Friday, 10 April 2015

ህዝባዊ ትግላችን ለዴሞክራሲያዊ ለውጥ ቅድሚያ በመስጠት የጀመረ ነው፣


እንደሚታወቀው አገራችን ለዘመናት በጨቋኝ አስተዳደሮች ስትመራ ከቆየች በኋላ የህዝቡ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች ከምንም ነገር በላይ ጎልተው ምላሽ የሚሹ ጉዳዮች እስከመሆን ደርሰው ነበር፡፡ የግልና የቡድን መብቶች ጥሰት ሥር የሰደደ ብቻ ሣይሆን ከፍተኛ ደረጃ ላይ በመድረሱ የመብት ጥያቄዎቹ መሠረታዊ ምላሽ ካላገኙ በስተቀር የማያላውሱ መሆን ጀምረው ነበር፡፡ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች፣ የብሄሮች፣ የሃይማኖቶችና የፆታ እኩልነት ጥያቄዎች መሠረታዊ ምላሽ የሚጠይቁ የህልውና ፈተናዎች መሆን ጀመሩ፡፡ በዴሞክራሲያዊ መብት እጦት ምክንያት የህዝቡ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ሊቃለሉ የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ መንግስታቱ በተለይ ደግሞ የደርግ አገዛዝ ይከተሉት የነበረው የተበላሸ የኢኮኖሚ ፖሊሲና በዚህ ምክንያት የተፈጠረው ድህነት ዴሞክራሲን በማስፈን ካልሆነ በስተቀር በሌላ መንገድ ሊስተካከል የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጠረ፡፡ በዚህም ምክንያት ድርጅታችን የደርግን ሥርዓት በህዝባዊ የትጥቅ ትግል ገርስሶ ወደ ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በተሸጋገረበት ወቅት በእርግጥም በአገራችን የዴሞክራሲ ጥያቄን በትክክል የመመለስና ያለመመለስ ጉዳይ የህልውና ፈተና የሆነበት ደረጃ ላይ ተደርሶ ነበር፡፡
ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መነሻ መሰረታችን ይህ መሠረታዊ እውነታ የነበረ የመሆኑን ያህል የአገራችን ዴሞክራሲ እንደ ምዕራቡ ዴሞክራሲ በጠባቡ ተከፍቶ ቀስ በቀስ እየሰፋ እንዲሄድ ለማድረግ የሚያስችል ዕድል የሚሰጥም አልነበረም፡፡ በአንድ በኩል የዘመናት የዴሞክራሲ ጥማት የነበረው ህዝባችን መብቱን ያለገደብ ለማስከበር የሚሻ ስለነበር ዴሞክራሲያችንን በጠባቡ ከፍቶ በሂደት የማስፋት አማራጭን ለመቀበል የሚችልበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ የአገራችን ህዝቦች ከአውሮፓ አቻዎቻቸው ዘግይተው ለዴሞክራሲ የበቁ ቢሆንም በእኛ ተጨባጭ ሁኔታ ከጅምሩ ሰፊ ዴሞክራሲ እንዲያጣጥሙ የሚያስችል ከአውሮፓውያን መሰሎቻቸው የተሻለ የኃይል ሚዛን ብልጫ ነበራቸው፡፡ የደርግን አገዛዝ ለማስወገድ በብሄርና የሃይማኖት እንዲሁም በልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች ዙሪያ የተቀሰቀሰው ትግል ህዝቡ በታዛቢነት ዳር ሆኖ የሚመለከተው ሳይሆን በተደራጀ አኳኋን በንቃትና በሰፊው የሚሳተፍበት ነበር፡፡ ይህም የአገራችን ዴሞክራሲ በጠባቡ ሣይሆን ወለል ብሎ በተከፈተ ሰፊ በር እንዲጀምር ያስቻለው ወሳኝ ምክንያት ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ ህዝባዊ ትግሉን የሚመራው ድርጅታችን በአስተሳሰብ ደረጃ ለህዝቡ ያልተገደበ የዴሞክራሲ መብትን የማጎናፀፍ ዓላማ አንግቦ የሚታገል ድርጅት በመሆኑ ዴሞክራሲያችን በተመጠነ በር እንዲያልፍ ሣይሆን ወለል ብሎ በተከፈተ ሰፊ በር የሚተላለፍ ዴሞክራሲ እንዲሆን ብቃት ያለው የአመራር ሚና መጫወቱ ገና ከማለዳው የኃይል ሚዛኑ ለሰፊ ዴሞክራሲ የተመቸ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
በአገራችን የዴሞክራሲ መብቶችን ታሪካዊ አነሳስ በተመለከተ ይህን ያህል ካልን በቂ ቢሆንም በህገ-መንግስታችን ዋስትና የተሰጣቸውን የዴሞክራሲ መብቶች መነሻ በማድረግ ንፅፅር ብንሰራም ተመሳሳይ ድምዳሜ ላይ መድረስ እንደምንችል ይታመናል፡፡ ህገ-መንግስታችን የዜጎችን መብቶች በተመለከተ በተባበሩት መንግስታት ቻርተር ላይ የተቀመጡ መሠረታዊና ዝርዝር መብቶችን ተቀብሎ ህጋዊ ጥበቃ አድርጎላቸዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ ረገድ አገራችን በየትኛውም ቀደምት የዴሞክራሲ አገር ከተደረገው አዝጋሚና የተበጣጠሰ የመብት ዕውቅና ሂደት በተለየ ሁኔታ የዜጎችን መብቶች አክብራለች፡፡ ለምሳሌ የመምረጥ መመረጥ መብት በሌሎች አገሮች በተሸራረፈ አኳኋን እውቅና የተሰጠውናበአዝጋሚ ሂደት ተግባር ላይ የዋለ መብት የነበረ ሲሆን፣ በእኛ አገር ደግሞ ከመጀመሪያው አንስቶ በተሟላና ባልተበጣጠሰ አኳኋን የተከበረና በተግባር ላይ የዋለ መብት ሆኖ ይገኛል፡፡ በዚህ ባህሪው ዴሞክራሲያችን የዜጎችን መብት አንዴ ከንብረት ባለቤትነት ይዞታ ጋር፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከዘርና ፆታ ልዩነት ጋር አያይዞ ሲያጠብ ከነበረው የምዕራቡ ዴሞክራሲ በእርግጥም የላቀ ሆኖ የጀመረ ዴሞክራሲ ነው፡፡
ለቡድን መብቶች በተለይ ደግሞ ለብሄር ብሄረሰቦች መብቶች የሰጠው ትኩረትና መፍትሄም በመሠረቱ ብዙዎች ከሩቅ የሚሸሹዋቸውን የዴሞክራሲ አማራጮች በድፍረትና በሙሉ ህዝባዊ መንፈስ በመቀበል የጀመረ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ የብሄር ብሄረሰቦችን የራስ ዕድል በራስ የመወሰን መብት ነፃ መንግስት እስከ መመስረት በሚደርስ አቅጣጫ ዕውቅና የሰጠ ዴሞክራሲ በማንኛውም መስፈርት ቢለካ የቡድን መብቶችን በመገደብ ቅኝት ከተገነቡ ዴሞክራሲዎች የማይተናነስ ይልቁንም የተሻለ እንደሆነ ለመገንዘብ አያዳግትም፡፡

እነዚህ ሁለት ተመጋጋቢና ጠንካራ አቅሞች የአገራችን ዴሞክራሲ ከምዕራቡ ዴሞክራሲ ዘግይቶ የጀመረ ቢሆንም ገና ከጥዋቱ የብዙሃኑን መብት ያስከበረና በሰፊው የተለቀቀ ዴሞክራሲ እንዲሆን አድርገውታል። ከዚህም በመነሳት የእኛ ዴሞክራሲ በይዘቱም ሆነ በባህሪው የተሻለ ዴሞክራሲ ነው እንላለን፡፡ እንደገናም በየአምስት ዓመቱ እየመጡ የዴሞክራሲ ኦዲተሮች ለመሆን የሚቃጣቸው አንዳንድ ምዕራባውያን ተቋማትና ግለሰቦች የራሳቸውን አዝጋሚ የዴሞክራሲ ጉዞ የማናውቅ ይመስል ስለእኛ ዴሞክራሲ በተናገሩ ቁጥር ደረጃውን ዝቅ አድርገነዋል ቢሉን ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ እንላለን፡፡ ስለዴሞክራሲ ሐዋርያ ሆነው የሚሰብኩና የእኛ ዴሞክራሲ በሁሉም መስፈርቶች ያነሰ እንደሆነ ለማረጋገጥ ለሚሹም ሆነ ለሚሞክሩ ሁሉ ከዚህ መሠረታዊ ግንዛቤ በመነሳት በሙሉ መተማመን መልስ መስጠት እንችላለን፡፡ ይገባናልም፡፡ አምስተኛውን አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ለማካሄድ በተዘጋጅንበት በዚህ መድረክ ስለአገራችን ዴሞክራሲ ስናስብ በዚህ እውነታ ላይ ልንመሰረት ይገባናል፡፡ ስለ ዴሞክራሲያችን ታሪካዊ አነሳስ ይህን ያህል ካልን በምርጫ ዴሞክራሲያችን ዙሪያ ደግሞ የተወሰነ ምልከታ በማድረግ ቀጣዩ ምርጫ በእርግጥም የህዝብ አመኔታ ያተረፈ፣ ህጋዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ለማድረግ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባ ጉዳዮችን ወደ መዳሰስ እንሸጋገራለን፡፡

No comments:

Post a Comment