Tuesday, 4 July 2017

የመፍትሔው አባት






 አቶ መንግስቱ አስፋው ይባላሉ፡፡ በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ ነዋሪ ሲሆኑ የበርካታ አዳዲስ ፈጠራዎች ባለቤት ናቸው፡፡ ባለሙያው ውልደታቸውም ሆነ እድገታቸው እዚሁ አዲስ አበባ ሲሆን ገና ከልጅነታቸው አንስቶ ለፈጠራ ስራ ልዩ ፍላጎትና ተነሳሽነት ነበራቸው”” ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራዎችን በወዳደቁ ቁሳቁስ አስመስሎ በመስራት የተለያዩ ሙከራዎችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን ያስታውሳሉ፡፡ በዚህም በአካባቢው ህብረተሰብ ዘንድ አድናቆትን አትርፈው እንደነበር የሚገልፁት አቶ መንግስቱ ከ11ኛ ክፍል በኋላ ግን በወቅቱ የኢህአፓ አባል ሆነው በመቀላቀላቸው እንኳንስ የፈጠራ ስራ ሊሰሩ ይቅርና ወጥተው ለመግባትም ትልቅ ፈተና ሆኖባቸው ነበር፡፡

የደርግ ካድሬዎችም በተደጋጋሚ ጊዜ ማስጠንቀቂያና ከዛም ባለፈ ሊገድሏቸው ሲሉ ህይወታቸውን ለማትረፍ ቤተሰብ እንኳ ሳይሰናበቱ ትምህርታቸውን አቋርጠው ሽሽትን መረጡ፡፡ ከትውልድ ቀያቸውም ርቀው ከቀን ሰራተኛነት ጀምሮ በአናፂና ግንበኛነት እንዲሁም እስከ መንግስት ሰራተኛነት ያገኙትን ስራ በስጋትና በሰቆቃ በመስራት በነቀምት፣ በባህርዳር፣ በደጀንና ከዛም ወደ አሰብ በማቅናት አስቸጋሪ ህይወት አሳልፈዋል፡፡

በአሰብ ከተማም በአንድ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው በብረታ ብረት ስራ ላይ በመሰማራት በልጅነታቸው የቀን ከቀን ልማድ የሆነውን የፈጠራ ስራ ዳግመኛ በመጀመር የተወሰነ እፎይታ አገኙ፡፡ አጋጣሚውንም ተጠቅመው በርካታ ፈጠራዎችን በመስራት በድርጅቱ ውስጥ አንቱታን አተረፉ፡፡ ይሁን እንጂ ባለሙያው በትርፍ ጊዜያቸው በመኖሪያ ቤታቸውም በግል ይንቀሳቀሱ ስለነበር በአሰብ ከተማ ነዋሪም ዘንድ እውቅና እያገኙ መጥተው በሻይ ማሽን እና በሌሎች የፈጠራ ስራዎቻቸው የራሳቸውን ድርጅት በማቋቋም የመንግስት ለውጥ እስኪደረግ ድረስ ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ከ1983 በኋላ ግን የሰቆቃና የስደት ዘመናቸውን ተሰናብተው ወደ ትውልድ ከተማቸው አዲስ አበባ አቀኑ፡፡

ትምህርታቸውን አቋርጠው ለስደትና እንግልት ተዳርገው የቆዩት የፈጠራ ባለቤቱ አቶ መንግስቱ በቆይታ ዘመናቸው ያገኙትን ልምድና እውቀት ተጠቅመው ለከተማችን አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በማበርከት ኑሯቸውን በአዲስ መልኩ መምራት ጀመሩ፡፡ “ወቅቱም ወደ ጦር ግንባር ሳይሆን እንደፈለገን ተንቀሳቅሰን ሀብት ማፍራት የምንችልበት በመሆኑ ለኔ እንደገና እንደመወለድ ቆጥሬ መስራት ቻልኩ፡፡ ውጤታማም ሆንኩ” ይላሉ፡፡

አዲሱን ህይወታቸውን በሰንዳፋ ከተማ በማድረግ በብረታ ብረት ስራ ተሰማርተው የሻይና፣ የሽንኩርት መፍጫ ማሽን፣ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የተለያዩ ምድጃዎችን የእንጀራ ምጣድ፣ በርና መስኮቶችን እንዲሁም የጫጩት ማስፈልፈያና የወተት ማርጊያ ማሽኖችን በመስራት ሁለገብ የፈጠራ ባለሙያ መሆን መቻላቸውን አጫውተውናል፡፡ በዚህም ከሰንዳፋ እስከ አዲስ አበባ ተቀባይነት እያተረፉ የመጡት ባለሙያው ከፈጠራ ስራዎቻቸው ጎን ለጎንም በከተማ ግብርና ዘርፉም የእንጉዳይ ምርት በማምረት ለከተማችን ነዋሪ አዲስ ነገር ይዘው ብቅ አሉ፡፡ በቀንም እስከ 60 ኪሎ ግራም ምርት ለገበያው በማቅረብ ተጨማሪ ገቢም ማግኘት መቻላቸውን ይናገራሉ፡፡ ይህም ተግባራቸው በከተማችን በሚገኝ የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ተቋማት ዘንድ ትኩረትን በመሳቡ ተቋማቱ ድርጅታቸው ድረስ በመሄድ ለሰልጣኞቻቸው የተግባር ስልጠና እንዲሰጡላቸውም ጠየቋቸው፡፡
አቶ መንግስቱም ባገኙት ሁሉ እድል ተጠቅመው ለመለወጥና ያጠፉትን ጊዜ ለማካካስ ቆርጠው የተነሱ በመሆናቸው ጥያቄውን ተቀብለው ለፈጠራ ስራቸው ይበልጥ ተሞክሮ ወደሚያገኙበት በዌንጌት፣ በእንጦጦ፣ በተግባረ እድ፣ በአቃቂ ቃሊቲ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጆች ውስጥ ለሰልጣኞች ያላቸውን ተሞክሮ በማካፈል የእንጉዳይ ምርትን በጥቃቅንና አነስተኛ በኩል በስፋት እንዲመረት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን በቆይታችን አውግተውናል፡፡

የፈጠራ ባለቤቱ ከሰንዳፋ አዲስ አበባ ከምመላለስ በሚልም ኑሮና ስራቸውን ወደ አዲስ አበባ አደረጉ፡፡ ተደራጅተውም ቢሰሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ ጥናት አድርገው አረጋገጡ፡፡ ጊዜ ሳያባክኑም ተመሳሳይ ሙያ ካላቸው መሰል ጓደኞቻቸው ጋር በመነጋገር በብረታ ብረትና እንጨት ስራ ተደራጅተው የፈጠራ ስራዎችን ለመስራት ወሰኑ፡፡

ከሁለት ጓደኞቻቸውም ጋር በመሆን ወደ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ አስተዳደር ጽ/ቤት አቅንተው ተደራጅተው ለመስራት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ የወረዳው ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽ/ ቤትም ያስገቡትን የስራ ተሞክሮና ልምዳቸውንም በማጤን ተደራጅተው እንዲሰሩ ፈቀደላቸው፡፡

አንድ ወር ባልሞላ ጊዜም ኢትዮ ቻይና ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋም አካባቢ በሚገኘው ኢንዱስትሪ መንደር 60 ካሬ ሜትር መስሪያ ወርክ ሾፕ አገኙ፡፡ “መንግስቱ፣ እዮብና ኮኮቤ ብረታ ብረትና እንጨት ስራ ሀላፊነቱ የተወሰነ የህብረት ሽርክና ማህበር” በሚልም ከሶስቱ አባላት በተውጣጣ 20 ሺህ ብር እና በተወሰኑ አነስተኛ ማሽኖች ህዳር 2008 ዓ.ም ማህበሩ መመስረቱንና ወደ ስራ መግባቱን ነግረውናል፡፡

ከዚህ በኋላ ነበር የፈጠራ ባለቤቱ ከአገር አገር ለ38 አመታት ተንከራትተው ያካበቱትን እውቀትና ልምድ በመመንዘር የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመተጋገዝ ይበልጥ ለማጎልበት የተነሱት፡፡ በዚህም የማህበሩ ሊቀመንበር በመሆን መንቀሳቀስ የጀመሩት የፈጠራ ባለቤቱ አቶ መንግስቱ ከተደራጁ በአንድ አመት ከስድስት ወር ውስጥ አምስት የፈጠራ ስራዎችን መንግስት በሰጣቸው ሼድ ውስጥ በማጠናቀቅና ሶስቱን በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ጽ/ቤት በማስመዝገብ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት አግኝተዋል፡፡

ባለሙያው አንድን ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራን ለመስራት ከችግር እንደሚነሱና ችግሩንም ለመፍታት ጥናትና ምርምር ቀድመው እንደሚያደርጉ ይናገራሉ፡፡ በዚህም በበርካቶች ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት ያተረፉት ባለሙያው “ለመጀመሪያ ጊዜ ሰርቼ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ያበቃሁት አዲስ የፈጠራ ስራ በጥቃቅንና አነስተኛ አንቀሳቃሾች ይሰራል ተብሎ የማይታሰብ ነበር” ይላሉ፡፡ የፈጠራ ስራው ለሀገራችን አዲስና የአርሶ አደሩን ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ በመቆጠብ ምርታማነቱን የሚያሳድግ የመስመር መዝሪያ ማሽን ነው፡፡ ማሽኑን ለመስራት ያነሳሳቸውን ነገር ምን እንደሆነም ጠየቅናቸው? “ከሰባት አመት በፊት በፖሊስና ህብረተሰብ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አንድ ዝግጅት ተመለከትኩ፡፡ የዘር ወቅት በመሆኑ አርሶ አደሩ የእርሻ መሬቱን በዘር እየሸፈነ ስለነበር የፖሊስ አባላቱ ያግዙታል፡፡ እያንዳንዷን መስመርም ተከትለው ዘር በመጣል ሲመላለሱ ስመለከት አድካሚ ስራ መሆኑን አረጋገጥኩ፡፡” በማለት ለምን በአንድ መስመር ብቻ በሚል የአርሶ አደሩን ጊዜና ጉልበት የሚቆጥብ ማሽን ለመስራት ተነሳሁ ይላሉ፡፡ ይሁን እንጂ አንድን ስራ ለመስራት ጊዜ ወስደው ማጥናት ስለነበረባቸው በመስመር መዝራት የሚያስችል ማሽን አገራችን ውስጥ መኖሩን አለመኖሩን ጠየቁ፡፡ መኖሩንም አረጋገጡ፡፡ ነገር ግን ይላሉ “ከውጭ የመጣው የዘር መዝሪያ ማሽን ባለ አንድ መስመር መሆኑና ወጭውም ከ40 ሺህ ብር በላይ በመጠየቁ እንዴት ተደራሽ ማድረግ እንዳለብኝ ማሰብ ጀመርኩ” ይላሉ ከውጭ በውድ ዋጋ የመጣውንም ማሽን ቀርበው በመመልከት በቀላል ወጭና በአገር ውስጥ ብረታ ብረት ማምረት እንደሚችሉም አረጋገጡ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥም ተሳክቶላቸው በአንድ ጊዜ አምስት መስመሮችን በዘር መሸፈን የሚችል ማሽንን እውን ማድረግ ቻሉ፡፡

ማሽኑንም ፈትነው በማረጋገጥ ውጤታማ መሆኑን የገለፁት የፈጠራ ባለሙያው ከጤፍ በስተቀር ሁሉንም የአገዳ እህሎች ዘርን በአስተማማኝ ሁኔታ እንደሚዘራ ማረጋገጣቸውን ይናገራሉ፡፡ ማሽኑ ፊት ለፊት በተገጠመለት ማረሻ መስመር እያወጣ የሚሄድ ሲሆን ዘሩም ጎማው በተሽከረከረ ቁጥር መስመሩን ተከትሎ እየተንጠባጠበ ከኋላ በተገጠመለት ብረት አፈር ማልበስ የሚያስችል ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ማሽኑ በቀላሉ በማንኛውም እንስሳ እየተጎተተ መስራት መቻሉ ደግሞ አርሶ አደሩ በቀላሉ እንዲጠቀምበት ያስችለዋል ይላሉ”” ከውጭ እንደሚመጣው ማሽን በሞተር እንዲሰራ ተደርጎ ቢሰራ ኖሮ አርሶ አደሩን ለሌላ ተጨማሪ ወጭ ይዳርገው ነበር ያሉት የፈጠራ ባለሙያው የእርሳቸው ማሽን ግን በቀላሉ በእንስሳት የሚጎተትና የተማረ የሰው ሀይል የማይጠይቅ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
እስካሁንም በሀገር አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት አግኝቶ ማሽኑን በ15 ሺህ ብር እየሸጡ እንደሚገኙም አጫውተውናል፡፡ ባለሙያው የ56 ዓመት ጎልማሳ ቢሆኑም ገና ሰርተው አልጠገቡም፡፡ ቀንም ማታም ችግርን መሰረት አድርገው በመስራት የመፍትሄ አባት ሆነዋል፡፡ ሁሉንም የፈጠራ ስራዎቻቸውን ችግር ፈቺ እንዲሆኑና ተግባር ላይ እንዲውሉ ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ፡፡

መንግስት በሰጣቸው የመስሪያ ሼድ ውስጥም ምቹ ሁኔታዎች ስለተፈጠሩላቸው በከተማ ግብርና ዘርፉ አዲስ የፈጠራ ስራም ሰርተው ውጤታማ መሆን ችለዋል፡፡ የፈጠራ ስራው ከአንድ ዘመናዊ የንብ ቀፎ በአንዴ እስከ 50 ኪሎ ግራም የተጣራ ማርና 20 ኪሎ ግራም በላይ ሰም ማስገኘት የሚያስችል ነው፡፡ ከዚህ በፊት የነበረውን የማር አመራረት ዘዴ ማለትም ንቧ ማር የምትሰራበትን ሰም የራሷን እንጀራ አስመስሎ ቀፎ ውስጥ በማስገባት በሰሙ ላይ ተጨማሪ ማር እንድታመርት የሚያደርግ ነበር ያሉት ባለሙያው አሁን ላይ ግን የፈጠራ ባለሙያው የሰም እንጀራውን ወይም ሰፈፉን ተመሳሳይ ቅርፅ አስይዘው በፕላስቲክ በመቀየር ከአንድ ቀፎ ከፍተኛ የማር ምርት እንደሚመረት አድርገዋል፡፡

በዚህም የማር ምርትን በከፍተኛ መጠን እንዲጨምር ያደረጉት ባለሙያው በሆለታና ሰበታ እንዲሁም አሶሳ የሚገኙ ግለሰቦችና ድርጅቶች ምርቶቻቸውን በመውሰድ ተጠቃሚ መሆናቸውን አረጋግጠውልናል፡፡ በተለይ በሰበታ ከተማ በከተማ ግብርና ተሰማርተው የሚገኙት አቶ ዋኘው አያልነህ ይህንን አዲስ ፈጠራ ተጠቅመው የማር ምርት ማምረት በመጀመራቸው ውጤታማ መሆን መጀመራቸውን ይናገራሉ፡፡

ከዚህ በፊት ዘመናዊ ነው ተብሎ ሲጠቀሙበት ከነበረው ቀፎ በአንዴ እስከ 30 ኪሎ ግራም ማር ያመርቱ እንደነበር ጠቁመው በአቶ መንግስቱ የፈጠራ ስራ ግን በአንዴ እስከ 50 ኪሎ ግራም ማር ማግኘት መቻላቸውን ይመሰክራሉ፡፡ በተለይ ከዚህ በፊት ከማር ሽያጭ ውጭ ተጨማሪ ገቢ ያልነበራቸው አቶ ዋኘው ዛሬ ላይ ግን በአዲሱ የፕላስቲክ ሰፈፍ በመጠቀማቸው አንድ ኪሎ ግራም ሰም 250 ብር በመሸጥ ተጨማሪ ገቢ ማግኘት መቻላቸውን ነግረውናል፡፡ አቶ መንግስቱ በአሁኑ ሰዓት የማር እንጀራ (ሰፈፍ) ለመስራት የሚያስችላቸውን የፕላስቲክ ሞልዱን ሰርተው በማጠናቀቅም በቀን 500 ያህል ፕላስቲክ ሰፈሮችን በማምረት አንዷን ፕላስቲክ በ36 ብር ለገበያ ማቅረብ ጀምረዋል፡፡
ጎልማሳው የፈጠራ ባለቤት ከግብርና ግብአቶችና ምርቶች ውጭም በሀይል ቆጣቢ ምጣዶችና የዳቦ መጋገሪያ ማሽኖች ላይም ሶስት አመት የፈጀ ጥናት በማድረግ አዲስ የፈጠራ ስራ ይዘው ብቅ ብለዋል፡፡

የፈጠራ ስራው እስካሁን በሀገራችን ያልተሞከረና አገልግሎት ላይ ያልዋለ ሲሆን በስምንት ሊትር የተቃጠለ ዘይት ካለምንም የሀይል መቆራረጥ እስከ 16 ምጣዶች ለ10 ሰዓት ያህል እንጀራ ማስጋገር የሚያስችል የጥናት ውጤት ነው፡፡ ለፈጠራውም መነሻ የሆናቸው ሚስጥር ሲገልፁ “በከተማችን በሀይል መቆራረጥና መጥፋት ምክንያት በእንጀራ ንግድ የተሰማሩ ዜጎች ሲማረሩ በማየቴ ነው” ይላሉ፡፡

በዚህም የከተማችንንም ወንዞች በመበከል ለተጓዳኝ የጤና መታወክ የሚዳርገንን የተቃጠለ ዘይትን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል ዘዴ ዘይደዋል፡፡ አጠቃቀሙም ቀላልና ጭስ አልባ በሆነ መንገድ የተሰራ ሲሆን ለረጅም ሰዓታት በአነስተኛ ወጭ የተገዛን የተቃጠለ ዘይት ከበርሜሉ ወደ ምጣዶች በተዘረጉ ቱቦዎች አማካኝነት እሳት በመለኮስና በማቀጣጠል ምጣዶች እንዲግሉና እንጀራ አብስለው እንዲያወጡ የሚያደርግ ነው”” አንድ ሊትር የተቃጠለ ዘይት በአሁኑ ሰዓት በ8 ብር በከተማችን እንደሚሸጥ የገለፁት ባለሙያው ወጭ ቆጣቢም በመሆኑ ለእንጀራ አምራቾች ትልቅ የምስራች ነው፤ የተቃጠለን ዘይትን መልሶ ከመጠቀም ባለፈ ምጣዶችንም ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ዝገት በማይነካው ቁስ በመስራት በሁለት ደቂቃ ውስጥ 16 እንጀራን ከታችና ከላይ ማምረት እንደሚያስችል በነበረን ቆይታ አረጋግጠውናል፡፡ ከዚህ በተረፈ አባ መላ አምራቾቹን ትርፋማ የሚያደርጋቸውንም ዘዴ ዘይደዋል፡፡ በወርክ ሾፑ የሰሩት የሊጥ ማቡኪያ ማሽን ራሱን በራሱ የሚያጥብና ሊጡ እስኪሳብ ድረስ በደንብ አሽቶ የሚያበካ በመሆኑ ከነባሩ የተሻለ ቁጥር ያለው እንጀራ ለማምረት ያስችላል፡፡ ከዚህ በፊት በእንጀራ ንግድ የተሰማሩ አንቀሳቃሾች መቶ ኪሎ ግራም ዱቄትን ከ750 እስከ 850 እንጀራ ማምረት እንደሚችሉ የገለፁት አቶ መንግስቱ በአዲሱ ማሽናቸው ግን እስከ 1 ሺህ 100 እንጀራ ማድረስ መቻላቸውን ነግረውናል፡፡ በዚህም ከነባሩ ማቡኪያ የ300 እንጀራ ትርፍ በማስገኘታቸው ከ38 በላይ ድርጅቶች ምጣዱንና ማቡኪያውን እንዲያቀርቡላቸው ጥያቄ አቅርበው ወረፋ እየተጠባበቁ መሆኑንና ስድስት በአንድ ለሆነው ማሽን 60 ሺህ ብር መጠየቃቸውን አጫውተውናል፡፡

የፈጠራ ባለቤቱ ደንበኞቻቸው የተቃጠለ ዘይት ተጠቅመው እንጀራ መጋገር ካልፈለጉም ሌላ የሀይል ምንጭ እንዲጠቀሙም አማራጭ አቅርበዋል፡፡ “ደንበኞቼ በተቃጠለ ዘይት መጠቀም ካልፈለጉ በኤሌክትሪክና በኬሮሲን እንዲጠቀሙ አድርጌ ሰርቼዋለሁ፡፡” ብለውናል”” በአንድ ድንጋይ ሶስት ወፍ ይላሉ ይህ ነው፡፡

ሌላውና አስገራሚው የፈጠራ ስራ ደግሞ በአንድ አነስተኛ የከሰል ወይም የኤሌክትሪክ ምድጃ ላይ በአንድ ጊዜ አምስት ህብስቶችን አብስሎ የሚያወጣ ማሽን ሰርተው ለአገልግሎት ማብቃታቸው ነው”” ይህም ማሽን እስካሁን ከነበሩት የዳቦ መጋገሪያ ማሽኖች በይዘትም በአጠቃቀምም የተለየና ቀላል ሲሆን ተደራራቢና እያንዳንዱ መጋገሪያ አራት ኪሎ ግራም ህብስትን (ዳቦን) በእኩል ሰዓት አብስሎ ማውጣት የሚችል ነው፡፡
ይሄ ደግሞ በዳቦ ሽያጭ ላይ ለተሰማሩ ዜጎች ጊዜ፣ ጉልበትና ለሀይል የሚያወጡትን ወጭ በመቆጠብ ትርፋማ የሚያደርግ ነው” ይላሉ፡፡ በዚህም በሀይል መቆራረጥና መጥፋት ምክንያት የዳቦ ሊጥ ተበላሽቶ እንዳይደፋ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ ሲሆን ሁሉም ሊጠቀምበት እንደሚገባም ይመክራሉ፡፡ ማሽኑንም በ3 ሺህ 500 በር ለገበያ ያቀረቡት የፈጠራ ባለቤቱ አንዷን ብቻ ለሚፈልግ ደግሞ በ1 ሺህ 500 ብር እንደሚሸጡ አጫውተውናል፡፡

የፈጠራ ባለሙያው ሁሉንም የፈጠራ ስራዎቻቸውን ሰርተው ለገበያ በማቅረብ አገልግሎት ላይ ያዋሉ ታታሪ ጎልማሳ ሲሆኑ አሁንም መንግስት በሰጣቸው ሼድ በርካታ የፈጠራ ስራዎቻችን በመስራትይህንን እድል ባላገኝ ኖሮ እዚህ ደረጃ ባልደረስኩ ነበርይላሉ፡፡ የዚህ ሁሉ ስኬት ሚስጥር ደግሞ አስረዋቸው ከተደራጁትና እየሰሩ ከሚገኙ ጓደኞቻቸው ጋር የነበራቸው ጥብቅ ትስስርና ተደጋግፎ መስራት ነው፡፡መንግስቱ፣ እዮብና ኮኮቤ ብረታ ብረትና እንጨት ስራ ሀላፊነቱ የተወሰነ የህብረት ሽርክና ማህበርአባላት ከአመት በፊት በትንሽ ካፒታል እና በይቻላል መንፈስ ወደ ስራ የገቡ ሲሆን ዛሬ ላይ የምርቶቻቸውን ቁጥር በማሳደግ በፈጠራ ስራዎቻቸውም ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል”” ለዚህም ስኬት መንግስትን ደጋግመው ያመሰግናሉ፡፡ አባላቱ በአጭር ጊዜ በዋጋም በጥራትም ተፈላጊ እየሆኑ የመጡ ሲሆን 15 ወጣቶችም የስራ እድል በመፍጠር ከሙያ ማስቀሰም በተጨማሪ 1 ሺህ እስከ 2ሺህ 500 ወርሃዊ ደመወዝ መክፈልም ችለዋል፡፡ በስራ ላይ ካገኘናቸው ወጣቶች መካከል የማህበሩ የዲዛይን ስራ ባለሙያው ወጣት አቤኔዘር ወንድወሰን እንደገለፀልን በማህበሩ “አይቻልም” የሚባል ነገር እንደሌለና ሁሉም ነገር በጥናት ተሰርቶ ለአገልግሎት እንደሚበቃ አረጋግጦልናል፡፡ በተለይ በፈጠራ ስራ ላይ ተሰማርተው ከሚገኙ ከማህበሩ ሰብሳቢ ከአቶ መንግስቱ በርካታ የፈጠራ ስራዎችን መቅሰሙን ነግሮናል፡፡ “ያላቸውን እውቀትና ልምድ ለኛ ለማስተማርና ለማስጨበጥ ደከመኝ ሰለቸኝ የማይሉ የሙያ አባታችን ናቸው” በማለት ከእርሳቸው ጋር በመስራቱ ከዲዛይነርነቱ በተጨማሪ የፈጠራ ባለሙያ ለመሆን መብቃት መቻሉን ይናገራል፡፡
ሌላኛውና በኢንተርፕራይዙ የስራ እድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል ወጣት አብርሃም ገብሬ አንዱ ነው፡፡ ወጣቱ የብየዳ ስራ ባለሙያ ሲሆን ወደ ኢንተርፕራይዙ ሲመጣ ምንም አይነት ሙያ እንዳልነበረው ነግሮናል፡፡ አሁን ላይ ግን በኢንተርፕራይዙ የብየዳ ባለሙያ ሲሆን በቀጣይም ከፈጠራ ባለሙያው ያገኘውን እውቀት ተጠቅሞ ተደራጅቶ ለመስራት ማቀዱን አጫውቶናል፡፡ እነ አቶ መንግስቱ እስካሁን በሰሩት ውጤታማ ተግባራት በየካ ክፍለ ከተማ በወረዳ ዘጠኝ ዘንድ ማህበራቸውን በጀማሪ ሞዴል ማኒፋክቸሪንግ አስይዘዋል፡፡ አሁንም ፈጠራ ላይ አተኩረው ለመስራት በሀገር ውስጥ ግብአቶች ከውጭ የሚመጡ ማሽነሪዎችን አስመስለው በመስራት የውጭ ምንዛሬን ለማስቀረት አቅደው እየሰሩ መሆኑን ነግረውናል፡፡ ዛሬ ላይ የማህበሩ አባላት በአጭር ጊዜ ትልቅ ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡ የተትረፈረፈ ጥሬ ገንዘበ ባይኖራቸውም መስሪያ ሼዳቸውን ለስራ በሚያስፈልጉ ማሽኖች አሟልተዋል፡፡

እኛም ወደ መስሪያ ሼዳቸው ባቀናንበት እለት ያየነውም አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችን እውን ለማድረግ ከማሽኖቻቸው ጋር ሲተጉ ነው”” ጥራቱን የጠበቀ ምርት በማምረታቸውም የገበያና የመስሪያ ቦታ ችግር ባይኖርባቸውም ስራዎቻቸውን ግን አስፋፍተው ለመስራት እንደሚፈልጉና ሰፋ ያለ መስሪያ ሼድ እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ፡፡ በየካ ክፍለ ከተማ ከሚገኙ ኢንተርፕራይዞች መካከል በፈጠራ ስራ ላይ ተሰማርተው ውጤታማ ከሆኑ ኢንተርፕራይዞች ውስጥ አንዱ መንግስቱ፣ እዮብና ኮኮቤ ብረታ ብረትና እንጨት ስራ ሀላፊነት የተወሰነ የህብረት ሽርክና ማህበር ስለመሆኑ የወረዳ ዘጠኝ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ጽ/ቤት ተወካይ አቶ ደራራ አልማው ይናገራሉ”” ለዚህ ስኬታቸው ደግሞ የመንግስት ድጋፍና ጠንክረው መስራት በመቻላቸው መሆኑን የገለፁት ተወካዩ “ጥቃቅንና አነስተኛን መደገፍና ማሳደግ የኢንዱስትሪ ሽግግሩን የሚያፋጥን በመሆኑ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል፡፡ በወረዳው ከሚገኙ ኢንተርፕራይዞች የእነ መንግስቱ በአጭር ጊዜ ውጤታማ በመሆኑ ሞዴላችንም ናቸው” ይላሉ””

በወረዳው 326 ኢንተርፕራይዞች የሚገኙ ሲሆን በውስጣቸውም 830 አንቀሳቃሾችን በስራቸው አቅፈው ይገኛሉ፡፡ እነ አቶ መንግስቱ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፈው ለዛሬው ስኬታቸው የበቁት ተግተው መስራት በመቻላቸው ነው፡፡ ምቹ ሁኔታዎችንም በአግባቡ በመጠቀማቸው ለዛሬው ስኬታማነት አብቅቷቸዋል፡፡ አሁንም የእድል በሩ አልተዘጋም”” ነገር ግን የዛሬ እድል ነገ ላትኖር ስለምትችል ካለስራ የተቀመጡ ወጣቶች ሊያስቡበት ይገባል፡፡

1 comment: