Friday, 1 April 2016

ውበትሽ ውበትሽ፣ የአባይ ልጅነትሽ!


በኩር፡- መጋቢት 23 ቀን 2008 ዓ.ም (ባሕር ዳር)፡ ስለ እርሱ ብዙ ተብሎለታል፣ ተዚሞለታል፣ ተገጥሞለታል:: “ማደሪያ የሌለው…” ሲሉም ባይተዋርነቱን ገልፀውታል፤ የኢትዮጵያችን ሀብት የሆነው ነገር ግን ለበርካታ ዘመናት ህዝቦቿን የበይ ተመልካች ያደረገው- አባይ:: ከሀገራችን ጠራርጐ የሚወስደውን ለም አፈር በመቀበል ግብርናን የምጣኔ ኃብታቸው የጀርባ አጥንት ያደረጉት ሀገራትን መጥቀሱ ብቻ አባባላችንን ያጠናክረዋል::
እናም ‘የበይ ተመልካችነት ይብቃ፣ የአባይ ባይተዋርነት ይቁም’ በሚል የህዳሴው ግድብ ግንባታ ብስራት ከተነገረ አምስት ዓመታት ተቆጠሩ::
የህዳሴው ግድብ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ስሜት የኮረኮረ፣ በአንድ አይነት ቋንቋ እንዲናገር ያደረገ የህዝብ የዘወትር ፍላጐትና ምኞት ነው::
የአባይ ነገር የኢትዮጵያውያን የዘመናት ቁጭት በመሆኑ የሀገሪቱን ኪነ ጥበብም እንዲቆዝም አድርጐት ቆይቷል::
አባይ…. አባይ …. አባይ… አባይ፣
የሀገር አድባር የሀገር ሲሳይ::
ያለ ሀገሩ ዘምሮ፣
ያለቅኝት ከርክሮ፣
አባይ ያለ አሻራ ኑሮ::
ሲሉም ድምፃውያን እንጉርጉሯቸውን በጋራ አሰምተውናል:: እኛም ይህንኑ ለዘመናት አዚመነዋል:: በእርግጥም አባይ የኢትዮጵያችን አድባር፣ ነገር ግን በተሳሳተ ቅኝት፣ በየዋህ ወለድ ግዞት እናቱን ትቶ የሌሎች ሲሳይ ሆኗልና:: ብቻ ሁሉም አባይን የተመለከቱ የጥበብ ቅኝቶች የአባይን ግዞተኛነት የሚያንፀባርቁ ነበሩ::
አባያዊ የሙዚቃ ቅኝት ቁጭት የወለደው ብሶት ነበር:: የሀገሬው ህዝብም አባያችን የሌሎች ሀገራት ሲሳይ መሆኑ ሆድ ቢያስብሰው፣ የአባይ ባይተዋርነት ቢያስከፋው የልጆቹንና የልጅ ልጆቹን ስም በአባይ በመሰየም ቁጭቱንና ብሶቱን የተወጣሁ ሲመስለው ቆይቷል::
አባይ የወለደው ህመም፣ የአባይ ብሶት መቸ እዚህ ላይ ቆመና::
.
.
.
ግርማ ሞገስ
የሀገር ፀጋ የሀገር ልብስ
አ… ባይ
የበረሃው ሲሳይ…
ስትልም ዘመን የማይሽራት ድምፀ መረዋዋ እጅጋየሁ ሽባባው አዚማለታለች:: እርግጥም ነው አባያችን ግርማ ሞገሳችን ግን ደግሞ የእናቱን ድንግል ሀብት ለበረሃ ሲሳይ የዳረገ ግዞተኛ ነበር::
የሆድ ብሶቱን በተመረጡና ቅኔ ለበስ በሆኑ ስነ ቃሎች ስሜቱን መግለጽ የተካነው የሀገሬው አርሶ አደርም ለልጆቹና የልጅ ልጆቹ ስያሜ ከመስጠት ባለፈ፡-
እኔን ከፋኝ እንጅ አንተ ምን ጐሎብህ፣
አገር ቆርጦ የሚሄድ አባይ እያለልህ::
በማለት ማደሪያ የሌለው ግን ግንድ ይዞ ስለሚዞረው የበረሀው ሲሳይ ተዝቆ በማያልቀው የስነ ቃል ቅርስ ገልፆታል::
የአባይ የዋህነት ከልክ በላይ ሆኖ ሆድ ሲያብሰውም ተስፋ የቆረጠ በሚመስል ስሜት፡-
አባይ ወዲያ ማዶ የዘራሁት አዝመራ፣
አጫጁ ድርቡሽ ነው ሰብሳቢው አሞራ::
በማለት የሀገሬው አርሶ አደር ብሶቱን አውጥቶ ተናግሮለታል:: በእርግጥም ይህ በረኸኛና የበረሀ ሲሳይ “የእናቱ ጡት ነካሽ” ሲባል ቆይቷል:: በዚህም ከስራ በቀር ተንኮል የማያውቀውን ታታሪውን አርሶ አደር አንገቱን አስደፍቶት ቆይቷል:: እናም አባይ በትውልድ ሀገሩ… “የማያውቁት ሀገር አይናፍቅም” ተባለ::
ይሁን እንጅ አባይ የባዕድ ሲሳይ መሆን በቅቶት፣ “የማያውቁት ሀገር አይናፍቅም” የሚለውን ብሂል ሽሮ ‘መመለሱ አይቀርም’ በሚል ኪነ ጥበቡ አሻራ አስቀምጧል::
አባይ ነጋ ጠባ ሀብቱን ያፈሰዋል፣
ጭስ አልባው ነዳጅ ነው ብለው ምን ያንሰዋል::
.
.
.
ስትልም የባህል አቀንቃኟ ገነት ማስረሻ የወደፊቱን የአባያችን የቱሪዝም በረከት በሩቁ እንድናይ አድርጋናለች:: ሁሉም የሀገሬው ብሶተኛ የ”እንገነባዋለን!” ወኔ እንዲሰንቅ ራዕይ አሳይታናለች::
.
.
.
አባይ አንተ እያለህ ታላቁ ወንዛችን፣
መሳለቂያ አንሆንም በድህነታችን::
.
.
.
በማለት የመንፈስ ጥንካሬ በመሆን በሀብታችን የበይ ተመልካችነታችን ይበቃ ዘንድ አውጃለች:: “ሳያጡ መቸገር እስከ መቸ…?” እንድንልም ያስገደደን የጥበብ ውጤት ሆነ::
የሀገሩን ዳር ድንበር በማስከበርና የነፃነት ተምሳሌት በመሆን ምሳሌ የሆነው ሀገሬውም “አባይ ላይ ተስፋ መቁረጥ የለም!” በሚል ስሜቱን በስነ ቃል ተቀኝቶለታል::
አባይ ከፋው አሉኝ አባይ ለምን ይክፋው፣
ፋሽሽት ያስለቀቀ ጀግና ልጅ እያለው::
ጀብዱ መፈፀም የማይሳናቸው የኢትዮጵያ ልጆች ለተከፋውም ፈጥኖ ደራሽ ናቸውና “አባይ አትከፋም!” በማለት የአባይን ሆድ ብሶት ለመጋራትና ማደሪያውን ከእናቱ ጓዳ እንዲያደርግ ከጐኑ መሆናቸውን ከስነ ቃል አልፈው በተግባር ለመተርጐም ተነቃንቀዋል::
የጊዜ ተፈጥሯዊ ኡደት ቀጥሎ ቁጭት ሌላ የቁጭት ካባ እየደረበ፣ የአፍሪካውያን የነፃነት ተምሳሌት ኢትዮጵያውያን ከአቅም በላይ ታጋሽነታቸው ጣሪያ ደርሶ ስሜታቸውን በውስጥ መያዝ አቃታቸው “እስከመቼ የቁጭት ዜማ?” የዘወትር ጥያቄያቸውም ሆነ::
ለታሪክ ቀያሪዋ እለት መጋቢት 24/2003 ዓ.ም ምስጋና ይግባትና የ”እንገድበዋለን!” ብስራት ሲነገር የሁሉም ሠው የቆዬ ስሜት ዳር እስከ ዳር አስተጋባ:: የዓለም ታላላቅ የዜና ማሠራጫዎችም መነጋገሪያ ርዕስ ሆነ::
በእርግጥ ይህች የአርበኞች ምድር የዓለምን ቀልብ የሳበችው አሁን አይደለም:: አውሮፖውያን የአፍሪካን ድንግል ሀብት በቅኝ ግዛት ሲቀራመቱ በአልደፈርም ወኔ ዳር ድንበሯን ያላስደፈረች ሀገርም ናት:: የህዝቦቿን አንድነት፣ በሀገራቸው ጉዳይ አልደራደርም ባይነታቸውንም ለአውሮፓውያን ያስተማረች ምድር ናት::
ኢትዮጵያ ህዝቦቿ የጥቁር ህዝቦች መመኪያነታቸውንም ያስመሰከሩባት ሀገር ናት:: ዘመን የማይሽረው የአፍሪካ ህዝቦች የነፃነት መለከት የተደመጠበት የጥቁር ህዝቦች የድል አውድማ- አድዋ እናት ናት::
እነሆ ታሪክ ራሱን ደግሞ ያኔ በሀገር ዳር ድንበር ማስከበሩ የታዬው አርበኝነት ዛሬ በድሀነት ላይ የዘመቻው ችቦ ተለኮሰ::
የሙዚቃ ቅኝቱ፣ የህዝቡ ለልጆቹና የልጅ ልጆቹ ስም አወጣጡ ተቀየረ:: ሁሉም ነገር በህዳሴ የታጀበ ሆነ::
እንጉርጉሮ ይብቃ ይገባል ውዳሴ፣
ጉዞውን ጀምሯል አባይ ለህዳሴ::
.
.
.
ሲሉም ተተኪ ወጣት ድምፃውያን የሙዚቃ ቅኝታቸውን በማይሰለቸው የልጅነት ድምጽ አስደመጡን:: በኢትዮጵያ ዘንድ ሁሉም ነገር እንደሚቻልም ስንኞች አስደመጡ:: “ያለ ቅኝት ከርክሮ” የተባለለት አባይም ወደ ህዳሴ ጉዞ መጀመሩን አዜሙልን:: እነዚህ የጥበብ ልጆች ከእናት አባቶቻቸው የወረሱትን ውብ ኢትዮጵያዊ ባህል በመጠቀም፡-
ለእኛ ብቻ አላልንም ጥቅሙ የጋራ ነው፣
ወትሮም ባህላችን ተካፍሎ መብላት ነው::
.
. .
በማለት ለሌሎች ሀገራት ያለንን አክብሮትና የጋራ ተጠቃሚነት አሳይተዋል::
የኢትዮጵያ ልጆች የዘመናት የአባይ ባይተዋርነት ቁጭትን ለማስቀረት በወኔ እና በአንድነት መንፈስ ከዳር ዳር ተነሱ:: እኛው በእኛው ጀምረን ለፍፃሜ እናበቃዋለን የሚል ስሜት አስተጋባ:: የአረንጓዴው ልማት አምባሳደርና ለየት ባለ የጥበብ አቀራረቡ የምናውቀው አርቲስት ስለሽ ደምሴም የህዝቡን ስሜትና አንድ ሆኖ መነሳት እንዲህ ገለፀው::
.
.
.
አባቱ ደጀን እናቱ ጣና፣
የኢትዮጵያ ልጆች መጡ እንደገና::
እናም የአባይ ጉዳይ የሁሉም አንደበቶች የመነጋገሪያ ርዕስ ሆነ::
ድምፀ መረዋዋ ፍቅርአዲስ ነቃጥበብና አርቲስት አበበ ብርሀኔም
ውበትህ ውበትህ፣
የአባይ ልጅነትህ::
.
.
.
.
ውበትሽ ውበትሽ፣
የአባይ ልጅነትሽ:: ሲሉም ተሞጋገሱበት::

የአባይ ቀደም ብሂሎች ተረት እስኪመስሉ ድረስ ቅኝታቸው ተቀየረ:: ከሊቅ እስከ ደቂቅ የአባይን አዲስ ቃል ኪዳን አስተጋበ:: ሁሉም በሚችለው “አባይን ለልማት” ዘመቻ አጠናክሮ ቀጠለ::
ውድ አንባብያን የአባይን “ድሮ እና ዘንድሮ” የጥበብ ቅኝት በዚህች አጭር ጽሑፍ ለመግለጽ መሞከር “አባይን በጭልፋ….” እንደማለት ነው:: በመሆኑም ሁሉንም የሀገሬውን ህዝብ ዳር እስከ ዳር ባነቃነቀው ከፀሀፊ ተውኔትና ገጣሚ ጌትነት እንዬው “አባይ ሐረግ ሆነ” ግጥም በተወሰዱ የስንኝ ቋጠሮዎች ጽሑፌን ላብቃ::
.
.
.
ሀገርን እንደ ልጓም በአንድ ልብ ያሰረ፣
ከእውነት የነጠረ ከእውቀት የጠጠረ፣
አባይ ሐረግ ሆነ ከደም የወፈረ::
እናም አደራህን ከእንግዲህ ሀገሬ፣
አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሶማሌ፣ ጉራጌ፣ አፋር ሆንክ ትግሬ፣
ወላይታ፣ ከፋ፣ ቤንሻንጉል፣ ኮንሶ፣ ጋምቤላ ሐረሬ::
አንተ የአንድ ወንዝ ልጅ ሁን፡-
ይሄን የአባይ ሐረግ ከእምነትህ ጋር ቋጥረህ፣
ከጋራ አንገት መድፋት ከጋራ መሳቀቅ ከጋራ ሀፍረት ወጥተህ፣
ከየዓለማቱ ጥግ በያለህበቱ በአንተነትህ ኮርተህ፣
በሙሉ የራስ እምነት አንገትህን አቅንተህ፣
ድምፅህን ከፍ አርገህ ደረትህን ነፍተህ፣
‘የአባይ ልጅ ነኝ እኔ ጦቢያ ናት ሀገሬ!’ በል አፍህን ሞልተህ::
ይሄው ነው ከእንግዲህ፣ የሠውነት ሞገስ ፀጋ በረከትህ፣
የትውልድ ኒሻን የእድሜ ሽልማትህ፣

2 comments:

  1. መልካም ትንታኔ ነው። ውበትሽ ውበትሽ የአባይ ልጅነትሽ ብሎ የዘፈነውን ብትነግሩኝ።

    ReplyDelete