የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች፣
የትራንስፖርት ዘርፍ ልማት በዋነኝነት ከአንዱ የሀገራችን አካባቢ ወደሌላኛው አካባቢ የሚደረገውን የምርቶች፣ የአገልግሎቶችና የሰዎች እንቅስቃሴ ለማሳለጥና አንድ የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ ለመገንባት የተቀመጠውን ሕገ መንግስታዊ ዓላማን የሚያሳካ ወሳኝ የመሰረተ ልማት ዘርፍ ነው፡፡ ዘርፉ የሀገራችንን ምርቶች በፍጥነት ወደ ውጭ ለመላክና ወደ ሀገራችን የሚገቡ የተለያዩ ምርቶችን ወደተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተሻለ ፍጥነትና ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ለማድረስ ወሳኝ ሚና ያለው በመሆኑ ኢህአዴግ ባለፉት ዓመታት ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራበት ቆይቷል።
የመንገድ ልማት ዘርፍ የህዝቦች ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥና ዕድገታችንን በማፋጠን
ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት የሚያምነው ኢህአዴግ ባለፉት ስርአቶች ትኩረት ሳያገኝ በመቆየቱ በመጠን፣ በጥራትና በፍትሃዊነት በርካታ ችግሮች የነበሩበትን የመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋት ከመሰረቱ በመቀየር ዘመናት ያስቆጠረውን የህዝቦች የመንገድ ተደራሽነት ጥያቄ መመለስ የሚያስችል አቅጣጫ ተከትሏል፡፡ ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊ መንግስታችን ከዓመታዊ በጀቱ እስከ 40 በመቶ ያክሉን የሀገሪቱ የካፒታል በጀት ለመንገድ ዘርፍ በመመደብ ለህዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ያለውን ቁርጠኛ አቋም በተግባር አረጋግጧል።
በሀገራችን በ1983 ዓ.ም የነበረው አጠቃላይ የመንገድ ርዝመት 18 ሺህ ኪሎ ሜትር አካባቢ የነበረ ሲሆን ዛሬ ኢህአዴግ ገጠር ከከተማ ባማከለ የልማት አቅጣጫ ህዝቡን አስተባብሮ አጠቃላዩን የሀገሪቱ ልማት በተፋጠነ እድገት ይዞ ለመጓዝ ባደረገው ርብርብ የሀገሪቱን አጠቃላይ የመንገድ ርዝመት 105ሺህ ኪሎ ሜትር ማድረስ ችሏል፡፡ በዚህም 10ሺህ 765 የገጠር ቀበሌዎች ከዋና ዋና መንገዶች ጋር ተገናኝተዋል፡፡ በተለያዩ የአገራችን ጫፎች በመንገድ እጦትና በአቅራቢያቸው የህክምና አገልግሎት ባለማግኘት ወደ ጤና ጣቢያ መድረስ አቅቷቸው በምጥ የሚሰቃዩ እናቶችና በህመም የሚንገላቱ ህጻናትና አረጋውያንን የዘመናት ብሶት መፍትሄ ለማግኘት ጥረት የተደረገው ኢህአዴግ ለትራንስፖርት ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት ነው።
በዚህ አመት ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረውና 84 ኪ.ሜትር የሚረዝመው የአዲስ አበባ - አዳማ የፍጥነት መንገድ ከዚህ በፊት እስከ 3 ሰዓት ድረስ ይፈጅ የነበረውን ጉዞ አሁን ወደ 45 ደቂቃ ማውረድ ያስቻለ ነው። በቀን እስከ 20ሺ መኪናዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው ይህ መንገድ የምስራቁንና የደቡቡን የአገሪቱን ክፍል ከመካከለኛው የአገራችን ክፍል ጋር በማስተሳሰርና የወጪና የገቢ ንግዱን በማፋጠን የላቀ ድርሻ እያበረከተ ይገኛል። በግንባታው ከተሳተፉት ውስጥ 90 በመቶ ያክሉ ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ሲታይ ደግሞ አገራዊ አቅማችንን ለማጎልበት ያስቀመጥነው አቅጣጫ ተፈፃሚ መሆኑን የሚያሳይ ነው።
በመንገድ ልማት በተገኛው ውጤት ቀደም ሲል ዜጎች የመኪና መንገድ ለመድረስ በአማካይ 10 ሰአት ሲወስድባቸው የነበረውን ወደ 1 ሰአት ተኩል ለማውረድ ተችሏል። ይህም የሚያሳየው በኢህአዴግ እየተረጋገጠ ያለው ልማት ምን ያህል የህዝብ ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ መሆኑን ነው፡፡ የመንገድ ልማታችን ቀደም ሲል የነበረውን የመንገድ የጥራት ደረጃ ችግር በእጅጉ ያሻሻለና በውጤቱ ከአንዱ ቦታ ወደሌላው ለመጓዝ ይወስድ የነበረውን ረጅም ጊዜም በከፍተኛ ደረጃ አሳጥሯል፡፡
ኢህአዴግ በአገር ውስጥ የተቋራጮችን አቅም በመገንባት በአገራችን የሚከናወኑት የመሰረተ ልማት ስራዎች በውስጥ አቅም እንዲከናወኑ ባለው ከፍተኛ ተነሳሽነት ይህ ዘርፍ ጎን ለጎን የሀገር ውስጥ ተቋራጮችና አማካሪዎች ዓቅም የሚገነባበት ሆኗል። በዘርፉ የአገር ውስጥ ተቋራጮችንና አማካሪዎች አቅም በማጎልበት ሀገራችን በራሷ አቅም ትላልቅ ፕሮጀክቶች ማከናወን የምትችልበት ደረጃ ላይም እየደረሰች ነው። በዚህም በአሁኑ ወቅት አንድ አገር በቀል ተቋራጭ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ፕሮጀክት አሸንፎ መሥራት የሚችልበት አቅም ላይ ደርሰናል፡፡
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች፣
በኢህአዴግ ትክክለኛ አቅጣጫ በባቡር ትራንስፖርት ንዑስ ዘርፍም አዲስ ታሪክ መጻፍ ተጀምሯል፡፡ በአገራችን የሚመረቱ ምርቶችን በብዛት፣ በፍጥነትና በተነፃፃሪ በአነስተኛ ዋጋ ወደ ዓለም ገበያ ለማቅረብ የባቡር ትራንስፖርት ያለውን ፋይዳ በመረዳት የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅዶችን በማቀድ የባቡር መስመር ዝርጋት በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ኢኮኖሚን ለመገንባት የምታደርገውን ሁለገብ ጥረት የሚያግዝ፣ ከብክለት የፀዳና በኤሌክትሪክ ሃይል የሚሰራ፣ የሀገሪቱን የልማት ማዕከላት የሚያስተሳስር እንዲሁም ከጎረቤት ሀገሮች ወደቦች ጋር የሚያገናኝ 2 ሺህ 395 ኪሎ ሜትር ዘመናዊ የባቡር መሰረተ ልማትና አገልግሎት ለመገንባት አቅደን እየተረባረብን እንገኛለን፡፡ በዚሁ መሰረት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገራችን ጫፎች የባቡር መሰረተ ልማት ግንባታው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በአገራችን በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት የተጀመረ ቢሆንም ዘርፉ በበርካታ ተግዳሮቶች የተተበተበ በመሆኑ ሊዘልቅ አልቻለም፡፡ ዛሬ በአገራችን በኢህአዴግ መሪነትና በህዝባችን ያልተቆጠበ ድጋፍ እየተካሄደ ያለው የባቡር ትራንስፖርት ልማት የእስካሁኑን ታሪካችንን የሚያድስና የህዝባችንን ዘላቂ ተጠቃሚነትም በተጨባጭ የምናረጋግጥበት አዲስ ምዕራፍ እንደሚሆን ኢህአዴግ በፅናት በማመን እየሰራ ይገኛል።
ግንባታው ከ95 በመቶ በላይ ተጠናቅቆ የፍተሻና ሙከራ ደረጃ ላይ የሚገኘው የመዲናችን አዲስ አበባ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት በሁለት አቅጣጫ በአንድ ሰዓት 60 ሺህ መንገደኞችን ማጓጓዝ እንዲችል ተደርጎ እየተገነባ ነው፡፡ 34 ነጥብ 35 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ይህ ፕሮጀክት በአጭር ጊዜ ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል። የከተማውን የትራንስፖርት ችግርም በወሳኝ መልኩ እንደሚያቃልለው የሚጠበቅ ሲሆን አዲስ አበባ ከተማንም ዘመናዊ የሆነ የባቡር ትራንስፖርት ያላት የዲፕሎማቲክ ከተማ ያደርጋታል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በአዲስ አበባ ቀላል ፕሮጀክት ግንባታ ወቅት ሲፈጠር የነበረውን ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር በመቋቋም ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ላደረጉት አስተዋጽኦ ኢህአዴግ ከፍተኛ ምስጋናውን ለማቅረብ ይወዳል፡፡
የአገር አቋራጭ የባቡር መስመር ዝርጋታ ስራችን በረዥምና አጭር ጊዜ የሚተገበር ሆኖ በአገር አቀፍ ደረጃ በመጀመሪያው ምእራፍ ከተካተቱት ውስጥ የ656 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የአዲስ አበባ-አዳማ-ድሬዳዋ-መኤሶ-ደወሌ-ጅቡቲ መስመር ይገኝበታል። ፕሮጀክቱ ከአዲስ አበባ እስከ አዳማ ድረስ ባለ ሁለት አቅጣጫ ሲሆን ቀሪው ባለ አንድ አቅጣጫና ከ55 በላይ ጣቢያዎች ያሉት ነው፡፡ ለፕሮጀክቱ ከ3.4 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር የተበጀተለት ሲሆን ባቡሩ ሥራ ሲጀምር በአንድ ጊዜ እስከ 4000 ቶን ጭነት ያጓጉዛል፡፡ የፕሮጀክቱ ስራም 78 በመቶ ገደማ ተጠናቋል፡፡ ፕሮጀክቱ እስከ ሚቀጥለው አመት አጋማሽ ድረስ እንደሚጠናቀቅም ይጠበቃል፡፡
በ42 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚገመተው የመቀሌ- ወልዲያ- ሀራ ገበያ የባቡር መሰረተ ልማት ግንባታ በይፋ ተጀምሯል። የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሃራ ገበያ የምድር ባቡር ፕሮጀክት ደግሞ ከ15 በላይ ጣቢያዎች የሚኖሩት ሲሆን 375 ኪሎ ሜትር ርዝመት ይኖረዋል፡፡ የሰበታ-ኢጃጅ-ጅማ-ጉራፈርዳ-ዲማ/ጅማ-በደሌ ፕሮጀክት 740 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውና በ25 ጣቢያዎች አገልግሎት እንዲሰጥ ሆኖ የሚገነባ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከደቡብ ሱዳን ጋርም የሚያገናኝም ይሆናል፡፡ የሞጆ-ሻሸመኔ/ሀዋሳ-ኮንሶ-ወይጦ-ኮንሶ ሞያሌን እንዲያገናኝ ሆኖ የሚገነባው የባቡር መስመር እንዲሁ ከኬንያ ጋር በባቡር ትራንስፖርት የሚያስተሳስረን ፕሮጀክት ነው።
በአገር አቀፍ ደረጃ በመካሄድ ላይ ያለው የባቡር መስመር ዝርጋታ የሀገራችን ወጪና ገቢ ምርቶችን በተሻለ ፍጥነት በማስወጣትና በማስገባት በጉዞ ይባክን የነበረውን ጊዜ በመቆጠብ አገራችን ከዘርፉ የምታገኘውን ጥቅምና አቅም ያሳድጋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያን ከጎረቤት አገሮች ጋር በማገናኘት በአገራቱ መካከል የሚኖረውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነትና ትስስር በእጅጉ የተሳለጠ የሚያደርግና ኢህአዴግ የአገራችንን ህዳሴ እውን ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የባቡር ትራንስፖርት ለቀጣይ የህዳሴ ጉዟችን ልዩ ትርጉም ያለውና የሀገራችን ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በማድረግ የህዳሴ ጉዟችን በተጀመረው ፍጥነት እንዲቀጥል የሚያስችል በመሆኑ ኢህአዴግ ለተፈፃሚነቱ ከህዝባችን ጋር መስራቱን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
በህዝብ ትራንስፖርት ከፍተኛ መሻሻል የታየበት ሌላው ንኡስ ዘርፍ የአየር ትራንስፖርት ነው። በአሁኑ ጊዜ አለማችን ያፈራቻቸው እንደ ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አይነት ዘመናዊ አውሮፕላኖች ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተደራሽነቱ፣ በአገልግሎት ጥራቱና በተወዳዳሪነቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህ አገራችን ከአፍሪካም ሆነ ከሌሎች የዓለም አገራት ጋር ያላትን ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ ሆኗል። በአገር ውስጥ አራት አለም አቀፍ ኤርፖርቶች ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። በተመሳሳይ የሀገር ውስጥ በረራ የሚያስተናግዱ ኤርፖርቶች ብዛት ወደ 17 በማሳደግ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት የኢኮኖሚ እድገታችንን በሚመጥን ሁኔታ የውሃ ትራንስፖርት ዘርፉ ተወዳዳሪ እንዲሆን አቅምን፣ አደረጃጀትንና ሎጂስቲክን ማሟላት ላይ ያተኮረ ሰፊና ተደጋጋሚ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። በዚህም መርከቦቻችን ከነበራቸው 50 ሺህ ቶን የመጫን ዓቅም ወደ 400ሺህ ከፍ ማድረግ ተችሏል። ሀገራችን በወጪና ገቢ ንግድ የገበያ ውድድር ሲያጋጥማት የነበረውን ዘርፈ ብዙ ችግር የመጫን አቅማቸው ከፍተኛ በሆኑ መርከቦቿ ከመፈታቱ በተጨማሪ ያለ ምንም ተጨማሪ መጉላላት ተፈላጊ ምርቶች በወቅቱ እንዲገቡና እንዲወጡ ማድረግ ችላለች። ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ በወጪና ገቢ ንግዱ ለውጭ ሀገር እቃ ጫኝ መርከቦች ሲወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ በከፍተኛ ደረጃ ማዳን
ተችሏል። የመልቲ ሞዳል አገልግሎት በሀገር ውስጥ በመጀመርም የወጪና የጊዜ ብክነትን ብሎም የወደብ ትራፊክ መጨናነቅን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ተችሏል።
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች፣
ኢህአዴግ ከእናንተው ጋር በመሆን በአገራችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥና የሀገራችንን ቀጣይ ዕድገት ለማፋጠን በወሰዳቸው ኃላፊነት የተሞላባቸው ውሳኔዎችና ቁርጠኛ አፈፃፀሞች የትራንስፖርት ልማት ዘርፉ ከአንድ የስኬት ምዕራፍ ወደ ሌላ ከፍተኛ የስኬት ምዕራፍ እየተሸጋገረ በከተማና በገጠር፣ በአገራችንና በጎረቤት አገሮች መካከል ያለውን ትስስር በማጠናከር ላይ ይገኛል። የትራንስፖርት ዘርፍ ልማታችን በበርካታ ድሎች የታጀበና በእርግጥም እመርታዊ ለውጥ የታየበት ቢሆንም ግን አሁንም መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ኢህአዴግ ይገነዘባል፡፡ በአንድ በኩል የጥራት ችግር በሌላ በኩል ፈጣኑ እድገታችን ያመጣው ከፍተኛ ፍላጎት እስካሁን ከፈፀምነው የበለጠ እንድንሰራ የግድ የሚሉን መሆናቸውንም ይገነዘባል።
በአንጻሩ ኢህአዴግ የሰራውን ማንኛውም ስራ በትክክለኛ ትችት ሳይሆን ተጨባጭ ስኬቶችን ጥላሸት መቀባት ላይ የተጠመዱት የአገራችን ተቃዋሚዎች አማራጭ ብለው የሚያቀርቡት ሃሳብም የአገራችን ህዝቦች በገሃድ የሚያውቋቸውን ስኬቶች የሚያስቀጥል ሳይሆን ወደ ኋላ የሚመልስ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ተቃዋሚዎቻችን አሁን ካለንበት ደረጃም ሆነው ጥሩውን ጥሩ፣ መጥፎውን መጥፎ ብለው ለመናገር እንኳ ድፍረት የላቸውም፡፡ ለዚህም ነው የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ጭምር የመሰከረላቸውን በአገራችን የተገነቡና እየተገነቡ ያሉ መሰረተ ልማቶችን ጭምር ማየት የተሳናቸው፡፡
ኢህአዴግ ከተግባር በመማር የተሻለ ለውጥ እያስመዘገበ በስኬቶች ታጅቦ የመጣ ህዝባዊ ድርጅት በመሆኑ በቀጣይነት በትራንስፖርት ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችንም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ከህዝባችን ጋር በመሆን በአስተማማኝ ሁኔታ እንደሚፈታቸው ያለፈባቸው ምዕራፎች ምስክሮች ናቸው፡፡ በህዝባችን ያልተቆጠበ ትግልና በኢህአዴግ መሪነት አሁንም እየጎመራ የመጣውን የትራንስፖርት ዘርፍ ልማት ስኬት ወደ ላቀ ደረጃ እናሸጋግራለን።
ኢሕአዴግን ምረጡ፣ ምልክታችን ጣፋጩን ማር የምታመርተው ንብ ነች።
No comments:
Post a Comment