Wednesday, 11 May 2016

መሪ ፕላን፤ፍኖተ ህዳሴ



ከተማችን አዲስ አበባ ከተቆረቆረች 130 አመታት ሆኗታል”” ከዛሬ 10 አመት በፊት በሀገራችን በከተሞች ከሚኖሩ ዜጎች ቁጥር 25 በመቶው ያህሉ የሚኖሩት በአዲስ አበባ ነበር፡፡ ባለፉት አመታት የክልል ከተሞችና የዞን ከተሞች እያደጉ በመምጣታቸው ዛሬ በአዲስ
አበባ የሚኖረው ዜጋ ከአጠቃላይ በከተሞች ከሚኖረው ዝቅ ብሎ 19 በመቶ ሆኗል፡፡ ይህ ድርሻ በየጊዜው ቀንሶ በ2032 ወደ 9 በመቶ ይወርዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይሁን እንጂ አዲስ አባባ የሚኖርባት እየቀነሰ ቢሄድም የከተማው ቋሚ ነዋሪ ህዝብ ግን ወደ 6 ነጥብ 6 ሚሊዮን እንደሚያድግ ጥናቶች ይተነቢያሉ”” በመሆኑም ከተማዋ እጅግ ዘመናዊ በሆነ መሪ ፕላን ካልተመራች ለተጠቀሰው ህዝብ መኖሪያ ሰጥታ፣ በትራንስፖርት አስተናግዳ፣ ጤናውን ተንከባክባ፣ የማያቋርጥ የስራ እድል ፈጥራ መሸከም አትችልም፡፡ በመሆኑም አሁን በልማት ጉዟችን እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎችን ለመፍታት ብቻ ሳይሆን ወደ ፊት የሚያጋጥማትን ሀገራዊና አለም አቀፋዊ ተፅእኖዎችን ለመቋቋም ከወዲሁ መዘጋጀት አለባት፡፡ መሪ ፕላን ማለት አንዲት ከተማ ያላትን የሰውሃይል፣ የተፈጥሮ ሃብትና ፋይናንስ አቅም አቀናጅታ ስትሰራ ከየት ተነስታ ወዴት እንደምታመራ የሚያመላክት መንገድ ወይም ፍኖት ማለት ነው፡፡ አዲስ አበባ ደግሞ ለትግበራው ባትታደልም ለወረቀት መሪ ፕላን ግን እንግዳ አይደለችም፡፡
እንደሚታወቀው ለአዲስ አበባ ከተማ ለዘጠነኛ ጊዜ የተዘጋጀው ማስተር ፕላን አሥረኛ ዓመት ተጠናቆ የመጠቀሚያ ጊዜው አብቅቷል”” ያለፈው ማስተር ፕላን የመጠቀሚያ ጊዜው በማለፉ ምክንያት አዲስ አበባ ከተማ የምትመራበትን ማስተር ፕላን ማዘጋጀት አስፈላጊ ነበር”” ነገር ግን የሁለቱም አስተዳደሮች አመራሮች የተለያዩ መለኪያዎችን ታሳቢ በማድረግ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል ከሚገኘው ልዩ ዞን ጋር የተቀናጀ ማስተር ፕላን እንዲዘጋጅ የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውሳኔ አሳልፎ ስራው እየተከናወነ እንደነበር ይታወቃል፡፡
ነገር ግን ማንኛውም የከተማ እድገት ካለ መሪ ፕላን የማይታሰብ በመሆኑ አዲስ አበባም ሆነች የኦሮሚያ ከተሞች /ሌሎች ከተሞችም በተመሳሳይ/ የሚመሩበት ፕላን ሊኖራቸው የግድ ነው፡፡ የከተማ መሪ ፕላን ትልቅም ሆነ ትንሽ ከተማ በመሆኗ አይወሰንም ከየት ተነስታ ወዴት እንዴት መጓዝ እንዳለባት የሚያመላክት ፍኖት በመሆኑ የግድ ያስፈልጋል፡፡ አዲስ አበባ የመጀመሪያ ማስተር ፕላን እንዲወጣላት የተደረገው ገና ነዋሪዎቿ 100 ሺህ በነበሩበት ዘመን ነው፡፡
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የአለም የከተሞች እድገት እንደሚያረጋግጠው ኩታ ገጠም ከተሞች እድገታቸውና ችግራቸው የተነጣጠለ አይደለም”” በመሆኑም አቀናጅቶ እድገታቸውን መምራት አስፈላጊ ነው የሚለው አስተሳሰብ አለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ነው፡፡ ይሁን እንጂ በተጨባጭ የኛ ሁኔታ በተለያየ ምክንያት በወሳኝነት በደካማ የህዝብ ግንኙነት ምክንያት የተቀናጀ መሪ ፕላኑ በኦሮሚያ ህዝብ ተቃውሞ ስላጋጠመው ድርጅታችን የህዝቡን ‹‹ይቁምልን›› ጥያቄ በመቀበል እንዲቆም ተደርጓል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማና በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞች የማቀናጀት ሃሳብ ከመጀመሪያ የነበረ ሳይሆን በኋላ የመጣ ነው፡፡ የመጀመሪያው እንቅስቃሴ የከተማው የ10 አመት መሪ ፕላን ጊዜው ስላበቃ ሌላ አዲስ መሪ ፕላን ለማዘጋጀት ነው የነበረው፡፡ ይህንን የሚሰራ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤትም ተከፍቶ እየሰራ ነበር፡፡ በመሆኑም ማቀናጀቱ ላይ ክፍተት ቢፈጠርም በትራንስፎርሜሽን ላይ ያለች ከተማ ለእድገቷ የሚመጥን መሪ ፕላን ሳይበጅላት መንደፋደፍ ለትውልዶች የሚተርፍ ዋጋ ስለሚያስከፍል የከተማው አስተዳደር አዲስ አበባ ከተማን ብቻ የሚመለከተውን መሪ ፕላን ከ2009 ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ወስኗል፡፡ ጥናቱም ተጠናቋል፡፡ከተማዋ የ1886 ‹‹የእቴጌ ጣይቱ የአሰፋፈር እቅድ›› ተብሎ በታሪክ ከሚታወቀው እቅድ ጀምሮ በተለያየ ወቅት ዘጠኝ የከተማዋን አከታተም የሚያመላክቱ ፕላኖች ወጥተውላታል፡፡ ከዚሁ ስምንቱ ሙሉ በሙሉ በውጪ ሃገር ሰዎች የተዘጋጁ ማስተር ፕላኖች ሲሆኑ ከተማዋ መሪ ፕላን አላት ከማለት ያለፈ ለከተማዋ እድገት መመሪያ ሆነው አገልግለዋል ሊባሉ የሚችሉ አይደሉም፡፡ ታሪክን ለማጣቀስ ያህል እኤአ በ1937 በጉዊደና ቫሌ/ Guidi and C. Valle/ የተዘጋጀው የመጀመሪያ ዘመናዊው መሪ ፕላን ተብሎ ይታወቃል”” ይህ በፋሽስት ጣሊያን ዘመን የወጣው ማስተር ፕላን ከተማዋን የአውሮጳውያን እና የሀገሬ ሰው መኖሪያ በሚል ከፋፍሎ አሰፋፈር የሚመለከት ያስቀምጣል፡፡
ቀጥሎም በ1956 በእውቁ የከተማ ፕላን ባለሙያ ፓትሪክ አበርኮምቢ የተዘጋጀ ሲሆን ከተማዋ በዙሪያዋ ሊኖሩ ከሚችሉ ትናንሽ ከተሞች ሊኖራት የሚገባ የመሰረተ ልማትና ኢኮኖሚ ቅንጅት ጭምር ያመላከተ መሆኑ ከፊተኞቹ የሚለየው ባህሪ ነበረው”” ቀጥሎ የመጣው የእንግሊዝያውያኑ ቦልተንና ሄልሲ በ1959 የተዘጋጀውና መሰረቱ የአበረኮምቢ ያደረገ ነው፡፡ ፕላኑ ከተማዋ ሊኖራት ስለሚገባት ቀለበት መንገድም ያመላከተ ነበር፡፡
የ1965ቱ ማስተር ፕላን ደግሞ በፈረንሳያዊው አርክቴክቸር በዲ.ማርዬን የተዘጋጀ ነው፡፡ የከተማው ማዘጋጃ ቤት እና የለገሀርን ባቡር ጣበያ የሚያስተሳስረው የቸርችል ጎዳና የተቀየሰው የዚህ ማስተር ፕላን ቱርፋት ነው፡፡ የከተማው ዩኒቨርስቲ ዛሬ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ባለበት እንዲሆን በፕላኑ ተመላክቶ እናገኘዋለን፡፡ የፊተኞቹን ማስተር ፕላን ያሻሻለው ደግሞ ፕሮፌሰር ፖሎኒ የተባለ ሲሆን ጊዜው በደርግ ዘመን ነው”” በፕላኑ የከተማና የገጠር ትስስርን ያመላከተ ሲሆን በአዲስ አበባ ዙሪያ ከተማ ያሉ ትናንሽ ከተሞች እንዴት መተሳሰር እንዳለባቸው ከማመላከት አልፎ እስከ አዳማ ከተማ ድረስ ሊኖር ስለሚገባ ሜጋሎፖሊስ እድገት መስመርም ያካተተ ነበር፡፡ በከተማዋ ዙሪያ እስከ 100 ኪሎሜትር ያሉት ከተሞችና ገጠሮች የሚያስተሳስሩ መንገዶችም በፕላኑ ተካቶ ነበር፡፡ እነዚህ የጠቀስናቸው ማሰተር ፕላኖች አንድም በአንድና ሁለት ባለሙያዎች ብቻ የተዘጋጁ መሆናቸው፣ በውጪ ሰዎች የተዘጋጁ መሆናቸው፣ ማስተር ፕላን ተሰርቷል ለማለት ያህል ካልሆነ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የህግ ማእቀፍ ያልወጣላቸውና የህግ ማእቀፉ ለማውጣት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እንዳልነበረ እንገነዘባለን፡፡ ማስተር ፕላኖቹ የ7ኛውንም ያህል ውስንነት ቢኖራቸውም የተግባር መመሪያ ቢደረጉ ኖሮ በተወሰነ መልኩም በከተማችን የተፈጠረው የተወሳሰበ አሰፋፈር፣ ደካማ የፍሳሽ ማስወገጃና የመንገድ ችግርን መቅረፍ ይቻል ነበር፡፡ በመሆኑም ከእነዚህ ማስተር ፕላኖች ትምህርት መውሰድ የሚቻለው ከምንም በላይ በመሪ ፕላን ለመመራት የሚያስችል የተቀየረ አስተሳሰብ ወሳኝ መሆኑ ነው፡፡ ሌላው ግን ከተማዋ ለማስተር ፕላን እንግዳ አለመሆኗን ነው፡፡
ኢትዮጵያውያንና የጣሊያን ባለሙያዎችም የከተማዋን 100ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በ1979 /እ. ኤ.አ 1986/ ሌላ ማስተር ፕላን ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ መሪ ፕላኑ ለየት የሚያደርገው ለመጀመሪያ ጊዜ 45 ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የተሳተፉበት መሆኑ ነው”” ማስተር ፕላኑ ከአርሲ ሸዋ ሪጂናል ፕላን ጋር እንዲተሳሰር የከተማዋ ቆዳ ስፋትም ቀስ በቀስ ወደ ምስራቅ፣ ደቡብና ምዕራብ እንደሚሰፋ አመላክቷል፡፡ የአዲስ አበባ መቶኛ አመትን አስመልክቶ በተዘጋጀ መፅሄት መጨረሻ ገፅ ላይ አንድ አስገራሚ ትንቢታዊ ቃል እናገኛለን፡፡
“In order to avoid the previous pitfall, it is necessary to enact it into law promptly, or else it will also be dubbed as the Master plan prepared during the Reign of the ‘Derg’ and its colorful maps hang on the walls of City Hall only for decorating purposes.”
በእርግጥም ፀሃፊው እንደተነበየው በደርግ ጊዜ ማስተር ፕላን ወጥቶ ነበር ከማለትና የማዘጋጃቤት ግድግዳ ማጌጫ ከመሆን ያለፈ ፋይዳ ሳይኖረው የቀረ ማስተር ፕላን ቢባል ማጋነን አይሆንም”” ከተማዋ አብዛኛው አቅሟ መንደሮችን በማፍረስ መልሶ ከተማ በመገንባት እንድትጠመድ ያደረገው ከነጉድለታቸውም ቢሆን ማስተር ፕላኖቹን የሚያስተገብር ህጋዊ ማእቀፍ ስላልወጣላቸውና የፖለቲካ ቁርጠኝነት ስላልነበረ ነው፡፡
በ1979 በኢትየጵያውያንና ጣሊያናውያን ባለሙያዎች በጋራ የተዘጋጀው መሪ ፕላን አንድ ትልቅ ያስቀመጠው ጉዳይ አዲስ አበባ 54 ሺህ ሄከታር ስፋት ያላት መሆኑ መወሰኑ ነው፡፡ በኋላም አጠቃላይ የሀገራችን የአስተዳደር አወቃቀር በተለወጠበት የፌደራል አወቃቀር የአዲስ አበባ ስፋት በደርግ ጊዜ የተወሰነውን ይዞ እንዲቀጥል ሆኖ የውስጥ የአስተዳደር አወቃቀሩ ብቻ ነው የተቀየረው፡፡ በእርግጥ አሁን ጥልቅ ልኬታ ሲደረግ ስፋቱ 54 ሺህ ሳይሆን 52 ሺህ ሄክታር ብቻ መሆኑ ተደርሶበታል፡፡
የ9ኛው መሪ ፕላን ቱርፋቶችና ጉድለቶች
ሌላውና ከየትኛውም መሪ ፕላን በተሻለ ስራ ላይ ውሏል የሚባለው በ1996 የወጣው ዘጠነኛው መሪ ፕላን ነው፡፡ መሪ ፕላኑ የከተማዋ ቀጣይ እድገት መሰረታዊ የሆኑ የመሰረተ ልማትን፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ የኢንዱስትሪ ዞኖችን፣ የባቡር ትራንስፖርትን ወዘተ ያመላከተ ነበር፡፡ እስከ ዛሬ በስራ ላይ ያለው የከተማ፣ የክፍለከተሞችና የወረዳዎች አወቃቀርም የዛ ማስተር ፕላን ቱርፋቶች ናቸው፡፡ ይሁንና የዘጠነኛው መሪ ፕላንም ቢሆን በጥብቅ ዲስፕሊን ሙሉ በሙሉ ተተግብሯል የሚባል አይደለም”” በተለያየ የአመራር ደረጃ ባለው አመራር መሪ ፕላኑ የሚጥሱ በርካታ ስህተቶችና በፕላን እርማት ስም መሪ ፕላኑን የሚጎዱ ተግባራት ተፈፅመዋል፡፡ በከተማችን መሪ ፕላኑን የሚጥሱ በርካታ የግል ባለሃብትና የመንግስት ተቋማት ግንባታዎች ተከናውነዋል፡፡ እጅግ ሰፋፊ የአረንጋዴ ቦታዎችና የወንዝ ዳርቻዎች ላይ ሰዎች በህገ ወጥ መንገድ ሰፍረውባቸዋል”” ማስተር ፕላኑ ጠንካራ የተቋማት ቅንጅታዊ ትስስር መሆኑን በመዘንጋት አንዱ የገነባውን ሌላው እያፈረሰ፣ አንዱ ያስዋበውን ሌላው እያቆሸሸ፣ አንዱ ያስከበረውን ሌላው እየጣሰ የሚውልበት ከተማዋ ከነበረችበት አዙሪት እንዳትወጣ አሉታዊ አስተዋፅኦ የሚያሳርፉ ተግባራት አሁንም ቀጥለዋል፡፡
በመሪ ፕላን የሚመራ አመለካከት መፍጠር
ከዚህ እውነታ መረዳት የሚቻለውና 10ኛውን መሪ ፕላን ለመተግበር ትምህርት የሚሆነው ዋናው መተግበሪያ መሳሪያ የሰው አእምሮ ላይ መፈጠር ያለበት አስተሳሰብ እንጂ የወረቀት ፕላን የመኖር እና አለመኖር ብቻ እንዳልሆነ ነው፡፡ በሰው አእምሮ ላይ ኢንቨስት ማድረግ ይገባል፡፡ ማስተር ፕላኑን ለጊዚያዊ ግላዊ ጥቅም ሲባል መጣስ በቀጣይ ትውልዶች ላይ የሚፈፀም ትልቅ ወንጀል መሆኑን አስፈፃሚው፣ ህግ አውጪው፣ ህግ ተርጓሚውም ከምንም በላይ ደግሞ ህብረተሰቡ ጠንካራ የተቃና አመለካከት እንዲይዝ ማድረግ ይገባል፡፡ በአስተሳሰብ ላይ የሚካሄደው ግንባታ በማንኛውም መልኩ የማይተካ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ መሪ ፕላኑ ሙሉ ለሙሉ እንዲተገበር ደግሞ በባለቤትነት የሚያስፈፅሙ ተቋማትና ህጎች መኖር እንዳለባቸው በመሪ ፕላኑ ተቀምጧል፡፡ የግንባታ ፈቃድ መመሪያን በጥብቅ መፈፀም ይገባል፣ የህንፃ ከፍታ ህግ እና የህንፃ ኮድ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል”” ከተቋማት አንፃርም የከተማ ፕላን ኮሚሽን፣ የትራንስፖርት ኮሪደር፣የማዕከላትና ገበያ ልማት የአስተዳደር ኮርፖሬሽን፣ የልማት ማስተባበሪያ፣ የግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን እና የተፋሰስ፣ አረንጓዴ፣ ወንዞች ዳርቻና ፓርኮች ልማት ኤጀንሲን ማቋቋም አስፈላጊ መሆኑን ማስተር ፕላኑ አስምሮበታል፡፡
አዲስ አበባ የተቀናጀና ሁሉን አቀፍ የከተማ ልማት ፕላን ሳይኖራት በዘፈቀደ ያደገች ከተማ ነች፡፡ በመሆኑም የሚበዙት ቤቶቿ ያለፈቃድ በግለሰቦች ውሳኔና ፍላጎት የተገነቡ ናቸው ስንል ከፍ ብሎ እንደተጠቀሰው የግድግዳ ማስዋቢያ ሆነው የቀሩት የከተማ ንድፎችና ካርታዎች አልነበሯትም ማለት አይደለም፡፡ እነዚህ መሪ ፕላኖች ግን የፈፃሚውም የነዋሪውም መመሪያ ሆነው አላገለገሉም፡፡ አንድ መሰረታዊ ነጥብ ብናነሳ በሁሉም መሪ ፕላኖች ላይ አዲስ አበባ ሰፊ የአረንጓዴ ስፍራና መዝናኛ ፓርኮች እንዲኖራት አመላክቷል፡፡ አካሄዳችን ግን ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ይህ አስተሳሰብ ዛሬም አለቅ ብሎን ህገወጥ ግንባታ የከተማዋ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በተለይም በነባር የከተማዋ ክፍል የተከማመሩ፣ የተፋፈጉ ቤቶችና መንደሮች ሰው ሞቶ አስክሬን ማውጣት የማይቻልበት፣ የእሳት አደጋ ቢያጋጥም የአደጋ ተከላካይ ባለሙያዎች ዘልቀው ውሃ መርጨት የማይችሉባቸው ናቸው፡፡ የሁሉም የሆነ የማንም አይደለም በሚል እጅግ አውዳሚ አስተሳሰብ የጋራ የሆነውን መሬት በመውረር ከማስተር ፕላኑ ጋር በሚቃረን መልኩ አገልግሎት ላይ እየዋሉ ቀጥለዋል፡፡ ዛሬም የከተማው አስተዳደር የሰነድ አልባ ጉዳይ ተመልሶ የመልካም አስተዳደር ችግርና አንድ ትልቅ የአገልገሎት ስራ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
የ10ኛው መሪ ፕላን ተልእኮና መሰረታዊ የእድገትና የልማት ምሰሶዎች
መሪ ፕላኑ መሰረታዊ የእድገትና የልማት ተልእኮ አለው ሲባል አንደኛው ፕላኑ መሰረታዊ ለውጥ አምጪ(Transformational/ Structural Change) መሆኑ ነው፡፡ ይህም ማለት ከዚህ በፊት በነበረው የከተማው እድገት መንገድ በነበረው ብቻ የሚያስቀጥል ሳይሆን አዲስና ከአጠቃላይ ሀገራዊ ራእይ ልንደርስበት የሚገባ ግብን ለመድረስ የምንመራበት ፍኖት ነው፡፡ እንደሚታወቀው እንደ ሀገር አንድ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ማህበረሰብ የመፍጠር ህገ መንግስታዊ ራእይ አለን፡፡ ይህ ማለት በሀገሪቱ ያለው ጉልበት፣ሃብትና ካፒታል በተጣመረና በተሳሰረ አቅጣጫ እንዲንቀሳቀስ፣ እንዲጎለብትና የበለፀገ ህብረተሰብ መፍጠር ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከየትኛውም የሀገራችን ክፍል በላይ የሀገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሁሉም የሚገኙባት አዲስ አበባ በዘርና በሃይማኖት ሳይለያይ በጠንካራ ኢኮኖሚ በመተሳሰር ልዩነትን ፀጋ እንጂ እርግማን እንደማይሆን ለአለም ህዝብ የሚያረጋግጥበት ነው፡፡ በመሆኑም በመሪ ፕላኑ የሚካሄዱ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ከየትኛውም የሀገሪቱ ብሄር ብሄረሰቦች ለመጡ ዜጎች ያለ አድልዎ የሚያስተናግዱ መሆናቸውን የማረጋገጥ ተልእኮ ይኖረዋል ማለት ነው፡፡
በበርካታ ሀገራት በሀገራችንም ጭምር ስለከተሞች ልማት ሲታሰብ ስለአገልግሎት መስጫ ተቋማት ህንፃ እና የመኪኖች መንገድ ቅድሚያ ሰጥቶ የሚመራ አስተሳሰብ ነው፡፡ በተመሳሳይ ከተሞች የሚለሙት በመንግስትና ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ በመመደብ ነው የሚለው አስተሳሰብም ገዢ ነው፡፡ መሪ ፕላኑ ግን እቅዱም ይሁን ከተማው በመገንባት ቅድሚያ መውሰድ ያለበት የሰው ልጅ ነው ይላል፡፡ ህዝብ ዋነኛ የልማት ሃይል ነው የሚለው ሌላው የመሪ ፕላኑ መሰረታዊ ምሰሶ ነው፡፡ በመሆኑም ለነዋሪዎቿ ጤንነትና አኗኗር የተመቸች ከተማን እውን ለማድረግ መንገዶችን ለእግረኛ ነዋሪ እንቅስቃሴ ምቹ፣ ወንዞችን የንፁህ አየር ምንጭ ማድረግ፣ የከተማውን 30 በመቶ በአረንጓዴ ልማት እንዲሸፈን ማድረግ ይገባል፡፡ 30 በመቶ ለመንገድ ሲሆን 40 በመቶ ደግሞ ለመኖሪያና ለኢንዱስትሪና ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፍ ግንባታዎች እንዲውል ይደረጋል፡፡
ማስተር ፕላኑ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ለማሳካት ለከተሞች የተሰጠውን ሚና የሚያሳይ በመሆኑ፣ ከሕገ መንግሥታዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ባሻገር የዜጐችን ሕይወት በአፋጣኝ ለመቀየር ከሚደረገው ጥረት ጋር ማየት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡ ማስተር ፕላኑ የአዲስ አበባን ነዋሪዎች ሕይወት ለመለወጥ እንደ ትልቅ መሣሪያ የሚያገለግል ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2025 በአፍሪካ ካሉ ምርጥ አሥር የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ውስጥ አንዷ እንድትሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2040 ደግሞ ከአምስቱ ምርጥ የቱሪስት መዳረሻ የአለም ቦታዎች አንዷ ለመሆን የተያዘውን ራእይ ለማሳካት እንደመሳሪያ የሚያገለግል ፍኖተ ካርታ ነው፡፡ በሌላ አገላለፅ የህዳሴያችን ፍኖት ነው፡፡ ይህንን ወርቃማ፣ የከተማችን የህዳሴ ጉዞ ለማፋጠን የሚያገለግል መሳሪያ፣ የከተማው ነዋሪ የመኖሪያ ቤቶች ልማት፣ የመንገድና ትራንስፖርት፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ የውሃ አቅርቦትና የደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ አወጋገድን ይበልጥ ለማዘመን፣ ወንዞቻችን የበሽታ ማመንጫ ሳይሆኑ ንፁህ ውሃ የሚፈስባቸውና ነዋሪዎች የሚዝናኑባቸው ለማድረግ መንግስታችን ያነገበውን ትልቅ ህዝባዊ ራእይ በሚቃረን መልኩ በማስተር ፕላኑ ላይ የሚንፀባረቁ አፍራሽ እና ጎታች አመለካከቶችን በሚገባ ልንታገላቸው ይገባል፡፡

No comments:

Post a Comment