር ሆነው የቆዩ ሶስት ትላልቅ
ችግሮች ተፈትተዋል፡፡ አንደኛው ከ1 ሺህ 500 ህዝብ በላይ ጥያቄ ሆኖ የቆየው የሰባት ማህበራት የባለቤትነት ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ
ይሰጠን የሚል የመብት ጥያቄ ነበር፡፡ 11 አመት የቆየ ጥያቄና ማህበራቱ ህጋዊ አይደሉም ተብለው በፀረ ሙስና ተይዘው ካርታቸው
ታግዶ ምንም አይነት ግልጋሎት ሳያገኙ የቆዩ ናቸው፡፡ ማህበራቱ ህንፃቸውን አጠናቀው ስለነበር በወቅቱ የማህበራቱ አመራሮች በህጋዊ
መንገድ ስላልሆነ የገነቡት በህግ ተጠይቀው እስከ ሰባት አመት ተፈርዶባቸው ታስረው የተፈቱ በመሆኑ የስልክ፣ የመታወቂያ፣ የውሃ፣
የመብራት አገልግሎት እንዳያገኙ ታግደው ቆይተዋል፡፡ ህንፃዎቹ ግን ትላልቅ በመሆናቸውና አመራሩ ባጠፋው ጥፋት አብዛኛው አባላት
የተጎዱ በመሆናቸው አሁን ላይ ከተማ አስተዳደሩ ችግሩን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሲንከባለል የቆየውን ችግር የሚፈታ ታሪካዊ ውሳኔ
ወስኗል፡፡ ማህበራቱን ባለመብት ማድረግ አለብን የሚል፡፡ ሁለተኛው ከአርሶ አደሩ ጋር የተያያዘና መፍትሄ የተሰጠበት ነው”” በተለይ የአርሶ አደሩ ልጆች የመብት ጥያቄ ለረጅም ጊዜ ሲጠየቅ ነበር፡፡ እድሜአቸው ከ18
አመት በላይ የሆናቸው የአርሶ አደሩ ልጆች ምትክ ቦታና ከካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ የሚጠይቁት ጥያቄ ነበር፡፡ ንፋስ ስልክ ላፍቶ
ክፍለ ከተማን ደግሞ ከሌሎች ክፍለ ከተሞች ለየት የሚያደርገው በማስፋፊያ አካባቢዎች በርካታ አርሶ አደሮች ያሉበት መሆኑ ነው፡፡
በሶስት ወረዳዎቻችን ውስጥ አርሶ አደሮች ይገኛሉ፡፡ እድሜአቸው 18 አመት እና ከዛ በላይ የሆናቸው የአርሶ አደር ልጆች ደግሞ
በጣም በርካታ ናቸው፡፡ የነዚህንም ዜጎች ጥያቄ ካቢኔው ወስኖ መብታቸው እንዲረጋገጥ በመደረጉ ለረጅም አመታት የነበረባቸውን የመብት
ጥያቄ በመፍታት የተሻለ አሰራር ዘርግቷል፡፡ በዚህም ከዚህ በፊት ይሰጣቸው የነበረውን 105 ካሬ ሜትር ምትክ ቦታ በአሁኑ ሰአት
ወደ 150 ሜትር ካሬ አሳድጎ ለጥያቄአቸው ምላሽ እንድንሰጥ ካቢኔው አሳውቆናል በዚህም ደስተኛ እንዲሆኑ አስችሏል፡፡
በሶስተኛ ደረጃ የተፈታው ትልቁ ችግር የመጠጥ ውሃ ችግር ነው፡፡ በተለይ በማስፋፊያ አካባቢዎች ወረዳ 11 ሃና ማሪያምና
ለቡ አካባቢዎች በርካታ ህዝብ የሰፈረበት ሲሆን የውሃ አቅርቦቱ ጭራሽ ያልተዘረጋለት ነበር፡፡ አሁን ላይ መስመሩ ተዘርግቶ ከ300
ሺህ በላይ ህዝብ ለረጅም ጊዜ የመልካም አስተዳደር ችግር ሆኖ የቆየውን ጥያቄ በመመለስ አብዛኛውን የክፍለ ከተማውን ህዝብ ተጠቃሚ
ማድረግ ተችሏል፡፡ እነዚህ ሶስቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በከተማ ደረጃ በመፍታት አስተዳደሩ ለህዝቡ ያለውን ወገንተኝነትና
ቁርጠኝነት በተግባር አረጋግጧል፡፡
በክፍለ ከተማ ደረጃም በርካታ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት አድርገናል፡፡ አንደኛው ልዩ ትኩረት የሚሰጠው የሰነድ አልባ
ቤቶች ጉዳይ ነው፡፡ በሰነድ አልባ ቤቶች በኩል የመልካም አስተዳደር ችግር ተደርጎ ሲነሳ የቆየው የካርታ ጥያቄ ምላሽ አለማግኘት
ነበር፡፡ የሰነድ አልባ ጉዳዩን በሁለት መልኩ በማየት ለመፍታት ጥረት አድርገናል፡፡ አንደኛው እስከ 1988 ዓ.ም ድረስ ያሉ ናቸው፡፡
ይሄ ቀደም ያለና እየተስተናገዱ የመጡ ሲሆን ግን ደግሞ የተንጠባጠቡም ናቸው፡፡ ሁለተኛው እስከ 1997 ዓ.ም ሲሆን ይሄ በጣም
በርካታ ቁጥር ያለው ነው፡፡
ከታች ተጣርቶ ወደኛ የመጣው 20 ሺህ 256 ባለመብት ነን የሚልና ካርታ ይሰራልን ጥያቄ ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ በትክክል
መስፈርቱን የሚያሟሉ ግን 3 ሺህ 26 ያህሉ ብቻ ናቸው፡፡ ከዚህም ውስጥ 2 ሺህ 160 ያህሉ ካርታ ተዘጋጅቶላቸዋል፡፡ 1 ሺህ
212 ያህሉ ደግሞ የፕላን ተቃርኖ ያጋጠማቸው ናቸው”” የፕላን
ተቃርኖ ማለት ሰዎቹ የሰፈሩበት ቦታ በማስተር ፕላኑ ላይ አረንጓዴ ልማት ወይም የመንገድ መሰረተ ልማት የሚሰራበት ቦታ በመሆኑ
ይሄን ማሻሻል ይጠይቃል፡፡ ሰዎቹ ግን ባለመብት ናቸው ማስተር ፕላኑ በሚጠይቀው መንገድ ተሻሽሎ ጥያቄያቸው ይስተናገዳል፡፡ ካርታ
ከተዘጋጀላቸው 2 ሺህ 160 ውስጥ እኛ ጋር ቀርበው ካርታ የወሰዱት ግን 285 ብቻ ናቸው፡፡
ሁለተኛ የተጠቃሚነት ጥያቄ ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የመስሪያ፣ መሸጫ ሼዶችን ያላገኙ በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁት
ጥያቄ ነበር ይሄ በአብዛኛው ተፈትቷል፡፡ ክፍት የሆኑና የታሸጉ ሼዶችን ለተደራጁ አንቀሳቃሾች የማስተላለፍ ስራ ሰርተናል፡፡ በዚህም
በርካታ ሰው ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡
ሌላውና በሶስተኛነት የተፈታው ጉዳይ ከትራንስፖርት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በበርካታ አካባቢዎች ትራንስፖርት ለማግኘት
ሰልፍ ይበዛል፡፡ በዚህም ህዝቡ ችግሩን ለመቅረፍ ተጨማሪ ተሽከርካሪዎች እንዲጨመሩና ታክሲዎችም ቆራርጠው የሚጭኑትን እንድናስቆም
ጠይቆን ነበር፡፡ በዚህም በኩል በበርካታ መስመሮች ላይ የማስተካከል ስራ ሰርተናል፡፡ ታክሲዎቹ ቆራርጠው እንዳይጭኑ የማድረግ ስራ
ተሰርቷል፡፡ ተጨማሪ ተሽከርካሪዎችንም ወደ መስመር እንዲገቡ ጠይቀን በማሰማራት የተሻለ ጥረት ተደርጓል፡፡ አሁንም ችግሩ ሙሉ በሙሉ
አልተቀረፈም፡፡ በከተማ ደረጃም ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ በዚህም በየአካባቢው ረጃጅም ሰልፎችን የቀነስንበት ሁኔታ
ተፈጥሯል፡፡
ሌላው በክፍለ ከተማው ጎላ ብሎ የሚታየው የመልካም አስተዳደር ችግር ከጋራዥ ጋር ተያይዞ በየአካባቢው የሚነሱ ጥያቄዎቸ
ናቸው፡፡ በክፍለ ከተማችን በርካታ አካባቢዎች የሚገኙ ጋራዦች ወደ አንድ አካባቢ ያልተሰባሰቡ በመሆናቸው በትምህርት ቤቶችና በመኖሪያ
ቤቶች እንዲሁም በተለያዩ ተቋማት ላይ የድምፅ ብክለት እያስከተሉ መሆናቸውን ህዝቡ በተደጋጋሚ ጊዜ ለአደጋ ተጋልጠናል የሚል ጥያቄ
ሲያነሳ ቆይቷል፡፡ በክፍለ ከተማችን 244 ጋራዦች አሉ፡፡ ወደ 41 ያህል ባለቤቶችን በተለያዩ ምክንያቶች ማግኘት አልተቻለም ይሁን
እንጂ በአጭር ጊዜ ባለንብረቶቹን በሙሉ ጠርተን የማስተካከያ እርምጃ እንወስዳለን፡፡
በጥናት የተገኘው ግኝት አንደኛ ከተሰጣቸው ቦታ አስፋፍተው የተገኙ አሉ፡፡ በርካቶችም መንገድ ዘግተውና አጣበው እየሰሩ
መሆኑንም ተደርሶበታል፡፡ በተለይ በርካቶች በመኖሪያ ቤቶች መካከል ሆነው በድምፅ ብክለት ነዋሪው እየተረበሸ መሆኑ በጥናቱ ተደርሶበታል፡፡
ቁጥራቸው የማይናቅና በርካታ ጋራዦች ደግሞ መንግስት በ1997 እና በ2007 ዓ.ም ምትክ ቦታ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ሰጥቷቸው
እያለም በሁለቱ ቦታ ላይ እየሰሩ ይገኛሉ””
አንዳንዶቹም ሸጠውታል፡፡ ስለዚህ
ይህን ያገኘነውን ዝርዝር ጥናት ከባለሀብቶቹ ጋር የጋራ ውይይት አድርገን የማስተካከያ እርምጃ እንወስዳለን፡፡ የማስተካከያ እርምጃውም
በቅርቡ እንዴት ማስተካከል እንዳለባቸው በዝርዝር ከተወያየን በኋላ ሲሆን ህግና ስርአት አክብረው ለሚሰሩትም እውቅና እንሰጣለን፡፡
ሌላው ከወጣት ማዕከላትና ከስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ጋር ተያይዞ ሰፋ ያሉ ቅሬታዎች ይነሳሉ፡፡ በርካቶች ግን በመፈታት
ሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡ አንዳንዱም የማስፋፊያ ጥያቄ ነው ያለው፤ አንዳንዱም አዲስ ይሰራልን ጥያቄ ነው ያቀረበው እንደ ክፍለ ከተማ
ወደ አምስት ወረዳዎች ከህዝቡ ጋር ተገናኝተው ውይይት ያደረጉ ሲሆን በኛ በኩልም በጀት በመጨመር ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ
ነው፡፡ በአንዳንድ ወረዳዎች ወጣት ማዕከላት ቢሰሩም እስካሁን በግብአት ችግር ወደ ስራ አልገቡም፡፡ ይህንንም የመልካም አስተዳደር
ጥያቄ ከልማት ጋር የሚነሳ በመሆኑ ወደ ስራ ለማስገባት ጥረት እያደረግን ነው፡፡
ሁለተኛው ከአገልግሎት አሰጣጣችን ጋር የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ናቸው፡፡ በዚህም
ብዙዎቹ ሴክተሮች በስታንዳርድ መስራት ጀምረዋል፡፡ እያንዳንዱን ስራ በስታንዳርዱ መሰረት እየመዘገቡ መሄድ ላይ ክፍተቶች ነበሩ፡፡
አሁን ላይ ግን ብዙዎቹ ሴክተሮች ወደዚህ ስርአት መግባትና ህዝቡን ማገልገል ጀምረዋል፡፡ በኛ በኩልም ዝርዝር መረጃዎችን በመያዝ
ማን ምን ፈፀመ በምን ያህል ጊዜ እያልን እየመዘገብን የምንሄድበትን ስርአት ዘርግተን የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ችግር እየቀረፍንእንገኛለን፡፡
ህዳሴ፡- የፀረ ኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉስ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል? በተለይ በክፍለ ከተማው ከጋራ መኖሪያ ቤቶች
አያያዝ ጋር ሰፊ ክፍተት ታይቷል፡፡ ለማጥራት የተደረገው ትግል ምን ይመስላል?
አቶ ፍፁም፡- የኪራይ ሰብሳቢነት ትግሉ የተጀመረው በመሬት ነው፡፡ የመንግስትና የህዝብ ሀብት የሆነውን ውስን
መሬት የሚወረርበት ሁኔታ ነው የነበረው”” ከዚህ ተነስተን በተደራጀና በታቀደ መንገድ የማጥራት ስራ ለመስራት ጥረት አድርገናል፡ ፡ የቴክኒክ ኮሚቴ አቋቁመን
የህዝብ አደረጃጀቶችን በማሳተፍ የማጥራት ስራውን በተሻለ መንገድ ሰርተናል፡፡ ከዚህ ተነስተን ረዘም ያለ ጊዜ ወስደን 13 የሚሆኑ
ፈፃሚዎችንና አራት አመራሮችን በህግ እንዲጠየቁ አድርገናል፡፡ ከ60 በላይ የሚሆኑ የወረዳና ክፍለ ከተማ አመራሮችም ህዝቡን ያማረሩና
ተጨባጭ መረጃ የተገኘባቸውን ከተቋሙ እንዲወጡ አድርገናል፡፡ ይህንንም በማድረጋችን ህዝቡ ደስተኛ ሆኖ አብሮን ለመስራት ቃል በመግባት
እየጠቆመንም ይገኛል፡፡ እገሌ ቀርቷል ለምን አላያችሁም በሚል በስም ሳይቀር እየጠቀሰ መጠየቅና ጥቆማ መስጠት ጀምሯል፡፡
ከቤቶች ጋር በተያያዘም በርካታ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ክፍት ሆነው እንደቆዩ ከመጀመሪያው እናውቃለን፡፡ በክፍለ
ከተማችንም ከአንድ ሺህ በላይ ቤቶች እንደሚገኙ መረጃውን ለሚመለከተው ቆጠራው ከመደረጉ በፊት ሰጥተናል፡፡ በከተማችን በርካታ የጋራ
መኖሪያ ቤቶች ከሚገኙባቸው ክፍለ ከተሞች አንደኛው የኛ ክፍለ ከተማ ነው፡፡ 18 ሳይቶች የሚገኙ ሲሆን 33 ሺህ 55 ቤቶች ይገኛሉ፡፡
ከዚህ ውስጥ ዘመናዊ በሆነና ከከተማ በወረደው አቅጣጫ መሰረት 32 ሺህ 422 ተቆጥሮ ወደ መረጃ ቋት ገብቷል፡፡
በተለያየ መንገድ 483 ቤቶች ሳይቆጠሩ ቀርተዋል ተለይተዋልም”” ባጠቃላይ ካሉን ቤቶች ውስጥ ግን 113 ያህሉ ሊታሸጉ የሚገባቸው ናቸው፡፡ 1 ሺህ 861 ያህሉ
ለረጅም ጊዜ ሰው ሳይገባባቸው ክፍት ሆነው ቆይተዋል፡፡ 150 አባዎራዎች የጋራ መኖሪያ ቤት ወስደው የቀበሌ ቤት ሳያስረክቡ አግኝተናቸዋል፡፡
በቆጠራው ላይም በርካታ ችግር አግኝተናል፡፡ ግለሰቦች ከሚኖሩበት ቤት ጎን ክፍት ሲያገኙ ቀላቅለው አንድ አድርገው መኖር፣ መንግስት
ለጤና ባለሙያዎች በኪራይ እንዲኖሩበት የሰጣቸውን የጋራ መኖሪያ ቤት ለሌላ ሶስተኛ ወገን አከራይተው አግኝተናል፣ የመኖሪያን ለንግድ፣
የንግድ ቤቱን ለመኖሪያ አድርገው አግኝተናል””
ስለዚህ በህገ ወጥ መንገድ ይዘው ሲጠቀሙበት ያገኘናቸው ቁጥራቸው
ቀላል አይደለም፡፡ እኛም ከዚህ ተነስተን በህገ ወጥ መንገድ የተያዙትን አስለቅቀን ዘጠኝ ያህል ግለሰቦችንም በህግ እንዲጠየቁ አድርገናል፡፡
ተላልፎላቸው
ቁልፍም ተሰጥቷቸው ያልገቡበት 500 ያህል ቤቶችን አግኝተናል፡፡ ይሄ የመንግስት ችግር አይደለም፡፡ ከዚህ ቁጥር በላይ የሚሆኑ
ቤቶች ደግሞ ሳይተላለፉ ክፍት ሆነው እስካሁን መኖራቸውን አረጋግጠናል፡፡ ስለዚህ እነዚህን ቤቶች አሁን ላይ አሽገናል በቀጣይ በሚወጣ
እጣ ላይ አብሮ እንዲወጣ እናደርጋለን፡፡ ስለዚህ ከጋራ መኖሪያ ቤቶች ጋር ተያይዞ ሰፊ ክፍተት የነበረበት መሆኑን ለመለየት ተችሏል፡፡
የመኖሪያ ቤት ችግር ላለባቸውም ተላልፎ ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡
ህዳሴ፡-
ባጠቃላይ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ገብተው የተገኙ አመራሮችና ፈፃሚዎችን ተጠያቂ ከማድረግ አንፃር በተግባር የተሄደበት ርቀት ምን
ይመስላል?
አቶ
ፍፁም፡- አሁን ላይ ከአመራር አኳያ በተለይ በመሬት ማኔጅመንት ጽ/ቤት በተሳካ ሁኔታ ሄደንበታል፡፡ በርካታ አመራሮች በህግ እንዲጠየቁና
በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል””
በህግ እንዲጠየቁ ካደረግናቸው አመራሮች በመሬት ላይ ያሉትን
ብቻ አይደለም፡፡ በተለያዩ ሴክተሮች የሚገኙ የወረዳ አመራሮችም ይገኙበታል፡፡ በፈፃሚዎችም በኩል በርካታ ችግሮች ይነሱባቸው የነበሩ
ፈፃሚዎችን እስከ ሁለት ወር ደመወዝ መቅጣትና ከቦታቸው የማንሳት በሂደትም የሚጠየቁበትን ሁኔታ እየሰራን ነው፡፡ አሁን ላይ አሰራሩን
ጀምረነዋል አጠናክረን እንቀጥልበታለን፡፡
ህዳሴ፡-
አባላትና የህዝብ አደረጃጀቶች በመልካም አስተዳደርና በኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች ላይ የነበራቸው ድርሻ እንዴት ይገለፃል? ለመፍትሄው
እያደረጉት ያለው ግንባር ቀደም ተሳትፎስ?
አቶ ፍፁም፡- በአደረጃጀቶች ዙሪያ ከፍተኛ ለውጥ አለ፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻለ አቋም ላይ ነው የሚገኙ፡፡ በተለይ የሴቶች ማህበርና ፎረሞች ክፍለ ከተማችን የማስፋፊያ አካባቢ በመሆኑ
ችግሮች ሲኖሩ ይጠቁማሉ፡፡ በተለይም በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤቶች ጠንካራ የሆኑ ቋሚ ኮሚቴዎች ስላሏቸው በየአካባቢያቸው የሚያዩአቸውን
ችግሮቸ በመተጋገል እንዲቀረፍ ግብረ መልስ በመስጠት የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ ነው፡፡
በአንፃሩም በህገ ወጥ መሬት ወረራ ላይ በተግባር ገብተው
የሚገኙም የህዝብ አደረጃጀት እና አባላትም አሉ፡፡ ከአጠቃላይ መዋቅራችን አንፃር ሲታይ ግን ጥቂት ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ከአደረጃጀት
አደረጃጀት የተለያየ አፈፃፀም ቢኖራቸውም አሁን ላይ የተሻለ መነቃቃትና ወደ ተግባር እየገቡ ይገኛሉ፡፡ በተለይ በክፍለ ከተማችን
የነጋዴዎች ፎረም ጠንካራና ህገ ወጥ ንግድን በመታገል እያደረገ ያለው ጥረት አበረታች ነው፡፡
ህዳሴ፡- ሁሉም እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች ቀጣይነት እንዲኖራቸውና
ወደኋለ እንዳይቀለበሱ ለማድረግ ምን ታቅዷል?
አቶ ፍፁም፡- መንግስታችን በግልፅ ያስቀመጠው ጉዳይ አለ”” በእያንዳንዱ መድረክ ህዝቡ ያሳየው ተሳትፎ የራሱን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን አረጋግጠናል፡፡
ከዚህ በፊት የመንግስት ድርሻ ብቻ ነበር የሚባለው፡፡ አሁን ላይ ግን ህዝቡ የኔ ድርሻ ይሄ ነው መንግስት ደግሞ ይህንን ማድረግ
አለበት በማለት መሞገት ጀምሯል፡፡ አሁን በጋራ ሆነን እያስመዘገብነው ያለው የልማትና የመልካም አስተዳደር ስኬቶች አሉ፡፡ እነዚህን
ስኬቶች ለማስቀጠል ቀጣይነት ያለው መድረክ ይጠይቃል፡፡ እኛም ይህንን በየወሩ የእንጠያየቅ መድረክ እያዘጋጀን አደረጃጀቶች፣ ህዝቡ፣
ግለሰቦችና መንግስት ምን ምን ስራ ሰሩ፡፡ ያልተሰራው ስራስ ምንድን ነው፡፡ ለምን አልተሰራም፡፡ በሚል ህገ ወጥ ግንባታው፣ ንግዱ
አጠቃላይ ኪራይ ሰብሳቢውና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች በህዝቡ ውስጥ ስለሚሰሩ የተጀመረውን ልማትና የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ወደኋላ
እንዳይመለስ መንግስት ድርጅትና ህዝቡ በጋራ ለመስራት ከህዝቡ ጋር መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡ አሁንም እያደረግን እንገኛለን፡፡
ስለዚህ ከዚህ አኳያ ሲታይ ከእቅድ ጀምሮ እስከአፈፃፀም ድረስ የተሳካ ስራ እየሰራን ነው፡፡
ህዳሴ፡- በልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ላይ የክፍለ
ከተማው ነዋሪ ድርሻ እንዴት ነበር? በቀጣይስ በምን መልኩ መቀጠል አለበት ይላሉ?
አቶ ፍፁም፡- ጅምሩ በጣም ጥሩና ተስፋ ያለው ነው፡፡ በክፍለ
ከተማችን ለምሳሌ በህብረተሰብ ተሳትፎ ልማት ህብረተሰቡ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ በማዋጣት በርካታ የልማት ስራዎችን እየሰራ ነው፡፡
ልማት ማለት ይሄ ነው፡፡ ከዚህ በላይም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ በመልካም አስተዳደር ዙሪያም በመጀመሪያ ደረጃ ከራሱ ትግል
መጀመር አለበት፡፡ ነዋሪው አደረጃጀቱን ማጠናከር ከቻለ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት ይችላል፡፡
ህዳሴ፡- ህገ ወጥ የመሬት ወረራ በልማትና በህዝብ ጥቅም
ያሳደረው ጫና እንዴት ይገለፃል?
አቶ ፍፁም፡- በክፍለ ከተማችን ወደ 887 ሄክታር መሬት
ነፃ በማድረግ ከ50 ሺህ በላይ ቤቶችን ለመገንባት እቅድ ተይዟል”” ቤቶች
በሚሰሩበት አካባቢም ለአርሶ አደሩ ምትክ ቦታና ካሳ ተከፍሏል፡፡ ግን ደግሞ ቦታው በህገ ወጥ ግለሰቦች ተወርሯል”” ወደ አንድ መቶ ሄክታር ቦታ የሚይዝ ኢንዱስትሪም እኛው ክፍለ ከተማ ላይ ነው የሚሰራው፣ ከ20
ሄክታር በላይ በፈረንሳይ መንግስት እርዳታ የሚሰራ ዘመናዊ ቄራም እኛ ክፍለ ከተማ ላይ ነው፡፡ በርካታ ትላልቅ ፕሮጀክቶች በኛ
ክፍለ ከተማ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ያለ ሲሆን ነገር ግን መሬቱ በህገ ወጦች ተወርሯል”” ሁሉንም ሰፋሪ መኖሪያ ቤት ስለሌለው ነው የሚል ግምት የለንም”” በርካታ ባለሀብቶች መሬቱን ይዘው እስከ ጊዜው ሌላ ሰው እንዲኖርበት ያደረጉ አሉ፡፡ በሌላ
በኩል ደግሞ ምንም መጠለያ የሌላቸው ግለሰቦችም ሰፍረው ይገኛሉ፡፡ ለነዚህ ዜጎች ደግሞ መንግስት አማራጮች አስቀምጧል፡፡ በዝቅተኛ
ዋጋ የሚገነባ ቤት በመስራት በአነስተኛ ዋጋ በኪራይ እንዲጠቀሙ የተደረገው በሞዴልነት በንፋስ ሰልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ነው፡፡
ወደ አንድ መቶ ቤት ሰርተናል፡፡
እነዚህ
ቤቶች በከተማችን ለናሙና ተብለው በ20 ሚሊየን ብር ካፒታል አንድ መቶ ቤቶች ግንባታ አምና ተጀምሮ በቅርቡ 53 ቤቶችን ለተጠቃሚዎች
አስተላልፈናል፡፡ መንግስት ለሁሉም ዜጋ እኩል እይታና ተጠቃሚነቱን ለመጠበቅ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ መንግስት ለደሀ ከመቆሙ ውጭ
ሌላ አጀንዳ ስለሌለው ስለዚህ ይህን ተግባራዊ ማድረግ ተጀምሯል፡፡ ህዝቡም ከመንግስት ጎን በመሰለፍ የልማትና የመልካም አስተዳደር
ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እያደረገ ነው ሊቀጥልበት ይገባል፡፡
No comments:
Post a Comment