Monday, 2 May 2016

የግንፍሌ ፋኖሶች by zemen jundi


የቀትሩ አየር እጅጉን ፀሃያማ ነው፡፡ ከተወሰኑ እንቅስቃሴዎች በቀር ሁሉ ነገር ፀጥ ረጭ ብሏል፡፡ የግንፍሌ ማምረቻና ሰርቶ ማሳያ ቅጥር ግቢ በዝምታ ተውጧል፡፡ ይህ ቅጥር ግቢ ባለፉት 10 አመታት በከተማችን በመንግስት ከፍተኛ ወጪ ከተገነቡ 109 ማምረቻና ማሳያ ህንፃዎች መካከል አንዱነው፡፡ ጠንካራ ጥበቃ ይካሄድበታል፤ ዙሪያውም አስተማማኝ በሆነ የግንብ አጥር ተከቧል፡፡ ህንፃውን ከዚህ ቀደም ጎብኝተነዋል፡፡ ያኔ አብዛኛው የህንፃው ክፍሎች በተለያዩ የማኑፋክቸሪግ ዘርፍ በተሰማሩ አንቀሳቃሾች የተያዘና ስራ የጀመሩበት ነበር፡፡ ከዚህ ህንፃ ማዕድ ግሩም ሌዘርን፣ ፍሬህይወት አሰፋና ጋርመንትን የመሳሰሉ ውጤታማ አንቀሳቃሾችን የህይወት ተሞክሮ አቋድሰናችሁ ነበር”” በተመሳሳይ በህንፃው ላይ ክፍት የነበሩ እና በጊዜው ለስራ አጥ ወገኖች ያልተላለፉ ክፍሎችን በሚመለከትም በእንነጋገርበት አምዳችን በአሉታ መልኩ አንስተን እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ዛሬስ በምን አይነት ደረጃ ላይ ይገኛሉ፣ የሚለውን ለመመልከት ዳግም ጉዞአችንን ወደ ግንፍሌ ህንፃ የተለያዩ ክፍሎች አድርገናል፡፡
በግቢው ካሉ ህንፃዎች መካከል በአንዱ ህንፃ 4ኛ ፎቅ ላይ ተገኝተናል፡፡ ክፍሎቹ እንደከዚህ ቀደሙ ባዶአቸውን አይደሉም”” እጆቻቸው ስራ ያልፈቱ እረፍት አልባ በርካታ ወጣት ሴትና ወንድ፣ ጉልማሳ፣ በተለያዩ የእድሜ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰራተኞችን ይዘዋል፡፡ ጨርቅ የሚቀደድበትን መቀስ፣ ቁልፍ የሚበሳበትን የልበስ ማሽን፣ ዲዛይን የሚያወጣበትን እርሳስ፣ የልብስ መተኮሻ ማሽን የክር መደወሪያ መርፌ በእጃቸው ጨብጠዋል፡፡ ግሩም የኢንዱስትሪ ድባብ ተላብሷል፡፡ አንዱ የስራ ዘርፍ ሌላኛውን ይመግባል፤ ሁሉም ፊት ላይ ፍፁም የድካም ሰሜት አይታይም፡፡ ሰርተው አልጠገቡም፡፡ የድህነትን ፅልመት በላባቸው፣ በወዛቸው ታሪክ ሊያደርጉ ደፋ ቀና ማለታቸውን ተያይዘውታል፡፡ እኛም ባየነው ለውጥ እጅጉን እየተደሰትን መቅረፀ ድምፃችንን ዘረጋን፡፡
ቴዎድሮስ እንግዳወርቅ በቅርቡ ስራ ከጀመሩ አንቀሳቃሾች መካከል አንዱ ሲሆን “የምሪሉ ጋርመንትና ቴክስታይል” ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ነው፡፡ በ2001 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቴክኖሎጂ ፋኩሊቲ በሲቪል ምህንድስና ትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪውን ይዟል፡፡ ከምረቃ በኋላም በግዙፍ ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ ተቀጥሮ ሰርቷል፡፡ ለአብነትም በጊቤ 1 እና 3 ፕሮጀክቶች ላይ የጥራት ተቆጣጣሪ (Quality control engineer) ሆኖ ሰርቷል፡፡ ከዛም ከሱር ኮንስትራክሽን ጋር በተከዜ ድልድይ ግንባታ ላይ እስከ 12 ሺህ ብር ወርሃዊ ደሞዝ እየተከፈለው ሰርቷል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው እንግዲህ ለሰባት አመታት የሰራበትን የቅጥር ስራ እርግፍ አድርጎ የራሱን የግል ስራ ለመስራት የወሰነው፡፡ ሲያወጣና ሲያወርድ ሰንበቶ ለምን የምወደውን የጨርቃ ጨርቅ ስራ አልሰራም ሲል ጉዞውን ወደ ጥቃቅንና አነስተኛ አደረገ፡፡ ስራውን ከመጀመሩ በፊት የሲኦሲ ፈተና ማለፊያ ውጤት አስፈላጊ ነውና፣ ፈተናውን ወስዶ በአራዳ ክፍለ ከተማ የግንፍሌ ሼድ ውስጥ በነበረ ክፍት ቦታ ከደሞዙ ቆጥቦ በ42 ሺህ ብር ወጪ በገዛቸው አምስት የልብስ መስፊያ ማሽን ነበር ስራውን የጀመረው፡፡ የተለያዩ የጨርቃ ጨርቅ ምርት ውጤት የሆኑ ሸሚዞችን፤ ቲሸርቶችን ያመርታል”” ነገሮች ሁሉ በአንዴ እንዲህ አልጋ በአልጋ አልነበሩም የሚለው ቴዎድሮስ፤ ዛሬ ከራሱ አልፎ ለ10 ስራ አጥ ዜጎች ቋሚ የስራ እድል መፍጠር ችሏል፡፡
“የገበያ ትስስር እስኪፈጠርልኝ ቁጭ ብዬ አልጠበኩም፤ የገበያ ችግርም የለብኝም” ሲል ይገልፃል፡፡ ምርቶቹን ሀዋሳ ድረስ ሄዶ በመሸጥ ሰፊ ገበያን ፈጥሯል፡፡ “በግሌ ተከራይቼ ልስራ ብል ከ20 ሺህ ብር በታች የማላገኘውን የመስሪያ ቦታ በአንድ ማሽን 17 ብር ብቻ እየከፈልኩ መብራትና ውሃ እንደልቤ እየተጠቀምኩ መንግስት ባመቻቸልኝ እድል ተጠቅሜ እየሰራሁ ነው” ይላል፡፡
የህንፃው ምቹነት እና መብራት እና ውሃ የማይጠፋ መሆኑ ይበልጥ ለስራ የሚያነሳሳ ሆኖ እንዳገኘው ይናገራል፡፡ ቴዎድሮስ ልብ ውስጥ አንድ ነገር አለ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅቶ መስራት የሚፈጥረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የግዙፍ ፋብሪካ ባለቤትና ተወዳዳሪ ምርቶችን በማቅረብ አለም አቀፍ እውቅናን ማግኘት እንደሚፈልግ ነው የገለፀው፡፡ ለዚህም ይረዳው ዘንድ ቁጭ ብሎ የጥቃቅንና አነስተኛ ቢሮን ድጋፍ አልጠበቀም፡፡ በራሱ ጥረት መንገዱን አንድ ብሎ ጀምራል፡፡
ቶኒ ኢሊሚኑ ፋውንዴሽን ከተባለና መቀመጫውን ናይጄሪያ ካደረገ ተቋሞ የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት የሚያስችለውን መልካም አጋጣሚ መፍጠር ችላል፡፡ ተቋሙ በየአመቱ የተሻለ የስራ ፕላን ያላቸውንና በጥቃቅን ዘርፍ ለተደራጁ ወጣቶች የማበረታቻ ሽልማትና ነፃ የድህረ ገፅ ትምህርት እንዲያገኙ የሚያደርግ መንግስታዊ ያልሆነና በናይጄሪያዊ ባለሀብት የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡ ለተቋሙ ካመለከቱ 45 ሺህ አፍሪካውያን ወጣቶች መካከል ለመጨረሻው ዙር ከታጩ ወጣት ስራ ፈጣሪዎች አንዱ ለመሆን ችሏል፡፡ ለዚህም በጥቃቅንና አነስተኛ በተለይም በማኑፋክቸሪግ ዘርፍ መሰማራቱና ሀገራችን ለዘርፍ የሰጠችው ከፍተኛ ትኩረት በውድድሩ ላይ ተመራጭ እንዳደረገው ይገልፃል፡፡ ይህ ሁሉ በጎ ጅምር እንዲሁ ቤቱ ቁጭ ብሎ ሳይሆን የጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የፈጠረለት መልካም አጋጣሚ እንዲሆነ ነው የሚናገረው፡፡ የትኛውም ወጣት ትንሽ ብልሀትና ብዙ የስራ ፍቅር ይዞ ቢመጣ ጥቃቅን እና አነስተኛ የውቅያኖስ ያህል ተቀድቶ የማያልቅ መልካም ገፀ በረከት እንዳለው ይናገራል፡፡ ዛሬ ከ80 ሺህ ብር በላይ የደረሰው ሀብቱም ለዚህ ማሳያ እንደሆነ ነው ወጣቱ የሚገልፀው፡፡
የማኑፋክቸሪግ ዘርፍ በተለይም ጨርቃ ጨርቅ ብዙ ሊሰራበት ይችላል የምትለው የተቋሙ ስራ አስኪያጅ ምህረት ደብሩ ናት”” ወጣት ምህረት ከባህር ዳር ዩኒቨርስቲ በቴክስታይል ኢንጂነሪግ የመጀመሪያ ዲግሪ ምሩቅ ስትሆን በዚህ በቴዎድሮስ ጋርመንት ውስጥ የስራ እድል ከተፈጠራላቸው ሰራተኞች መካከል አንዷ ናት”” እሷም ወደፊት ልምድና ተሞክሮዋን ካዳበረች በኋላ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅታ ለመስራት ማቀዷን ነው የምትገልፀው፡፡
ጉብኝታችን አልተጠናቀቀም፡፡ እዛው ህንፃ ላይ የሚገኘው ሌላኛው ኢንተርፕራይዝ የመስፍን ማርታና ጓደኞቻቸው የሽርክና ማህበር አንዱ ነው፡፡ በ5 ሺህ ብር ካፒታል የጀመሩት ስራ ዛሬ የ12 ማሽን ባለቤት እንዳደረጋቸው ስራ አስኪያጁ መስፍን አበበ ይገልፃል፡፡ ከጥቃቅንና አነስተኛ ከሚያገኙት ድጋፍ በተጨማሪ ከአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም የሚያገኙት የማሽን ብድር ለስኬታቸው የጀርባ አጥንት እንደሆናቸው ይገልፃል፡፡ በቅርቡም ተጨማሪ 12 ማሽኖችን ጠይቀው ማሽኖቹን በእጃቸው ለማስገባት በሂደት ላይ ናቸው፡፡ መስከረም ላይ የጀመሩት ስራ ዛሬ ለ18 ዜጎች ቋሚ የስራ እድል መፍጠር አስችሏቸዋል፡፡
ከወረዳው እንዲሁም ከክፍለ ከተማው የጥቃቅንና አነስተኛ ባለሙያዎች የሚያገኙት ክትትልና ድጋፍ ውጤታማ እንዳደረጋቸውም ነው የሚናገረው፡፡ በየጊዜው የሚሰጣቸው የካይዘን ፍልስፍና ትምህርትም ስራቸውን የበለጠ ውጤታማና ከብክነት የፀዳ እንዳደረገው ይገልፃል፡፡ የግንፍሌ ፋኖሶች እነዚህ ብቻ አይደሉም ሄኖክና መሰረት የሹራብ ስራ ሽርክና ማህበር አንዱ ነው፡፡ ዛሬ 20 ቋሚ ሰራተኞች አሏቸው፡፡ በአንድ ማሽንና የልብስ መስፊያ ሲንጀር ከ10 ወራት በፊት የጀመሩት ስራ ዛሬ 700 ሺህ ብር ያህል ተቀማጭ ያለው ማህበር ባለቤት እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡ ሹራብ፣ ኮፊያ፣ የአንገት ልብስ ከምርቶቻቸው መካከል ይገኙበታል፡፡ በመንግስት ከሚደረግላቸው ድጋፍ መካከል ኤግዚቢሽንና ባዛር ምርታቸውን ለነጋዴና ለህብረተሰቡ በማስተዋወቅ ረገድ ጉልህ ድርሻ አለው ይላሉ፡፡ ጥራት ያላቸው ምርቶችን በኤግዚቢሽንና ባዛር ላይ ይዘን በመቅረብ ሰፊ የገበያ ትስስር እየፈጠርን ምርቶቻችንን እያስተዋወቅን ነው ይላሉ”” ወደፊት ምርቶቻቸው ከአገር ውስጥ አልፈው በአለም ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ይፈልጋሉ፡፡ ይህንን ለማሳካትም ከጨርቃ ጨርቅ ኢንስቲቲዩት የሚደረግላቸው ድጋፍ ከፍተኛ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
የስራ እድል ከተፈጠረላቸው በርካታ ወጣቶች በተጨማሪ አቅመ ደካሞችም በአቅማቸው የስራ እድል አግኝተዋል፡፡ ከዚህ መካከል አንዷ የሆኑት ወ/ሮ ለታይ ግርማይ ናቸው፡፡ ለሹራብ ስራ በጥሬ እቃነት የሚያገለግለውን ክር እየደወሩነበር ያገኘናቸው”” እንደወጣቶቹ ሁሉ ብርቱ የስራ መንፈስ ይታይባቸዋል፡፡ በሚያገኙት ገቢ ልጆቻቸውን ያስተምራሉ “የመስራት ፍላጎት ካለ ስራ ሞልቷል” የሚሉት ወይዘሮዋ ወላጆች ለልጆቻቸው ጥሩ የስራ ባህልን በማስተማር ረገድ ትልቅ ሃላፊነት አለባቸው ይላሉ፡፡ በመንግስት የተመቻቸውን ትልቅ አጋጣሚ ሊጠቀሙበት እንደሚገባም ነው የገለፁት፡፡
ወጣትነት ሮጠህ የማትደክምበት ጊዜ ነው የሚሉት ወ/ሮ ለታይ በወጣትነት ዘመኔ እንደ አሁኑ ወጣት ይህን አይነት እድል ባገኝ ዛሬ አንቱታን ያተረፍኩ ባለሀብት እሆን ነበር አሉን፡፡
ግንፍሌ ዛሬ በማያባራ ለውጥ ላይ ይገኛል፡፡ የማይሰሩ እጆች አይታዩም፡፡ ሆኖም አሁንም ግን ዛሬም ከ100 በላይ ስራ አጦችን ሊይዝ የሚችል 450 ካሬ ሜትር ክፍት ቦታ እንዳለ ተመልክተናል”” ይህ ክፍት ቦታ መፃኢ እጣ ፋንታው ምንድነው ስንል ለክፍለ ከተማው የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ሽመልስ ታምራት ጥያቄያችንን አቀረብን፡፡
ሃላፊው ክፍት ቦታው መፍትሄ ተበጅቶለታል ይላሉ፡፡ ይህም በቅርቡ ከዩኒቨርስቲና ቴክኒክና ሙያ ተመርቀው ስራ ያልጀመሩ ወጣቶችን ልናሰማራበት ቅድመ ሁኔታዎችን ጨርሰናል ነው ያሉት፡፡ ክፍለ ከተማው በዘንድሮው አመት ብቻ ለ13 ሺህ 500 ስራ አጦች የስራ እድል መፍጠር ችሏል የሚሉት ሃላፊው በቅርቡ ወደ ስራ ለሚገቡ ስራ አጦችም በወረዳ 7 ሳንፎርድ ትምህርት ቤት አካባቢ ዘመናዊ ህንፃ ተገንብቶ በመጠናቀቅ ላይ ነው ብለዋል፡፡
220 የሚደርሱ ኢንተርፕራይዞችን የያዘው ግንፍሌ የማምረቻ ማዕከል ሌላም መልካም ነገር ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ ይህም የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ እዛው ቅጥር ገቢ ውስጥ እንዲያገኙ ብርሃን ኢትዮeያ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋም ስራውን ሊጀምር የማሽን ተከላና ሌሎች ስራዎችን እያጠናቀቀ ነው፡፡
ይህ ደግሞ የበለጠ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠሩ በተጨማሪ ኢንተርፕራይዞቹ በምርት ማምረት ሂደት ውስጥ የሚያጋጥማቸውን የክህሎት ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈቱ የሚያስችል ፍቱሁን መድሀኒት ነው፡፡ በኢንተርፕራይዞቹ መካከል ያለው የእርስ በእርስ መመጋገቡም የበለጠ ውጤታማ ይሆናል”” በተመለከትነው ለውጥ እጅጉን ተደስተናል፡፡ እኛም ግንፍሌን ወደኋላትተን ተሰናብተን ወጥተናል፡፡ ነገ ደግሞ ከዚህ የበለጠ ውጤት አፍርቶ የግምባር ቀደም ኢንተርፕራይዞች መና¡ሪያ፤ የልማታዊ ባለሀብቶች መፈልፈያ ሆኖ እንደምናገኘው ያለን ተስፋ እጅጉን ትልቅ ነው፡፡
በአጠቃላይ በከተማችን ባለፉት 8 ወራት ጊዜ ውስጥ ከጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ስራዎች ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ረገድ በቢሮው በኩል ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ እንደቢሮው መረጃ መሰረት ከዚህ ቀደም ተደራጅተው ስራ ካልጀመሩ 271 ኢንተርፕራዞች መካከል 214 የሚሆኑት በቀጥታ ስራ እንዲጀምሩ ተደርጓል፡፡ የሚያጋጥማቸው የገበያ ችግር ለመቅረፍም የ2 ቢሊዮን 224 ሚሊዮን 669 ሺህ 289 ብር የገበያ ትስስርም እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ቢሮው የ2 ቢሊዮን 61 ሚሊዮን 267 ሺህ 58 ብር የብድር አቅርቦትም በማቅረብ ያለባቸውን የፋይናንስ አቅም በመቅረፍ ይበልጥ ኢንተርፕራይዞቹ ወደፊት እንዲጓዙ፤ አቅም እንዲገነቡ ተደርጓል፡፡ በተወዳዳሪነት፤ በምርት ጥራትና ውጤታማነት ላይ ያለውን የክህሎት ችግር ለመቅረፍም ለ3 ሺህ 403 አዲስና ነባር ኢንተርፕራይዞች የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍና ክትትል እንዲያገኙ አስችሏል፡፡
በተጨማሪም በሼዶች ልማትና አስተዳደር ላይ የነበረውን ችግር በመቅረፍ በኩልም የጥቃቅንና አነስተኛ ልማት ቢሮ መልካም ጅማሬ ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ ቀደም ስራ ላይ ያልዋሉና 1 ሺህ 100 አንቀሳቃሾችን ሊያሰማሩ የሚችሉ በተለያዩ የማምረቻና ማሳያ ህንፃዎች ላይ ያሉ ባዶ ስፍራዎችን በመለየት ለስራ አጦች አስተላለፏል፡፡ በሂደት ስራ እንዲጀምሩም አድርጓል፡፡ በአጠቃላይ ቢሮው በአመቱ ያስቀመጣቸውን ቁልፍ ግቦች እውን በማድረግ እና ያጋጥሙት የነበሩ ችግሮችን መቅረፍ የቻለበት መልካም አቋም ላይ እንደሚገኝ ያሳያል፡፡ ቻይናውያን አንድ አባባል አላቸው፡፡ “100 ሚልዮን ቻይናውያን በድህነት ላይ ሆነው ማንም ቻይናዊ ለእንቅልፍ ዓይኑ አይጨፈንም” ይላሉ፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ በርካታ መቶ ሺህ ዜጎች በጥቃቅንና አነስተኛ ፕሮግራም ወደስራ እንዲገቡና ድህነትን መቅረፍ እንዲችሉ እየተደረገ ቢሆንም አሁንም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስራ አጥ ነዋሪዎች መፍትሄ ይጠብቃሉ”” ስለሆነም እስካሁን የተሰራው የሚያበረታታ ቢሆንም ለእንቅልፍ አይን የሚያስጨፍን አይደለምና ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡

No comments:

Post a Comment