Monday, 11 January 2016

ዘርፈ ብዙው የእፅዋት ማእከል!




ማዕከል የማቋቋም ስራ የተጀመረው እ.ኤ.አ በ1543 በጣሊያን ሀገር ነው፡፡ ጣልያን ሀገር የሚገኙ የፓድዎና የፒሳና ማዕከላት በእፅዋት ማዕከል ታሪክ አንጋፋ እንደሆኑ የተለያዩ ጥናቶቹ ያመላክታሉ፡፡ በእፅዋት ስብስቡና በሳይንሳዊ ይዞታው ተወዳዳሪ የማይገኝለት ግን እ.ኤ.አ በ1759 የተቋቋመው የእንግሊዙ ሮያል ኪው እጽዋት ማዕከል ነው፡፡
በአፍሪካም ዘመናዊ የእጽዋት ማዕከላት በ20ኛው ክፍለ ዘመን ማግስት እ.ኤ.አ በ1913 መቋቋም እንደጀመሩ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡ በአፍሪካ የእፅዋት ማዕከል ቀዳሚውና እድሜ ጠገቡ የደቡብ አፍሪካው ክሪስታን ቡሽ ብሔራዊ የእጽዋት ማዕከል ነው፡፡
ዘመናዊ የእጽዋት ማዕከላት እጽዋቶቹን ከመጥፋት አደጋና ስጋት በመከላከል ለምርምር፤ ለትምህርትና ለኢኮ ቱሪዝም ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፡፡ ዛሬ ላይ ከ130 የሚበልጡ ሀገራት የእጽዋት ማዕከላትን ጥቅም ጠንቅቀው በመረዳታቸው ከ2 ሺህ 500 በላይ መሠል የእጽዋት ማዕከላትን አቋቁመው ለመጥፋት የተቃረቡ እጽዋትን በማራባት ለአረንጓዴው ልማት መቀጣጠል የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ ይገኛሉ፡፡
መረጃዎች እንደሚነግሩን አውሮፓ 500 ማዕከላትን በመገንባት ቀዳሚ ናት፡፡ ሰሜን አሜሪካ 350፣ ኤሲያ 300፣ ማዕከላዊ ደቡብ አሜሪካ 200፣ እንዲሁም አውስትራሊያ 200 የእፅዋት ማዕከላት የገነቡ ሲሆን በአመት እነዚህን ማዕከላት ለመጐብኘት ከ150 ሚሊዮን በላይ ሰዎች እንደሚጐርፍ ከጉለሌ እጽዋት ማዕከል ያኘናቸው ሰነዶች ያረጋግጣሉ””
በአሁን ሰአት ከ20 ሺህ በላይ የእጽዋት ዝርያዎች ለመጥፋት በመቃረባቸው እንደዚህ አይነት የእጽዋት ማዕከላት ተቋቁመው እጽዋቱን ከመጥፋት አደጋ በመታደግና በመንከባከብ፣ በማባዛት ዝርያቸው ወደ ነበረበት ለመመለስ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ፡፡
በተለያዩ አጋጣሚዎችና በስነ ምህዳር መለዋወጥ ችግር ምክንያት ዝርያቸው የመጥፋት አደጋ የተጋረጠባቸውን እጽዋቶችንም ከተለያዩ አካባቢዎች በሣይንሳዊ መንገድ ሰብስቦ በማምጣትና በመንከባከብ ከጥፋት የመታደጊያ መንገድ ነው፡፡ በሀገራችንም ይህን መሰል ማዕከል ለማቋቋም ከ1970ዎቹ ጀምሮ በተያዩ አካላት ጥረቶች ቢደረጉም የአምባገነኑ የደርግ መንግስት ፋይዳውን በውል ባለመረዳቱ የእጽዋት ማዕከል ሳያቋቁም አልፏል፡፡
ከቅርብ አመታት ወደህ ግን የእጽዋት ማዕከል ግንባታና መሰል ስራዎች ከመስራት ባለፈ የአፍሪካ አንደበት በመሆን ለአረንጓዴ ልማት ስራ ጥብቅና የቆመችው ሀገራችን ዘመናዊ የእፅዋት ማዕከላትን መገንባት ጀምራለች፡፡
በሀገራችን የመጀመሪያ የሆነውም የጉለሌ እጽዋት ማዕከል ተቋቁሞ ወደ ስራ ተገብቷል፡፡ ይህ ማዕከል በከተማው ነዋሪዎች፣ ተማሪዎች፣ ሙሁራንና የውጭ ቱሪስቶች መጎብኘት ያለበት ነው፡፡
በማዕከሉ ከገቡ በኋላ ከማዕከሉ ለመውጣት አይፈልጉም፡፡ በተፈጥሮ ቃና ማዕዛው የሚያውደው ጫካው መንፈስን በሀሴት ይሞላል”” እርስዎ በአካል እስኪጎበኙ እኛ በብዕራችን እናስጎብኝዎ፡፡ በዚሁ ማዕከል ሊጠፉ የተቃረቡ አገር በቀል የእጽዋት ዝርያዎችን በማሰባሰብ በመንከባከብና በማላመድ ዝርያቸው እንዳይጠፋ የመታደግ ስራ እየተሰራ መሆኑን የማዕከሉ ምክትል ዳይሬክተር አቶ መስፍን ሀይሉ ገልፀውልናል፡፡ የጉለሌ የእጽዋት ማዕከል የሚኝበት ስነ ምህዳር ወይና ደጋ ቢሆንም ለማዕከሉ አላማ እንዲመች ተደርጐ ቦታውን በከፍታ ልዩነት በበረሀ፣ በቆላ፣ በወይና ደጋ፣ በደጋና በውርጭ ስነ ምህዳሮች የመለየት ስራ ተከናውኗል፡፡
ዝርያዎቹ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተሰብስበው ለተወሰነ ጊዜ ችግኝ ጣቢያ ውስጥ እንዲቆዩ ከተደረገ በኋላ አካባቢውን ሊላመዱ እንደገና ከጣቢያው ተወስደው ከአምስቱ የማዕከሉ ስነ ምህዳሮች በአንዱ ተተክለው ተገቢውን እንክብካቤ እንደሚደረግላቸው የማዕከሉ የእጽዋት ባለሙያ ወጣት ያሬድ ታረቀ ይናገራል፡፡
የጉለሌ የእጽዋት ማዕከል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋራ ጥረት ወደ ተግባር የተሸጋገረ ተቋም ነው፡፡ ማዕከሉ ከመሀል አራዳ ሰሜናዊ አቅጣጫን ተከትለን ስንሄድ የጉለሌና ኮልፌ ክፍለ ከተሞችን የጋራ ድንበር ላይ የእንጦጦን ተራራ ራስጌ በማድረግ በ705 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ማዕከል ነው”” የስነ ምህዳርና መልከአ ምድር ባለሙያዎች እንደሚነግረን ከሆነ የአባይና የአዋሽ ተፋሰስ መለያያ ነጥብ ወይም መስመር የሚገኘው እዚህ ነው፡፡
ማዕከሉ የሀገራችንን የብርቅዬ አገር በቀል የእጽዋት ዝርያዎች የመንከባከብ፣ ቀጣይነታቸውን የሚያረጋግጥና ምርምር ለማካሄድ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ሲሆን ተግባር ተኮር የስነ ምህዳር ሣይንስ ትምህርት መስጠትና የኢኮ ቱሪዝም አገልግሎትን መሠረት ያደረጉ አላማዎችን ለማሣካት ርብርብ በማድረግ ላይ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡
ማዕከሉ የእፅዋት ብዝሀ - ህይወት ሀብት ተጠብቆ እንዲቆይ ካላስፈላጊ ከሰውና ከእንሰሳ ንክኪ ለመጠበቅ የሚያስችል የሰባት ኪሎ ሜትር አጥር፣ አጐራ ሁለት የአገልግሎት መስጫ ህንፃ፣ ጥልቅ የውሃ ጉድጊድ ቁፋሮ፣ ግድብ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ የመከለያ ቤት (Green House)፣ የመመልከቻ ማማ፣ መፀዳጃ ቤት እና ሌሎች መሠረተ ልማት አውታሮች ግንባታ ተካሄደው ተጠናቀዋል፡፡
ማዕከሉ ከመመስረቱ በፊት ቦታው ላይ 250 ያህል የእጽዋት ዝርያዎች በተፈጥሮ ለምተው የተገኙ ሲሆን ማዕከሉ ከተቋቋመ በኋላ በተሰራው የእጽዋት ማሰባሰብ ስራ ከሁሉም ክልሎች በመሰብሰብ ነባር አገር ቀል የእጽዋት ዝርያዎችን በእጥፍ በማሳደግ 700 ያህል የእጽዋት ስብስብ በጉለሌ እጽዋት ማዕከል እንዲገኙ አስችሏል፡፡ ከማዕከሉ ያገኘነው መረጃ እንደሚያሳየው ከነዚህ የእጽዋት ዝርያዎች ውስጥ 26ቱ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ናቸው፡፡
ማዕከሉ ገና ከምስረታው አራት መሠረታዊ ዋና ዋና አላማዎችን አንግቦ በመነሳቱ በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በርካታ ተግባራትን ማከናወን መቻሉን ምክትል ዳይሬክተሩ አቶ መስፍን ይናገራሉ፡፡
በእቅድ ዘመኑ ሊሰራቸው ካቀዳቸው ተግባራት ዋነኛውና የመጀመሪያ ተግባር የነበረው ማዕከሉን መጤ ከሆኑ እጽዋትና ከባህር ዛፍ ነፃ በማድረግ በአገር ቀበል እጽዋት የመተካት ስራ ተከናውኗል፡፡
ከዚህ ጐን ለጐን የተለያዩ መሠረት ልማቶችን በማዕከሉ ውስጥ በመስራት ለተመራማሪዎች፣ ለጐብኝዎችና ባጠቃላይ ለኢኮ ቱሪዝም ምቹ ሁኔታ መፍጠር መቻሉን የእጽዋት ባለሙያው ወጣት ያሬድ ታረቀ ማዕከሉን በጐበኘንበት  ወቅት ገልፆልናል፡፡
የ24 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን በኮብል ስቶን የማንጠፍ ስራ በመከናወኑ ጐብኝው እንደልብ የሚንቀሣቀስበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ጉለሌ እጽዋት ማዕከል በከተማችን ክልል ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ በርካታ ጐብኝዎች ከአሁኑ ጀምሮ እየጐበኙት ሲሆን የውስጥ ለውስጥ መንገዱም ለጉብኝቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን በማዕከሉ ቆይታችን አረጋግጠናል፡፡
በማዕከሉ ውስጥ ነርሰሪ የእጽዋት ማባዣ ጣቢያም የማቋቋም ተግባር ተከናውኗል፡፡ በመሆኑም በችግኝና በዘር ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ አገር በቀልና ብርቅዬ እጽዋቶችን የማባዛትና በግቢው ውስጥ በመትከል እፅዋቱንም ከመጥፋት የመታደግ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡
በጉለሌ እጽዋት ማዕከል ከተሰሩ ትላልቅ ስራዎች ውስጥ ለማዕከሉ መቋቋም ዋና አላማ የሆነው የእጽዋት መከለያ ቤት (Green House) አንዱ ነው፡፡ የመከለያ ቤቱ በ240 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተገነባና ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን ዘመናዊና ለእጽዋቱ ምቹ አየር ጠባይ በመፍጠር ከተለያዩ አካባቢዎች የተሰበሰቡ እጽዋቶችን የማላመድና የመንከባከብ ስራ ይከናወንበታል፡፡
ከተለያዩ ክልሎች ተሰብስበው የሚመጡ እጽዋቶችን በማቆየትና በማላመድ የአካባቢውን አየር ንብረት ሲለምዱ በመጡበት የአየር ፀባይና በየስነ ምህዳራቸው በመትከል የደን ሽፋኑን ከማሳደግ ባሻገር ለመድሀኒትነት፣ ለውበት መጠበቂያ፣ ለአፈርና ውሃ ጥበቃ እንዲሁም ለላቀ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዲውሉ የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ለማረጋገጥ ችለናል፡፡
የእፅዋት መከለያ ቤቱ ለእጽዋቱ ተስማሚ በሆነ መንገድ በውጭ ባለሙያዎች የተገነባ መሆኑን የገለፁልን ምክትል ዳይሬክተሩ የመከለያ ቤቱ በዋናነት ብርሃን አስተላለፊ ከሆኑና ሌሎች ግብአቶች የተሰራ በመሆኑ ለእጽዋቶች ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ እጽዋቱን በሰው ሰራሽ መንገድ በሚፈለገው አካባቢያዊ የአየር ፀባይ በመንከባከብና አላምዶም ለመትከል ይህ ቴክኖሎጂ መተኪያ የሌለው እንደሆነም ነግረውናል፡፡
ምክንያቱም በግሪን ሐውስ ቴክኖሎጂ እጽዋቱን ከመጡበት አካባቢ የአየር ንብረት ጋር ተመሣሣይ የሆነ ሙቀትና ቅዝቃዜ በመስጠት በአጭር ጊዜ አላምዶ ዝርያቸውን በተለያዩ አካባቢዎች ለመትከል እንደሚያስችል ምክትል ዳይሬክተሩ ስለቤቱ ጠቀሜታ ሲያስረዱ ሰምተናል፡፡ በአሁኑ ሰአት በጉለሌ እጽዋት ማዕከል የተለያዩ አገር በቀል እጽዋቶች ፀድቀው ለማዕከሉ ልዩ ገጽታ ማላበሳቸው ቴክኖሎጂው በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋሉን የሚያሳይ ነው፡፡
በሌላ በኩል ማዕከሉ በመጀመሪያው እቅድ ዘመን ሊሰራቸው ካቀዳቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የአገልግሎት መስጫ ህንፃ /አጐራ ሁለት/ ነው፡፡ የአጐራ ሁለት ግንባታ በ2003 መጨረሻ ተጀምሮ በባለፈው አመት የተጠናቀቀና ጊዜያዊ ርክክብ የተደረገ መሆኑን ምክትል ዳይሬክተሩ ገልፀውልናል፡፡
አጐራ ሁለት የአገልግሎት መስጫ ህንፃ በባህር ዛፍ ቅጠል ቅርጽ የተሰራ፣ በ2 ሺህ 500 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ እና በእንጦጦ ተራራ ደረት ላይ በአረንጓዴ እጽዋት ተከቦ ሲታይ ለአይን ማራኪና አስደሳች ነው፡፡ በባህር ዛፍ ቅርጽ ለመስራት የተፈለገውም ቀደም ሲል ማዕከሉ ያረፈበት ቦታ 80 በመቶ በባህር ዛፍ የተሸፈነ ስለነበር ያንን ለማስታወስ እንደሆነ ባለሙያዎቹ ነግረውናል፡፡
ህንፃው ሙሉ በሙሉ በማዕከሉ ውስጥ በሚገኙ የእጽዋት ውጤቶች ተገንብቶ የተጠናቀ ሲሆን ጣሪያውም ሳይቀር እጽዋት እንዲበቅልበትና አረንጓዴ እንዲለብስ ተደርጐ ነው የተገነባው”” አጐራ ሁለት የአገልግሎት መስጫ ህንፃ ባህላዊ ሬስቶራንት፣ ቤተ መጽሀፍት፣ የስጦታ እና ባህላዊ አልባሳት መሸጫ ሱቆች የሚገኙበት ህንፃ ነው፡፡
ህንፃው በማዕከሉ መሀል ክፍል ላይ የሚገኝ ሲሆን አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ባህላዊ ሬስቶራንቱ በአንዴ ከ500 በላይ ሰዎችን የማስተናገድ አቅም አለው፡፡ ሰባት የተለያዩ የስጦታ እቃዎችንና ባህላዊ አልባሳት መሸጫ ሱቆችንም አቅፏል፡፡ በተለይ በባህላዊ መንገድ የተገነባው ቤተ መፃህፍ ለንባብ ምቹና የተለየ ስሜት የሚፈጥር ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ አጐራ ሁለት ከተለመደው የቤት አሰራር የተለየና የአገራችንን ባህል እንዲያንፀባርቅ ተደርጐ በመገንባቱ ለጐብኝው ማረፊያና መዝናኛ በመሆን ከቱሪስቱ ጠቀም ያለ ገቢ ለማግኘትም ያስችላል፡፡
አጐራ ሁለት በአሁኑ ሰአት ግንባታው በመጠናቀቁ አስፈላጊ የሚባሉ የውስጥ ግብአቶች ተሟልተውለታል፡፡ አይ ሲቲ፣ መብራት፣ ውሃ ገብቶለታል፡፡ በመሆኑም አገልግሎት ለመጀመር የውጭ ተጫራቾችን ጭምር ለማጫረት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አቶ መስፍን ነግረውናል፡፡ ከሌሎች ህንፃዎች ለየት የሚያደርገውም በባህላዊ መንገድ መገንባቱ ብቻም ሣይሆን ሙሉ በሙሉ የሀይል አቅርቦቱን የሚያገኘው ከፀሀይ ብርሃን ማድረጉ ነው፡፡ የታዳሽ ሀይል ተጠቃሚ መሆን መቻሉ ደግሞ ማዕከሉ ከተቋቋመበት አላማ ጋር የሚዋደድ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
አጐራ ሁለት የሙዚየም አገልግሎት የሚሰጥ ሰፋ ያለ ክፍል ያለው ሲሆን የሀገራችንን ባህልና እሴቶች ለጐብኝው በማስተዋወቅ አንድ የገቢ ምንጭ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ለማወቅ ችለናል፡፡
ህንፃው ከሚሰጣቸው ሦስት ዋና ዋና አገልግሎቶች በተጨማሪ የምርምር፣ የቤተ ሙከራና ሙዚየም የሚኖሩ ሲሆን በማዕከሉ ያሉ ሁሉም የእጽዋት ዝርያዎች ደርቀው ለናሙና በሙዚየም ተቀምጠው ጐብኝው እንዲጐበኛቸው ይደረጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም 30 ሺህ ኪዮቢክ ሜትር ውሃ የሚይዝ ግድብ ተገንብቶ የተጠናቀቀ ሲሆን የታችኛውን የማዕከሉን ክፍል በመስኖ ለማጠጣት የሚያስችል ስራም መሰራቱን ከእጽዋት ባለሙያው ከወጣት ያሬድ ታረቀ ለማረጋገጥ ችለናል፡፡
በቅጥር ግቢው ለመጠጥ የሚያስፈልገውን ውሃ ለማቅረብም ከ350 ሜትር በታች ጥልቅ ጉድጓድ ውሃ በማስቆፈር የውሃ መስመር ዝርጋታ እየተካሄደ መሆኑን ለማየት ችለናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ማዕከሉ የሚሰጣቸውን አገልግሎት የተሻለና ለጐብኝው አመቺ እንዲሆኑ በርካታ ስራዎችን ለመስራት ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነም ለመረዳት ችለናል፡፡
እነዚህን ሁሉ ተግባራት ለማከናወን ከእጽዋት ማዕከሉ ቋሚ ሠራተኞች በተጨማሪ በማዕከሉ ዙሪያ የሚገኙ ነዋሪዎችን አቅም መጠቀም አስፈላጊ ነበር፡፡ በመሆኑም ጊዜያዊ የስራ እድል በመፍጠር ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ምክትል ዳይሬክተሩ ገልፀውልናል፡፡
በተለይ ሴቶች በማዕከሉ ተጠቃሚና የስራ እድል ባለቤት መሆን መቻላቸውን በማዕከሉ የእቃ ግምጃ ቤት ሠራተኛ የሆኑት ወ/ሮ የትምወርቅ ዳኜ ይገልፃሉ፡፡ ወይዘሮዋ በእጽዋት ማዕከሉ ለአምስት አመታት በጊዜያዊነት ሰራተኝነት ተቀጥረው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡
ጉለሌ እፅዋት ማዕከል ይህን ተግባራት በአጭር ጊዜ ያከናወነ ቢሆንም ከተያዘው በጀት አመት ጀምሮ በ5000 ሺህ ሜትር ካሬ ላይ የሚያርፍ አጐራ አንድ የአገልግሎት መስጫ፣ አምፊ ቲያትር፣ የመሮጫ ሜዳ፣ አረግራጊ ድልድይና የፈረስ መጋለቢያ እንዲሁም የፊልም መስሪያ ለማስገንባት የቦታ መረጣ ተጠናቅቆ ለግንባታው ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ምክትል ዳይሬክተሩ አቶ መስፍን ሀይሉ ነግረውናል፡፡
ባጠቃላይ ጉለሌ እጽዋት ማዕከል በመጀመሪያው እድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ሊሰራቸው ካቀዳቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶች አብዛኞቹን ሰርቶ በማጠናቀቁ በያዝነው ወር ሲሰራቸው የቆዩትን የውሃ፣ የመስኖ፣ የአጐራ ሁለት አገልግሎት መስጫ ህንፃና የእጽዋት የመከለያ ቤት (Green House) ፕሮጀክቶችን አስመርቆ ለጐብኝው ክፍት ለማድረግ መዘጋጀቱን ሰምተናል፡፡
የጉለሌ እጽዋት ማዕከል በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ከ2000 በላይ የእጽዋት ዝርያዎችን ለማሰባሰብ አቅዷል፡፡ ከአምስቱም ምህዳሮች ማለትም ከበረሃ፣ ከቆላ፣ ከወይና ደጋ፣ ከደጋና ከውርጭ በማሰባሰብ በማላመድና በመትከል ማዕከሉን ከሌሎች የእጽዋት ማዕከላት ጋር ተወዳዳሪና ተመራጭ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራ እያከናወነ ይገኛል፡፡
እፅዋትን በማሰባሰብ ረገድ አገር በቀልና ብርቅዬ እጽዋቶች ልዩ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል፡፡ እነዚህን እፅዋት በማሰባሰብ ለምርምር ስራውም ሆነ ለተግባር ተኮር ትምህርት አጋዥ ማዕከል ለማድረግ በእቅድ እየተሰራ ነው፡፡
ለዚህም ይረዳ ዘንድ በአሁኑ ሰአት በማዕከሉ የሚገኙ የእጽዋት እንክብካቤና ጥበቃ፣ የትምህርት ስልጠናና ማስተባበሪያ፣ የምርምርም ማስተባበሪያና የመዝናኛ ኢኮኖሚ ቱሪዝም የስራ ሂደቶች የማዕከሉን አላማ ለማሣካት ተግተው እየተንቀሣቀሱ መሆኑን ዳሬክተሩ ገልፀውልናል፡፡
በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የተመሠረተው የጉለሌ የእጽዋት ማዕከል የሀገራችንን የአረንጓዴ ልማት ስራ እንደሚያፋጥን አንጠራጠርም፡፡
ለከተማችን ነዋሪዎችም ሆነ ለውጭ ሀገር ጐብኝዎች ጉለሌ የእጽዋት ማዕከል አማራጭ የመዝናኛ ማዕከል ለመሆንም ተቃርቧል፡፡ በአሁኑ ሰአትም በርካታ ዜጐችና ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸውን ይዘው በመሄድ በነፃ እያስጐበኙ ይገኛሉ፡፡
ማዕከሉ የከተማችንን ገጽታ ከማሳመር በተጨማሪ የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆን ለኢኮ ቱሪዝሙ አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ ስለሆነም አረንጓዴውና ነፋሻማው የእጽዋት ማዕከል ከማዝናናት ባለፈ በረሀማነትን መከላከል ትልቅ ራዕይ ሰንቆ የተነሳ ተቋም ነውና ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
ውድ አንባቢዎቻችንም ሄዳችሁ የእጽዋት ማዕከሉን በመጐብኘት ዘና ብላችሁ ቁም ነገር ቅሰሙ፡፡


4 comments: