Tuesday, 5 May 2015

ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የሞት ቀጠና ጉዞ፤ የተስፈኞች መቅሰፍት (ህዳሴ ጋዜጣ)


 
መግቢያ

ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር የዓለማችን ቀዳሚ አስከፊ ወንጀል ተብሎ የሚፈረጅ ሆኗል፡፡ በዓለም ኢትዮጵያን ጨምሮ 127 ሃገራት ለከፍተኛ ድንበር ተሻጋሪ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ተጋላጭ መሆናቸውን ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት”” በተለይ ምስራቅ እስያ፣ አውሮፓ፣ አሜሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅ፣ ማዕከላዊ እስያና አፍሪካ ግንባር ቀደም ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ይህ ከ32 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚንቀሳቀስበት ህገወጥ የሰዎች ዝውውር /ድንበር ማቋረጥ/ ለጥቂቶች ሲሳይ ለብዙዎች መቅዘፍት ሆኗል፡፡ ከጦር መሳሪያ ንግድ በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃ ይዞ የነበረውን የዕፅ ዝውውር ንግድን በመብለጥ ከፍተኛ የወንጀል ሃብት ማግኛ የሆነው  ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር በተደራጁ ወንበዴዎች የሚፈጸም ወንጀል ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንም የዚህ ከሃገርውስጥ ጀምሮ እስከ አለምአቀፍ ትስስር ያለው የዚሁ ወንጀል ሰለባ በመሆን ዜገቿ ለማቴሪያላዊ፣ አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳት ከመዳረግ አልፈው የበረሃ አውሬና የባህር ዓሳ ነባሪ ሲሳይ እየሆኑ ነው፡፡ ወደ ደቡብ አፍሪካ ከሚደረገው ህገወጥ ዝውውር በስተቀር በሁሉም አቅጣጫ ውቅያኖስና ባህር ተሻጋሪ በመሆናቸው በቅጡ እንኳን ስለመሞታቸው ያልተነገረላቸው ዜጎች ቁጥር የት የለሌ ነው፡፡ ህገወጥ ሰዎች አዘዋዋሪዎችና ሌሎች ወንጀለኞች ደግሞ እንደ ሊቢያ ያሉትን ማእከላዊ መንግስት ቀውስ የገባባቸው ሃገሮችን እንደ ምቹ ሁኔታ ይጠቀማሉ፡፡ 

* የሰዎች ዝውውር አለም አቀፋዊ ገጽታ
   የሰዎች ከቦታ ቦታ መዘዋወር የሰው ልጅ መብት ሲሆን ይህ ዝውውር በሁለት መልክ ይፈጸማል፡፡ አንደኛው ሕጋዊ ስርአትን የተከተለ ሲሆን ሌላኛው ህገ-ወጥ በሆነ መንገድ የሚፈጸም ነው፡፡ አለም አቀፍ ህግና ስርአት እስከተከበረ ድረስ የሰዎች ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር መዘዋወር ተፈላጊና ተቀባይነት ያለው ጉዳይ ነው፡፡ በሃገራችንም የሰዎች ከቦታ ቦታ በነፃ መንቀሳቀስ ህገመንግስታዊ ዋስትና ካገኘ ሁለት አስርት ዓመታት ተቆጥሮዋል፡፡
 አሁን ባለንበት ግሎባላይዜሽን ዘመን ለልማትና ብልጽግና አገሮች አለም አቀፋዊ የስራ አገልግሎት ትብብር (International Labour Service Cooperation) ማድረግ እንደሚገባቸው በሁሉም ዘንድ የሚታመንና ተግባራዊም እየተደረገ ያለ እንቅስቃሴ ነው፡፡ይህ አለም አቀፋዊ ትብብርም በሁለት መልክ የሚታይ ነው፡፡አንደኛው የሠው ሀይል ወደ አገሮች መላክን (Labour Exporting) ሲያመላክት ሁለተኛው የሠው ሀይልን ወደ አገር ውስጥ ማስገባትን (Labour Importing) የሚያመላክት ነው፡፡ ሁለቱም የየራሳቸው ፋይዳ አላቸው፡፡
   የሠው ሀይል ወደ ውጭ አገር መላክ የውጭ ምንዛሬ ወደ አገር በማስገባት ረገድ ፣ የስራ  አጥ ችግር ከመፍታት አኳያ፣ የላቀ ቴክኖሎጂና የስራ አመራር እውቀትና ክህሎት ለማሸጋገር እና የአገር ውስጥ ምርት ወደ ውጭ ለመላክ መልካም አጋጣሚ ከመፍጠርና ከማስፋት አኳያ ጠቃሚ ነው፡፡ እንደዚሁም የሠው ሀይል ወደ አገር ውስጥ ማስገባት የሚከሰተውን የሰራተኛ ሀይል ዕጥረት ከመሙላት አንፃር፣ በአገር ውስጥ የሚያጋጥሙትን የቴክኒክ ችግር ከመፍታት እና የምርት ወጪን በመቀነስ በገበያ ተወዳዳሪነትን የሚያጠናክር ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል በአለም ኢኮኖሚ ውስጥ ሳይንስና ቴክኖሎጂን በአለም ዙሪያ በማስተላለፍ ፣የየአገሮችን ምርት በማስተዋወቅ ከማስረጽና አለም አቀፍ ንግድን ከማስፋፋት አኳያ ከፍተኛ ጥቅም አለው፡፡
  ከሰዎች ህጋዊ ዝውውር ጋር ተያይዞ ከላይ የተጠቀሰው ልማታዊ አስተዋጽኦ ቢኖረውም በድርጅታችንም የሚደገፍ ቢሆንም በአንፃሩ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ /በህገወጥ/ የሚደረግ የሰዎች ዝውውር ሰውን ለተለያዩ ወንጀሎች ይዳርጋል”” በዚህ ህገወጥ ሰለባ የሚሆኑ ሰዎች እስከ ሞት የሚያደርስ አደጋ ያጋጥማቸዋል፡፡ በሃገር መልካም ገፅታም የራሱን አሉታዊ ጥላ ያጠላል፡፡

* የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ምንነትና ገፅታ
ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ሲባል ድንበር ተሻጋሪና በአንዲት ሀገር ውስጥ የሚደረግ ጭምር ነው፡፡ በህገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማቋረጥ/Human Smuggling/  ሲባል ሰዎች በህገ-ወጥ መንገድ ማለትም ምንም ዓይነት የዜግነት መብት ወይም ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው የተቀባዩን ሃገር ይሁንታ ሳያገኙ ወይም ወደ ተቀባዩ ሃገር ለመግባት መሟላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎችን ሳያሟሉ ቀጥተኛም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ወይም ገንዘብና ሌሎች ጥቅሞችን በመፈለግ የአንድን አገር ድንበር ያለፈቃድ በድብቅ አቋርጦ መግባት ማለት ነው፡፡
   ሰዎችን በህገ-ወጥ መንገድ የማዘዋወር አይነተኛ አላማ አንድን ግለሰብ ለብዝበዛ መዳረግ ሲሆን፣ የሰዎች ድንበር ተሸጋሪነት ዋና አላማ ሰዎችን ዜግነት ወደሌላቸው ወይም ህጋዊ ነዋሪ ወደ አልሆኑበት አገር በህገ-ወጥ መንገድ ማስገባት ነው፡፡ ነገር ግን ሁለቱም ድርጊቶች ለጥቅም ሲባል በሰው ልጆች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ናቸው፡፡
ህገወጥ ድንበር ማቋረጥ በባህሪው መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት/Irregular Migration/ በመሆኑ ይህ ዓይነቱ ፍልሰት ከላኪ፣ ከተቀባይ እና ከመሸጋገሪያ ትራንዚት አገሮች አካሔድ ቁጥጥር ውጭ የሚደረግ የሰዎች እንቅስቃሴ ነው፡፡ ይህ በመሆኑም ተጓዦቹ ከማንኛውም አደጋ ከለላ ውጪ ናቸው፡፡
ጉዞዎቹ እንደየ አካባቢው እና ሁኔታዎች አመችነት ከመደበኛ ትራንስፖርት አገልግልሎት ጀምሮ፣ በሌሊት፣ በበረሃ ሃሩር፣ በባሕር እና በውቅያኖስ ማጓጓዝን፣ ኬላዎችን እና የቁጥጥር ቦታዎችን ተሰውሮ ማለፍን ያካትታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ግን በሞት ቀጠና ላይ የሚደረጉ የሞት ጉዞ ናቸው፡፡ ሁሉም አስቸጋሪ ፈተናዎችንና አደጋዎች የመሸከም ግዴታ በስደተኛው እንጂ በአዘዋዋሪዎቹ የሚወድቅ ሃላፊነት አይደለም፡፡
በእነዚህ ተጓዦች የሚደርሰው የብዝበዛው አይነትም እጅግ ዘግናኝ ነው፡፡ ከነዚህ መካከል ወሲባዊ ጥቃት፣ የዝሙት አዳሪነት ስምሪት፣ የጉልበት ሥራ፣ ባርነት፣ ባርነት መሰል ተግባር፣ የግዴታ አገልጋይነት እና የሰውነት አካል ክፍልን ማውጣትና መሸጥን ያጠቃልላል”” እነዚህ ወንጀሎች በሰሃራ በረሃ በየቀኑና በየደቂቃ የሚፈፀሙ ናቸው፡፡ 

* ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር በኢትዮጵያ
 ያለው ገጽታ
   ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ዓለም አቀፋዊ ችግር እንደመሆኑ መጠን ኢትዮጵያ በችግሩ ውስጥ ከሚገኙ ሀገራት ተርታ ትገኛለች”” በተለያዩ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ሕፃናት፣ ሴቶችና ወጣቶች ለችግሩ ሰለባ ሆኖዋል እየሆኑም ነው፡፡ ኢትዮጵያ አብዛኛውን ጊዜ በዚህ ችግር ውስጥ እንደመነሻ ሀገር የምትታወቅ ሲሆን አልፎ አልፎም ከሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ለሚነሱ ሰለባዎች እንደመተላለፊያ መስመርም ሆና ታገለግላለች፡፡

* የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ዋና
  ተዋናዩች
የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ዋና ተዋናዩች ሕገ ወጥ ደላላዎች ናቸው፡፡  በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ውስጥ ግለሰቦችን ከመመልመል አንስቶ ማጓጓዝን እና በመጨረሻም በብዝበዛም ላይ ቀጥተኛም ይሁን ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የሚሣተፉና በምልመላ ወቅት የግለሰቦችን ልብ የሀሰት ተስፋና መደለያ በመስጠት የሚያነሳሱ በጉዞ ወቅትም ግለሰቦች በሕገ ወጥ መንገድ የሚጓጓዙበትን መንገድ የማመቻቸትና የማስተላለፍ ሥራ በመሥራት በመጨረሻ ለብዝበዛ ወደ ተፈለገው ቦታ ያደርሣሉ፡፡ ሕገ ወጥ ደላላ የምንላቸው በአራት የሚከፈሉ ሲሆኑ እነሱም የአካባቢ ደላላ፣ አገናኝ ደላላ፣ ተረካቢ ደላላና መንገድ መሪ ደላላ የምንላቸው የተሳሰረ ኔትወርክ ያላቸው ናቸው፡፡

የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መነሻ ገፊ ምክንያቶች

ሀ) የአመለካከት ችግር
 በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መባባስ ዋነኛው ችግር የአስተሳሰብ ድህነት ነው፡፡ በሀገራችን ያለውን መልካም አጋጣሚ ከማየት ይልቅ በሆነ አጋጣሚ ከአመታት በፊት ሔደው የተሳከላቸውን ሰዎች ብቻ እንደሞዴል በማየት ሁኔታው በተገላበጠበት ዘመን ሰው ራሱን ለስደት እየዳረገና ለከፋ አደጋ እየተጋለጠ ይገኛል፡፡
የችግሩ ዋነኛ ምንጭም በአካባቢ ያለን መልካም አጋጠሚ ሳያስተውሉ በስደት ያልፍልኛል በማላውቀው ሀገር የተሻለ ነገር ይገጥመኛል ብሎ መመኘት ነው፡፡ ይህ ምኞት ሁለት አደጋ ያስከትላል የመጀመሪያው ያለንን ሀብት እንዳናይ በሀገራችን ሰርተን መለወጥ የምንችልበትን አማራጭ እንዳናማትር አይናችንን ይጋርደናል፡፡ የራሱንና የቤተሰቡን በሃገር ውስጥ ሰርቶና ለፍቶ የቋጠረውን ሃብት ጠራርጎ በመውሰድ በማባከን ወይም የብድር ቀንበር ውስጥ በማስገባት ቤተሰቡን ጭምር ለከፋ የድህነት አደጋ ያጋልጣል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ጉም አስጨብጦ ህይወትን ለአደጋ ይዳርጋል፡፡ በቅርቡ ያጋጠመው የሊቢያው ዘግናኝ መርዶ የዚህ በቂ ማሳያ ነው፡፡

ለ) ድህነት /የገቢ ማነስ/ እና ስራ አጥነት
ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እንድ መነሻ ምክንያት ከሚጠቀሱት ውስጥ ድህነት/ የገቢ ማነስና ስራ አጥነት ነው የሚል የቆየ መግባባት አለ፡፡ በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ደላሎች በሚሰጡት የሀሰት ተስፋና መደለያ የመሣሳት እድላቸው የሰፋ በመሆኑ ሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን ዓላማ አድርገው ይንቀሣቀሣሉ፡፡
 ነገርግን በተለይም ድንበርን በማቋረጥ የሚደረገው ህገወጥ የሰዎች ዝውውር በ10ሺዎች ከዚህም አልፎ እስከ መቶ ሺህ ብር ገንዘብ ለደላሎች የሚከፈልበት መሆኑን ሲታይ/እንግዲህ ተጓዡ ለስንቅና ሌሎች ጉዳዮች የሚያወጣውን ሳይጨምር/ ድሃ ተብለው ሊፈረጁ ይችላሉ ወይ የሚለው ጥያቄ በስፋት እንዲደመጥ አድርጎታል፡፡
አንዳንድ ጊዜም በአገር ውስጥ የተመቻቸ ኑሮ ያላቸውም ቢሆኑም ለዚህ ህገወጥ ድርጊት ሲዳረጉ እና ሰለባ ሲሆኑ ይታያል”” ያም ሆኖ ሃገራችን ድህነትን ለማስወገድ ከፍተኛ ርብርብ እያደረገች ባለችበት ሁኔታ አሁንም ስራአጥነትና ድህነት በመኖሩ ምክንያት የተሻለ  ስራ ፍለጋ በሚል ዜጎች ውጭን እንዲያስቡና ለህገወጥ ድርጊት ተጠቂ እየሆኑ ያሉበት ጉዳይ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጥበት የሚገባ ነው፡፡

ሐ) የቤተሰብ እና የጓደኛ ግፊት
አንዳንድ የሕብረተሰብ ክፍሎች በአካባቢያቸው ነዋሪ የነበሩ ዜጐችን ውጭ ሀገር ወጥተው ሰርተው በመመለስ የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ኑሮ ሲያሻሽሉ በመመልከትና ለቤተሰባቸው በሚልኩት የውጭ ምንዛሬ በመማረክ ለሰለባው/ተጎጂው ቅርብ የሆነ የቤተሰብ አባል እና ጓደኛ ሰለባው/ተጎጂው ወደ ውጭ ሀገር ሄዶ እንዲሠራ ጫና በመፍጠር ዜጐችን በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር መረብ ውስጥ እንደሚከትዋቸውም ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡

መ) ሕገ ወጥ ደላሎች የሚሰጡት ሀሰተኛ 
    መረጃና ተስፋ
ሕገ ወጥ ደላሎች በዚህ ድርጊት ውስጥ የሚያገኙት ጥቅም እጅግ በጣም የተጋነነ ከመሆኑ የተነሣ ሰለባዎችን ለመመልመልና ልባቸውን ለማንሣት ከፍተኛ የሆኑ ስልቶችን በመጠቀም ዜጐችን የሀስት ተስፋና መደለያ በመስጠት ዜጐች ወደ ውጭ ሀገር ቢሄዱ ለራሣቸውና ለቤተሰባቸው የሚተርፍ ሀብት ማፍራት እንደሚችሉ፣ የተሻለ ሥራ እና የኑሮ ሁኔታ እንደተመቻቸላቸው ቃል በመግባት የሚጠቀሙበት ሀሰተኛ መረጃና ተስፋ ለሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የራሱን ድርሻ ይዞ ይገኛል፡፡

ረ) የተሻለ ሕይወት ፍለጋ
ዜጐች አሁን ያሉበትን የኑሮ ሁኔታ ወደ ሌላ ሀገር ቢሄዱ ሊስተካከልና የተሻለ ሊሆን እንደሚችል በማሰብበ በሃገራቸው መካከለኛ ገቢ የሚያገኙ ቢሆኑም የተሻለ የሥራ እንቅስቃሴ እና የኢኮኖሚ አቅም ወዳለበት ሀገር በመጓዝ ከትሩፋቱ ለመቋደስ በማለም በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ውስጥ ይወድቃሉ፡፡

* ችግሩን ለመግታት የተወሰዱ ወቅታዊ
  እርምጃዎች
 በሀገራችን የሚገኙ ዜጎች ለህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ በመሆን በሚፈልጉበት ቦታ ለመድረስ በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች ሆነ በተለያዩ ችግሮች ውጣ ውረድ ውስጥ አልፈው በህገ-ወጥ መንገድ ተጉዘው ተስፋ ወደ አደረጉበት አገር ከደረሱ በኃላ  የሚደርስበቸው ስቃይና እንግልት በየጊዘው እየጨመረ በመምጣቱና አሰቃቂ ግፍና በደልን ለመግታት በሀገር ደረጃ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ  የሚመራ አገር አቀፍ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር አስወጋጅ ብሔራዊ ምክር ቤት ተቋቁሟል፡፡ በመላው ሃገሪቱም በተዋረድ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተከላካይ ምክር ቤት ተቀቁሟል፡፡ በዚህም ህበረተሰቡ በጉዳዩ ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲያገኝ በሃገር ደረጃ ሰፋፊ መድረኮች ተፈጥረው እንዲወያይበትና የመፍትሄው አካል እንዲሆን በየክልሉ ሰፊ  ስራ ሲሰራ ቆይቷል፡፡
 በተደራጀው ግብረ ሀይልም በሀገራቸውም ሆነ ወደ ውጭ ሀገር በህጋዊ ተንቀሳቅሰው መስራት ለሚፈልጉ ዜጎች በመንግስት ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች በማስገባት በተለያዩ የስራ መስኮች የአጭር ጊዜ ስልጠና መስጠት፣ ከሥልጠና በኋላ በሠለጠኑበት ሙያ በሀገር ውስጥ በመደራጀት ወደ ሥራ መሰማራት የሚፈልጉ ዜጎችን ከስራ ጋር ማስተሳሰር፣ የመስሪያና የመሸጫ ቦታ አቅርቦት ለሚፈልጉ ዜጎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት አገልግሎቱን እንዲያገኙ ማድረግ፣ ለስልጠናና መሰል ስራዎች ድጋፍ የሚውል ሐብት ማስገኛ ፕሮጀክቶችን ማዘጋጀትና ሀብት ማፈላለግ ሲሆን በዚህ ረገድ በአዲስ አበባ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ ለምሳሌ ከአረብ አገር ተመላሾችን በጊዜያዊነት በመንከባከብ እንዲረጋጉ ከማድረግም አልፎ  ለ2 ሺህ 797 ከስደት ተመላሾች የስነ ልቦ፣ የአመለካከትና የክህሎት ስልጠና እንዲያገኙና ወደተለያዩ የስራ መስኮች እንዲሰማሩ ተደርጓል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን በዚህ ትውልድን ለአደጋ በሚዳርግ ተግባር የተሰማሩ ደላሎች ላይ የህግ ማስከበር ስራዎችም ተወስደዋል፡፡ የሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራት፡-
የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መነሻ፣ መተላለፊያና መዳረሻ ቦታዎችን መለየት ችግራቸውን መሰረት አድርጎ በተመረጡ እና ቁልፍ በሆኑ ቦታዎች የቁጥጥር ስራ ተከናውኗል፡፡ በሀገሪቱ የሚገኙ የውጭ ሀገር የግል ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ህግን መሰረት አድርጎ ነው እንዲንቀሳቀሱ የማድረግ ስራዎችም ተሰርተዋል፡፡ የህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ተጎጂዎችን የሚመለምሉና የሚያዘዋውሩ ደላላዎችን፣ ተባባሪና ቤት አከራዮችንና አጓጓዦችን መረጃ ማሰባሰብና በመለየት በህግ ተጠያቂ የሚሆኑበትን አሰራር የመፍጠር እርምጃዎችም ሲወሰዱ ቆይቷል፡፡

* ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን
  በመከላከል ረገድ የመዋቅራችን ሚና
የህገ-ወጥ የሰዎች  ዝውውር ችግር  በዋናነት ከአስተሳሰብ የሚመነጭ ችግር በመሆኑ በአገር ሰርቶ መኖር ብሎም መክበር እንደሚቻል ያለማወቅ ወይም ለማወቅ ያለመፈለግ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡ በመሆኑም በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ተለያዩ ሀገራት የሚሄዱና የተለያዩ ችግሮች የሚያጋጥማቸው ሴቶችና ወጣቶች ስራ የሌላቸው ብቻ ሳይሆኑ ለህገወጥ ስደት ገፊ ምክንያቶች በሚል ንኡስ ርዕስ እንደጠቃቀስነው ሰዎች ለስደት የሚሄዱት በተለያየ ምክንያት መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡
ስደትን አማራጭ ያደረጉ ሰዎች ሁሉም ቤሳቤስቲ የሌላቸው ናቸው የሚለው ድምዳሜ የተሳሰተ መሆኑ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡ በተለያየ የትምህርት ደረጃዎች ተምረው፣ በተለያዩ የመንግስት ስራ ተቀጣሪ የሆኑና ወደ ቢዝነስ ለማሰማራት የሚያስችል የራሳቸውና የቤተሰብ መነሻ ካፒታል ያለቸው ጭምር ሳይቀሩ ተሳታፊ የሆኑበት መሆኑም መዘንጋት የለበትም፡፡
ምንም ይሁን ምን ግን ህገወጥ የሰዎች ዝውውር በማይጨበጡ ህልሞች የተሞላ ሲሆን ህብረተሰቡ እጅግ የሚዘገንን ታሪኮችን ተሸክመው በዕድል ወደ ተነሱበት ሃገር ደርሰው የተሳካላቸውን ብቻ ሳይሆን በአንድ ቀን እስከ 800 ሰዎችም በአንድ ጃልባ ውቅያኖስ ገብተው የሚቀሩበት የመቅዘፍት መንገድ መሆኑን እያጋጠሙ ያሉ እውነታዎችን በማብራራት የድርጅቱ አባላት ትውልድን ልንታደግ ይገባል፡፡  አባላት ህብረተሰቡን በሃገር ዉስጥ ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል በቂ ግንዛቤና ቁርጠኝነት በመያዝ በተለይም ወጣቶችና ሴቶች በደላሎች ሰበካ እንዳይታለሉ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ለህብረተሰቡ በመስጠት የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት የሚገባቸው መሆኑን አውቀው መንቀሳቀስና ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡




Thursday, 30 April 2015

በኢህአዴግ ትክክለኛ ፖሊሲ በትራንስፖርት መሰረተ ልማት የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስቀጠል የህዳሴ ጉዟችንን እናሳካለን!



የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች፣
የትራንስፖርት ዘርፍ ልማት በዋነኝነት ከአንዱ የሀገራችን አካባቢ ወደሌላኛው አካባቢ የሚደረገውን የምርቶች፣ የአገልግሎቶችና የሰዎች እንቅስቃሴ ለማሳለጥና አንድ የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ ለመገንባት የተቀመጠውን ሕገ መንግስታዊ ዓላማን የሚያሳካ ወሳኝ የመሰረተ ልማት ዘርፍ ነው፡፡ ዘርፉ የሀገራችንን ምርቶች በፍጥነት ወደ ውጭ ለመላክና ወደ ሀገራችን የሚገቡ የተለያዩ ምርቶችን ወደተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተሻለ ፍጥነትና ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ለማድረስ ወሳኝ ሚና ያለው በመሆኑ ኢህአዴግ ባለፉት ዓመታት ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራበት ቆይቷል።  
የመንገድ ልማት ዘርፍ የህዝቦች ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥና ዕድገታችንን በማፋጠን  ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት የሚያምነው ኢህአዴግ ባለፉት ስርአቶች ትኩረት ሳያገኝ በመቆየቱ በመጠን፣ በጥራትና በፍትሃዊነት በርካታ ችግሮች የነበሩበትን የመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋት ከመሰረቱ በመቀየር ዘመናት ያስቆጠረውን የህዝቦች የመንገድ ተደራሽነት ጥያቄ መመለስ የሚያስችል አቅጣጫ ተከትሏል፡፡ ኢህአዴግ የሚመራው ልማታዊ መንግስታችን ከዓመታዊ በጀቱ እስከ 40 በመቶ ያክሉን የሀገሪቱ የካፒታል በጀት ለመንገድ ዘርፍ በመመደብ ለህዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ያለውን ቁርጠኛ አቋም በተግባር አረጋግጧል።
በሀገራችን 1983 . የነበረው አጠቃላይ የመንገድ ርዝመት 18 ሺህ ኪሎ ሜትር አካባቢ የነበረ ሲሆን ዛሬ ኢህአዴግ ገጠር ከከተማ ባማከለ የልማት አቅጣጫ ህዝቡን አስተባብሮ አጠቃላዩን የሀገሪቱ ልማት በተፋጠነ እድገት ይዞ ለመጓዝ ባደረገው ርብርብ የሀገሪቱን አጠቃላይ የመንገድ ርዝመት 105ሺህ ኪሎ ሜትር ማድረስ ችሏል፡፡ በዚህም 10ሺህ 765 የገጠር ቀበሌዎች ከዋና ዋና መንገዶች ጋር ተገናኝተዋል፡፡ በተለያዩ የአገራችን ጫፎች በመንገድ እጦትና በአቅራቢያቸው የህክምና አገልግሎት ባለማግኘት ወደ ጤና ጣቢያ መድረስ አቅቷቸው በምጥ የሚሰቃዩ እናቶችና በህመም የሚንገላቱ ህጻናትና አረጋውያንን የዘመናት ብሶት መፍትሄ ለማግኘት ጥረት የተደረገው ኢህአዴግ ለትራንስፖርት ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት ነው። 
በዚህ አመት ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረውና 84 .ሜትር የሚረዝመው የአዲስ አበባ - አዳማ የፍጥነት መንገድ ከዚህ በፊት እስከ 3 ሰዓት ድረስ ይፈጅ የነበረውን ጉዞ አሁን ወደ 45 ደቂቃ ማውረድ ያስቻለ ነው። በቀን እስከ 20 መኪናዎችን የማስተናገድ አቅም ያለው ይህ መንገድ የምስራቁንና የደቡቡን የአገሪቱን ክፍል ከመካከለኛው የአገራችን ክፍል ጋር በማስተሳሰርና የወጪና የገቢ ንግዱን በማፋጠን የላቀ ድርሻ እያበረከተ ይገኛል። በግንባታው ከተሳተፉት ውስጥ 90 በመቶ ያክሉ ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ሲታይ ደግሞ አገራዊ አቅማችንን ለማጎልበት ያስቀመጥነው አቅጣጫ ተፈፃሚ መሆኑን የሚያሳይ ነው።
በመንገድ ልማት በተገኛው ውጤት ቀደም ሲል ዜጎች የመኪና መንገድ ለመድረስ በአማካይ 10 ሰአት ሲወስድባቸው የነበረውን ወደ 1 ሰአት ተኩል ለማውረድ ተችሏል። ይህም የሚያሳየው በኢህአዴግ እየተረጋገጠ ያለው ልማት ምን ያህል የህዝብ ተጠቃሚነትን እያረጋገጠ መሆኑን ነው፡፡ የመንገድ ልማታችን ቀደም ሲል የነበረውን የመንገድ የጥራት ደረጃ ችግር በእጅጉ ያሻሻለና በውጤቱ ከአንዱ ቦታ ወደሌላው ለመጓዝ ይወስድ የነበረውን ረጅም ጊዜም በከፍተኛ ደረጃ አሳጥሯል፡፡
ኢህአዴግ በአገር ውስጥ የተቋራጮችን አቅም በመገንባት በአገራችን የሚከናወኑት የመሰረተ ልማት ስራዎች በውስጥ አቅም እንዲከናወኑ ባለው ከፍተኛ ተነሳሽነት ይህ ዘርፍ ጎን ለጎን የሀገር ውስጥ ተቋራጮችና አማካሪዎች ዓቅም የሚገነባበት ሆኗል። በዘርፉ የአገር ውስጥ ተቋራጮችንና አማካሪዎች አቅም በማጎልበት ሀገራችን በራሷ አቅም ትላልቅ ፕሮጀክቶች ማከናወን የምትችልበት ደረጃ ላይም እየደረሰች ነው። በዚህም በአሁኑ ወቅት አንድ አገር በቀል ተቋራጭ 2 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ፕሮጀክት አሸንፎ መሥራት የሚችልበት አቅም ላይ ደርሰናል፡፡
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች፣        
በኢህአዴግ ትክክለኛ አቅጣጫ በባቡር ትራንስፖርት ንዑስ ዘርፍም አዲስ ታሪክ መጻፍ ተጀምሯል፡፡ በአገራችን የሚመረቱ ምርቶችን በብዛት፣ በፍጥነትና በተነፃፃሪ በአነስተኛ ዋጋ ወደ ዓለም ገበያ ለማቅረብ የባቡር ትራንስፖርት ያለውን ፋይዳ በመረዳት የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅዶችን በማቀድ የባቡር መስመር ዝርጋት በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ኢኮኖሚን ለመገንባት የምታደርገውን ሁለገብ ጥረት የሚያግዝ፣ ከብክለት የፀዳና በኤሌክትሪክ ሃይል የሚሰራ፣ የሀገሪቱን የልማት ማዕከላት የሚያስተሳስር እንዲሁም ከጎረቤት ሀገሮች ወደቦች ጋር የሚያገናኝ 2 ሺህ 395 ኪሎ ሜትር ዘመናዊ የባቡር መሰረተ ልማትና አገልግሎት ለመገንባት አቅደን እየተረባረብን እንገኛለን፡፡ በዚሁ መሰረት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የአገራችን ጫፎች የባቡር መሰረተ ልማት ግንባታው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
በአገራችን 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት የተጀመረ ቢሆንም ዘርፉ በበርካታ ተግዳሮቶች የተተበተበ በመሆኑ ሊዘልቅ አልቻለም፡፡ ዛሬ በአገራችን በኢህአዴግ መሪነትና በህዝባችን ያልተቆጠበ ድጋፍ እየተካሄደ ያለው የባቡር ትራንስፖርት ልማት የእስካሁኑን ታሪካችንን የሚያድስና የህዝባችንን ዘላቂ ተጠቃሚነትም በተጨባጭ የምናረጋግጥበት አዲስ ምዕራፍ እንደሚሆን ኢህአዴግ በፅናት በማመን እየሰራ ይገኛል።
ግንባታው 95 በመቶ በላይ ተጠናቅቆ የፍተሻና ሙከራ ደረጃ ላይ የሚገኘው የመዲናችን አዲስ አበባ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት በሁለት አቅጣጫ በአንድ ሰዓት 60 ሺህ መንገደኞችን ማጓጓዝ እንዲችል ተደርጎ እየተገነባ ነው፡፡ 34 ነጥብ 35 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ይህ ፕሮጀክት በአጭር ጊዜ ለህብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል። የከተማውን የትራንስፖርት ችግርም በወሳኝ መልኩ እንደሚያቃልለው የሚጠበቅ ሲሆን አዲስ አበባ ከተማንም ዘመናዊ የሆነ የባቡር ትራንስፖርት ያላት የዲፕሎማቲክ ከተማ ያደርጋታል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በአዲስ አበባ ቀላል ፕሮጀክት ግንባታ ወቅት ሲፈጠር የነበረውን ከፍተኛ የትራንስፖርት ችግር በመቋቋም ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ላደረጉት አስተዋጽኦ ኢህአዴግ ከፍተኛ ምስጋናውን ለማቅረብ ይወዳል፡፡
የአገር አቋራጭ የባቡር መስመር ዝርጋታ ስራችን በረዥምና አጭር ጊዜ የሚተገበር ሆኖ በአገር አቀፍ ደረጃ በመጀመሪያው ምእራፍ ከተካተቱት ውስጥ 656 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የአዲስ አበባ-አዳማ-ድሬዳዋ-መኤሶ-ደወሌ-ጅቡቲ መስመር ይገኝበታል። ፕሮጀክቱ ከአዲስ አበባ እስከ አዳማ ድረስ ባለ ሁለት አቅጣጫ ሲሆን ቀሪው ባለ አንድ አቅጣጫና 55 በላይ ጣቢያዎች ያሉት ነው፡፡ ለፕሮጀክቱ 3.4 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር የተበጀተለት ሲሆን ባቡሩ ሥራ ሲጀምር በአንድ ጊዜ እስከ 4000 ቶን ጭነት ያጓጉዛል፡፡ የፕሮጀክቱ ስራም 78 በመቶ ገደማ ተጠናቋል፡፡ ፕሮጀክቱ እስከ ሚቀጥለው አመት አጋማሽ ድረስ እንደሚጠናቀቅም ይጠበቃል፡፡
42 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚገመተው የመቀሌ- ወልዲያ- ሀራ ገበያ የባቡር መሰረተ ልማት ግንባታ በይፋ ተጀምሯል። የአዋሽ-ኮምቦልቻ-ሃራ ገበያ የምድር ባቡር ፕሮጀክት ደግሞ 15 በላይ ጣቢያዎች የሚኖሩት ሲሆን 375 ኪሎ ሜትር ርዝመት ይኖረዋል፡፡ የሰበታ-ኢጃጅ-ጅማ-ጉራፈርዳ-ዲማ/ጅማ-በደሌ ፕሮጀክት 740 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውና 25 ጣቢያዎች አገልግሎት እንዲሰጥ ሆኖ የሚገነባ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከደቡብ ሱዳን ጋርም የሚያገናኝም ይሆናል፡፡ የሞጆ-ሻሸመኔ/ሀዋሳ-ኮንሶ-ወይጦ-ኮንሶ ሞያሌን እንዲያገናኝ ሆኖ የሚገነባው የባቡር መስመር እንዲሁ ከኬንያ ጋር በባቡር ትራንስፖርት የሚያስተሳስረን ፕሮጀክት ነው።
በአገር አቀፍ ደረጃ በመካሄድ ላይ ያለው የባቡር መስመር ዝርጋታ የሀገራችን ወጪና ገቢ ምርቶችን በተሻለ ፍጥነት በማስወጣትና በማስገባት በጉዞ ይባክን የነበረውን ጊዜ በመቆጠብ አገራችን ከዘርፉ የምታገኘውን ጥቅምና አቅም ያሳድጋል።  በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያን ከጎረቤት አገሮች ጋር በማገናኘት በአገራቱ መካከል የሚኖረውን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግንኙነትና ትስስር በእጅጉ የተሳለጠ የሚያደርግና ኢህአዴግ የአገራችንን ህዳሴ እውን ለማድረግ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የባቡር ትራንስፖርት ለቀጣይ የህዳሴ ጉዟችን ልዩ ትርጉም ያለውና የሀገራችን ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በማድረግ የህዳሴ ጉዟችን በተጀመረው ፍጥነት እንዲቀጥል የሚያስችል በመሆኑ ኢህአዴግ ለተፈፃሚነቱ ከህዝባችን ጋር መስራቱን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ 
በህዝብ ትራንስፖርት ከፍተኛ መሻሻል የታየበት ሌላው ንኡስ ዘርፍ የአየር ትራንስፖርት ነው። በአሁኑ ጊዜ አለማችን ያፈራቻቸው እንደ ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አይነት ዘመናዊ አውሮፕላኖች ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተደራሽነቱ፣ በአገልግሎት ጥራቱና በተወዳዳሪነቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህ አገራችን ከአፍሪካም ሆነ ከሌሎች የዓለም አገራት ጋር ያላትን ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ ሆኗል። በአገር ውስጥ አራት አለም አቀፍ ኤርፖርቶች ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። በተመሳሳይ የሀገር ውስጥ በረራ የሚያስተናግዱ ኤርፖርቶች ብዛት ወደ 17 በማሳደግ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት የኢኮኖሚ እድገታችንን በሚመጥን ሁኔታ የውሃ ትራንስፖርት ዘርፉ ተወዳዳሪ እንዲሆን አቅምን፣ አደረጃጀትንና ሎጂስቲክን ማሟላት ላይ ያተኮረ ሰፊና ተደጋጋሚ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። በዚህም መርከቦቻችን ከነበራቸው 50 ሺህ ቶን የመጫን ዓቅም ወደ 400ሺህ ከፍ ማድረግ ተችሏል። ሀገራችን በወጪና ገቢ ንግድ የገበያ ውድድር ሲያጋጥማት የነበረውን ዘርፈ ብዙ ችግር የመጫን አቅማቸው ከፍተኛ በሆኑ መርከቦቿ ከመፈታቱ በተጨማሪ ያለ ምንም ተጨማሪ መጉላላት ተፈላጊ ምርቶች በወቅቱ እንዲገቡና እንዲወጡ ማድረግ ችላለች። ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ በወጪና ገቢ ንግዱ ለውጭ ሀገር እቃ ጫኝ መርከቦች ሲወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሬ በከፍተኛ ደረጃ ማዳን  ተችሏል። የመልቲ ሞዳል አገልግሎት በሀገር ውስጥ በመጀመርም የወጪና የጊዜ ብክነትን ብሎም የወደብ ትራፊክ መጨናነቅን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ተችሏል።  
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች፣
ኢህአዴግ ከእናንተው ጋር በመሆን በአገራችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥና የሀገራችንን ቀጣይ ዕድገት ለማፋጠን በወሰዳቸው ኃላፊነት የተሞላባቸው ውሳኔዎችና ቁርጠኛ አፈፃፀሞች የትራንስፖርት ልማት ዘርፉ ከአንድ የስኬት ምዕራፍ ወደ ሌላ ከፍተኛ የስኬት ምዕራፍ እየተሸጋገረ በከተማና በገጠር፣ በአገራችንና በጎረቤት አገሮች መካከል ያለውን ትስስር በማጠናከር ላይ ይገኛል። የትራንስፖርት ዘርፍ ልማታችን በበርካታ ድሎች የታጀበና በእርግጥም እመርታዊ ለውጥ የታየበት ቢሆንም ግን አሁንም መሻሻል ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ኢህአዴግ ይገነዘባል፡፡ በአንድ በኩል የጥራት ችግር በሌላ በኩል ፈጣኑ እድገታችን ያመጣው ከፍተኛ ፍላጎት እስካሁን ከፈፀምነው የበለጠ እንድንሰራ የግድ የሚሉን መሆናቸውንም ይገነዘባል።
በአንጻሩ ኢህአዴግ የሰራውን ማንኛውም ስራ በትክክለኛ ትችት ሳይሆን ተጨባጭ ስኬቶችን ጥላሸት መቀባት ላይ የተጠመዱት የአገራችን ተቃዋሚዎች አማራጭ ብለው የሚያቀርቡት ሃሳብም የአገራችን ህዝቦች በገሃድ የሚያውቋቸውን ስኬቶች የሚያስቀጥል ሳይሆን ወደ ኋላ የሚመልስ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ተቃዋሚዎቻችን አሁን ካለንበት ደረጃም ሆነው ጥሩውን ጥሩ፣ መጥፎውን መጥፎ ብለው ለመናገር እንኳ ድፍረት የላቸውም፡፡ ለዚህም ነው የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ጭምር የመሰከረላቸውን በአገራችን የተገነቡና እየተገነቡ ያሉ መሰረተ ልማቶችን ጭምር ማየት የተሳናቸው፡፡
ኢህአዴግ ከተግባር በመማር የተሻለ ለውጥ እያስመዘገበ በስኬቶች ታጅቦ የመጣ ህዝባዊ ድርጅት በመሆኑ በቀጣይነት በትራንስፖርት ዘርፍ የሚታዩ ችግሮችንም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ከህዝባችን ጋር በመሆን በአስተማማኝ ሁኔታ እንደሚፈታቸው ያለፈባቸው ምዕራፎች ምስክሮች ናቸው፡፡ በህዝባችን ያልተቆጠበ ትግልና በኢህአዴግ መሪነት አሁንም እየጎመራ የመጣውን የትራንስፖርት ዘርፍ ልማት ስኬት ወደ ላቀ ደረጃ እናሸጋግራለን።
ኢሕአዴግን ምረጡ፣ ምልክታችን ጣፋጩን ማር የምታመርተው ንብ ነች።